ኢሳይያስ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ክፉንም ጽሕፈት ለሚጽፉ ወዮላቸው! 2 መበለቶች ቅሚያቸው እንዲሆኑ፥ የሙት ልጆችንም ብዝበዛቸው እንዲያደርጉ፥ የድሃውን ፍርድ ያጣምሙ ዘንድ፥ የችግረኛውንም ሕዝቤን ፍርድ ያጐድሉ ዘንድ የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ ወዮላቸው! 3 በተጐበኛችሁበት ቀን፥ ምን ታደርጉ ይሆን? መከራ ከሩቅ ይመጣባችኋልና፥ ለረድኤትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? 4 በሐሣር እንዳትወድቁ፥ ክብራችሁን ወዴት ትተዉታላችሁ? በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። 5 ለቍጣዬ በትር ለሆኑ፥ ለመዓቴም ጨንገር በእጃቸው ላለ ለአሦራውያን ወዮላቸው! 6 ቍጣዬን በኀጢአተኛ ሕዝብ ላይ እልካለሁ፤ ይማርኳቸውና ይበዘብዙአቸው ዘንድ፥ ከተሞችንም ይረግጡአቸውና እንደ ትቢያ ያደርጓቸው ዘንድ ሕዝቤን አዝዛለሁ። 7 እርሱ በልቡ እንዲህ አይመስለውም፤ እንዲህም አያስብም፤ ነገር ግን ማጥፋት፥ ጥቂት ያይደሉትንም አሕዛብ መቍረጥ በልቡ አለ። 8 “አንተ ብቻህን አለቃ ነህን?” ቢሉትም፥ የሔማትን መንደር ወሰድሁ ይላል። 9 እንደ ሔማት አርፋድ፥ እንደ አርፋድ ሴፋሩሔም፥ እንደ ሴፋሩሔም ካሌና፥ እንደ ካሌናም ደማስቆ፥ እንደ ደማስቆም ሰማርያ አይደለችምን? 10 ይሁዳንም እንዲሁ አደርጋታለሁ፤ በኢየሩሳሌምና በሰማርያ የሚያድን ጣዖት አለን? 11 በሰማርያና በጣዖቶችዋም እንዳደረግሁ፥ እንዲሁ በኢየሩሳሌምና በጣዖቶችዋ አደርጋለሁ። 12 ስለዚህ እንዲህ ይሆናል፤ ጌታ ሥራውን ሁሉ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ በፈጸመ ጊዜ የአሦርን ንጉሥ የኵሩ ልብን ፍሬ፥ የዐይኑንም ከፍታ ትምክሕት ይቀጣል። 13 እርሱ እንዲህ ብሎአልና፥ “በኀይሌ አደርጋለሁ፤ በማስተዋል ጥበቤም የአሕዛብን ድንበሮች አርቃለሁ፤ ሀብታቸውንም እዘርፋለሁ፤ 14 የሚቀመጡባቸውንም ከተሞች አናውጣለሁ። በእጄም ዓለምን ሁሉ እንደ ወፍ ቤት እሰበስባለሁ፤ እንደ ተተወ እንቍላልም እወስዳቸዋለሁ፤ ከእኔም የሚያመልጥ የለም፤ የሚቃወመኝም የለም። 15 “በውኑ መጥረቢያ በሚቈርጥበት ሰው ላይ ይነሣልን? ወይስ መጋዝ በሚስበው ሰው ላይ ይጓደዳልን? ይህም ዘንግ በሚመቱበት ላይ እንደ መነሣት፥ በትርም ዕንጨት አይደለሁም እንደ ማለት ነው።” 16 ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በክብርህ ላይ ውርደትን፥ በጌጥህ ላይም የሚነድና የሚያቃጥል እሳትን ይሰድዳል። 17 የእስራኤልም ብርሃን እንደ እሳት ይሆናል፤ በሚነድድ እሳትም ይቀድሰዋል፤ ዛፉንም እንደ ሣር ያቃጥለዋል። 18 ያንጊዜ ተራሮችና ኮረብቶች፥ ዛፎችም ይጠፋሉ። ነፍስና ሥጋንም ይበላል፤ የሚሸሽም ከሚነድድ የእሳት ነበልባል እንደሚሸሽ ይሆናል። 19 የቀሩትም የዱር ዛፎች በቍጥር ጥቂት ይሆናሉ፤ ታናሽ ብላቴናም ይጽፋቸዋል። የእስራኤል ቅሬቶች 20 በዚያም ጊዜ እንዲህ ይሆናል፤ የእስራኤል ቅሬታ ከያዕቆብም ቤት የዳኑት ከእንግዲህ ወዲህ በአቈሰሉአቸው ላይ አይደገፉም፤ ነገር ግን በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ በእውነት ይደገፋሉ። 21 የያዕቆብም ቅሬታ በኀያሉ እግዚአብሔር ይጸናሉ። 22 የእስራኤልም ሕዝብ ቍጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆን የቀሩት ይድናሉ። 23 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀና የተቈረጠ ነገርን በዓለም ሁሉ በእውነት ይፈጽማል። 24 ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በጽዮን የምትኖር ሕዝቤ ሆይ፥ ከአሦር የተነሣ አትፍራ፤ በበትር ይመቱሃልና፥ የግብፅንም መንገድ ታይ ዘንድ መቅሠፍቴን አመጣብሃለሁና። 25 ለጥቂት ጊዜ ቍጣዬ ይበርዳል፤ ነገር ግን መዓቴ በምክራቸው ላይ ይሆናል።” 26 እግዚአብሔርም ምድያምን በመከራው ቦታ እንደ መታው ጅራፍን ያነሣበታል፤ ቍጣውም በባሕሩ መንገድና በግብፅ መንገድ በኩል ይሆናል። 27 በዚያም ቀን ቀንበሩ ከጫንቃህ፥ ፍርሀቱም ከአንተ ላይ ይወርዳል፤ ቀንበሩም ከጫንቃህ ወርዶ ይሰበራል። 28 ወደ አንጋይ ከተማ ይመጣል፤ በመጌዶን በኩል ያልፋል፤ በማክማስም ውስጥ ዕቃውን ያኖራል፤ 29 በቆላ ያልፋል፤ ወደ አንጋይም በደረሰ ጊዜ ሬማትና የሳኦል ከተማ ገባዖን ይፈራሉ፤ 30 የጋሊም ልጅ ትሸሻለች፤ ላይሳም ትሰማለች፤ አናቶትም ትሰማለች። 31 መደቤናና በጌቤር የሚኖሩ ይደነግጣሉ። 32 ዛሬ በእጁ እንዲኖሩ በመንገዱ ለምኑ፤ የጽዮን ልጅ ተራራንና የኢየሩሳሌምን ኮረብቶች አጽኑ። 33 እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ክቡራንን በኀይል ያውካቸዋል፤ ታላላቆችንም በሐሣር ይቀጠቅጣቸዋል፤ ከፍ ያሉትም ይዋረዳሉ። 34 ታላላቆችም በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ሊባኖስም ከረዣዥም ዛፎች ጋር ይወድቃል። |