መዝሙር 33 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ባሳደደው በአቤሜሌክ ፊት መልኩን በለወጠ ጊዜ፥ በሄደም ጊዜ የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ። ምስጋናውም ዘወትር በአፌ ነው። 2 ነፍሴም በእግዚአብሔር ትከብራለች፥ ገሮችም ይስሙ፥ ደስም ይበላቸው። 3 እግዚአብሔርን ከእኔ ጋር ከፍ ከፍ አድርጉት፥ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ። 4 እግዚአብሔርን ፈለግሁት መለሰልኝም፥ ከመከራዬም ሁሉ አዳነኝ። 5 ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፥ ፊታችሁም አያፍርም። 6 ይህ ችግረኛ ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው፥ ከመከራውም ሁሉ አዳነው። 7 የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል። 8 እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ፥ ዕወቁም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ብፁዕ ነው። 9 ለሚፈሩት ችግር የለባቸውምና ቅዱሳን ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፍሩት። 10 ባለጠጎች ደኸዩ፥ ተራቡም፥ እግዚአብሔርን የሚፈልጉት ግን ከመልካም ነገር ሁሉ አልተቸገሩም። 11 ልጆቼ ኑ፥ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችሁ ዘንድ፤ 12 ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው? 13 አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ። 14 ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን ሻት፥ ተከተላትም። 15 የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃኑ፥ ጆሮቹም ወደ ልመናቸው ናቸውና። 16 መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው። 17 ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው፥ ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው። 18 እግዚአብሔር በልባቸው የዋሃን ለሆኑ ቅርብ ነው፥ በመንፈስ ትሑታን የሆኑትንም ያድናቸዋል። 19 የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል። 20 እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፥ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም። 21 የኃጥእ ሞቱ ክፉ ነው ጽድቅንም የሚጠሉ ይጸጸታሉ። 22 የባሪያዎቹን ነፍስ እግዚአብሔር ይቤዣል፥ በእርሱም የሚያምኑ ሁሉ አይጸጸቱም። |