ሚልክያስ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 በሚልክያስ እጅ ለእስራኤል የሆነ የጌታ ቃል ይህ ነው። ከኤዶም ይልቅ እስራኤል ተወደደ 2 ወድጃችኋለሁ ይላል ጌታ፤ እናንተ ግን፦ “እንዴት ወደድከን?” ትላላችሁ። ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ይላል ጌታ። ሆኖም ያዕቆብን ወደድኩት። 3 ዔሳውን ግን ጠላሁት፤ ተራራውን አጠፋሁ፥ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮች ሰጠኋቸው። 4 ኤዶም፦ “እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን” ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ የክፋት አገር፥ ጌታ ለዘለዓለም የተቆጣው ሕዝብ ብለው ይጠሩአቸዋል።” 5 ዐይኖቻችሁም ያያሉ፥ እናንተም፦ “ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ ጌታ ታላቅ ይሁን!” ትላላችሁ። የካህናት ምግባረ ብልሹነት 6 “ስሜን የምትንቁ ካህናት ሆይ፥ ልጅ አባቱን፥ ባርያም ጌታውን ያከብራል፥ እኔ አባት ከሆንሁ መከበሬ የት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ?” ይላችኋል የሠራዊት ጌታ። እናንተም፦ “ስምህን የናቅነው እንዴት ነው?” ብላችኋል። 7 “በመሠዊያዬ ላይ የረከሰ ምግብ ታቀርባላችሁ።” እናንተም፦ “ያረከስንህ እንዴት ነው?” ትላላችሁ። “የጌታ ገበታ የተናቀ ነው” በማለታችሁ ነው። 8 “የታወረውን ለመሥዋዕት ስታቀርቡ፥ ይህ ክፉ አይደለምን? አንካሳውንና የታመመውን ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? ይህንን ለገዢህ አቅርብ፤ በውኑ በአንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ፊትህንስ ይቀበላልን?” ይላል የሠራዊት ጌታ። 9 “አሁንም እንዲራራልን የእግዚአብሔርን ፊት ለምኑ፤ ይህ ከእጃችሁ የተሰጠ ሲሆን ከቶ ፊታችሁን ይቀበላልን?” ይላል የሠራዊት ጌታ። 10 “በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ መካከል በሮችን የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም፥” ይላል የሠራዊት ጌታ። ቁርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም። 11 “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በሕዝቦች መካከል ታላቅ ይሆናል፤ በሁሉም ስፍራ ለስሜ ዕጣን ያመጣሉ፥ ንጹሕ ቁርባንም ያቀርባሉ፤ ስሜ በሕዝቦች መካከል ታላቅ ይሆናል፥” ይላል የሠራዊት ጌታ። 12 እናንተ ግን፦ “የጌታ ገበታ የረከሰ ነው፤ ፍሬውና ምግቡም የተናቀ ነው በማለታችሁ አረከሳችሁት። 13 “እነሆ፥ ይህ ድካም ነው ብላችሁ ጢቅ አላችሁበት፥” ይላል የሠራዊት ጌታ፤ “የተሰረቀውን፥ አንካሳውንና የታመመውን አምጥታችኋል፤ እንዲሁም ቁርባንን አምጥታችኋል፤ በውኑ ከእጃችሁ መቀበል ይገባኛልን?” ይላል ጌታ። 14 “በመንጋው ውስጥ ተባዕት እያለው ለጌታ ተስሎት እያለ ነውር ያለበትን የሚሠዋ ተንኮለኛ ሰው የተረገመ ነው። እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝና፥” ይላል የሠራዊት ጌታ፥ “ስሜም በሕዝቦች መካከል የተፈራ ነውና።” |