ዘዳግም 26:18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ርስቱና ሕዝቡ ትሆን ዘንድ፥ ትእዛዙንም ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ ዛሬ መርጦሃልና፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት አንተ፣ ሕዝቡና ርስቱ መሆንህን፣ ትእዛዙንም ሁሉ እንደምትጠብቅ በዛሬው ዕለት ተናግሯል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ በሰጠህ ተስፋ መሠረት አንተ ሕዝቡና ርስቱ መሆንህን፥ ትእዛዙንም ሁሉ እንደምትጠብቅ ዛሬ ተናግሮአል፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ስለዚህም እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት እነሆ፥ ዛሬ ለእርሱ የተለየህ ውድ ሕዝብ አድርጎ ተቀብሎሃል፤ ትእዛዞቹንም ሁሉ እንድትፈጽም ያዝሃል፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም እንደ ሰጠህ ተስፋ ገንዘቡና ሕዝቡ መሆንህን፥ ትእዛዙንም ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ |
ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፤ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
መታጠቂያ በሰው ወገብ ላይ እንደምትጣበቅ፥ እንዲሁ ለስም፥ ለመመኪያና ለክብር ሕዝብ ይሆኑልኝ ዘንድ የእስራኤልን ቤት ሁሉ፥ የይሁዳንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣብቄአለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን አልሰሙም።”
በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፥ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፣ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፥ በምድርም ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ እግዚአብሔር አንተን መርጦአልና።
“እንዲህም ይሆናል፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽመህ ብትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ትእዛዙን ሁሉ ብታደርግ፥ ብትጠብቅም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከምድር አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል።
የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትሰማ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር ለአባቶችህ እንደ ማለ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል።
ዛሬ ለእርሱ ሕዝብ ያደርግህ ዘንድ፥ እርሱም ለአንተ እንደ ተናገረ ለአባቶችህም ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንደ ማለ አምላክ ይሆንልህ ዘንድ ነው።
“ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦሃልና።
መድኃኒታችንም ከዐመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል።
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤