ኤርምያስ 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከተልባ እግር የተሠራ መታጠቂያ 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል፦ ሂድ፥ ከተልባ እግር የተሠራችን መታጠቂያ ለአንተ ግዛ፤ ወገብህንም ታጠቅባት፤ በውኃውም ውስጥ አትንከራት። 2 እግዚአብሔርም እንዳለኝ የተልባ እግር መታጠቂያን ገዛሁ፤ ወገቤንም ታጠቅሁባት። 3 ዳግመኛም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ 4 “ለወገብህ የገዛሃትን ያቺን መታጠቂያ ወስደህ ተነሥ፤ ወደ ኤፍራጥስም ሂድ፤ በዚያም በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ ሸሽጋት።” 5 እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ ሄድሁ፤ በኤፍራጥስም ወንዝ አጠገብ ሸሸግኋት። 6 ከብዙ ቀንም በኋላ እግዚአብሔር፥ “ተነሥተህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፥ በዚያም ትሸሽጋት ዘንድ ያዘዝሁህን መታጠቂያ ከዚያ ውስጥ ውሰድ” አለኝ። 7 እኔም ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ሄድሁ፤ ቈፈርሁም፤ ከቀበርሁበትም ስፍራ መታጠቂያዪቱን ወሰድሁ። እነሆም መታጠቂያዪቱ ተበላሽታ ነበር፤ ለምንም አልረባችም። 8 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እንዲሁ የይሁዳን ትዕቢት፥ ታላቁንም የኢየሩሳሌምን ትዕቢት አበላሻለሁ። 10 ቃሌን ይሰሙ ዘንድ እንቢ የሚሉ፥ በክፉ ልባቸውም እልከኝነት የሚሄዱ፥ ያገለግሏቸውና ይሰግዱላቸው ዘንድ ሌሎችን አማልክት ተከትለው የሚሄዱ እነዚህ ክፉ ሕዝብ አንዳች እንደማትረባ እንደዚች መታጠቂያ ይሆናሉ። 11 መታጠቂያ በሰው ወገብ ላይ እንደምትጣበቅ፥ እንዲሁ ለስም፥ ለመመኪያና ለክብር ሕዝብ ይሆኑልኝ ዘንድ የእስራኤልን ቤት ሁሉ፥ የይሁዳንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣብቄአለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን አልሰሙም።” የወይን ጠጅ ማድጋ 12 ስለዚህ፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ ይሞላል” ብለህ ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱም፥ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ እንዲሞላ በውኑ እኛ አናውቅምን?” ቢሉህ፤ 13 አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡትን ነገሥታት፥ ካህናቱንም፥ ነቢያቱንም፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ። 14 ሰውንና ወንድሙን፥ አባቶችንና ልጆችን በአንድ ላይ እበትናቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ አጠፋቸዋለሁ እንጂ አልራራላቸውም፤ አላዝንላቸውም፤ አልምራቸውምም።” ኤርምያስ ስለ ትዕቢት የሰጠው ማስጠንቀቂያ 15 ስሙ፤ አድምጡ፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና አትታበዩ። 16 ሳይጨልምባችሁ፥ ጨለማም ባለባቸው ተራሮች እግሮቻችሁ ሳይሰነካከሉ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ፤ በዚያም የሞት ጥላ አለና በጨለማውም ውስጥ ያኖራችኋልና ብርሃንን ተስፋ ታደርጋላችሁ። 17 ይህን ባትሰሙ ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ በስውር ታለቅሳለች፤ የእግዚአብሔርም መንጋ ተሰብሮአልና ዐይኔ ታነባለች፤ እንባንም ታፈስሳለች። 18 ለነገሥታቱና ለመኳንንቱ፦ የክብራችሁ አክሊል ከራሳችሁ ወርዶአልና ራሳችሁን አዋርዳችሁ ተቀመጡ በላቸው። 19 የደቡብ ከተሞች ተዘግተዋል፤ የሚከፍታቸውም የለም፤ ይሁዳ ሁሉ ተሰድዶአል፤ ፈጽሞም ተሰድዶአል። 20 ኢየሩሳሌም ሆይ! ዐይንሽን አንሥተሽ እነዚህን ከሰሜን የሚመጡትን ተመልከቺ፤ ለአንቺ የሰጠሁሽ መንጋ፤ የክብር በጎችሽ ወዴት አሉ? 21 አንቺ ትምህርት ያስተማርሻቸው አለቆችሽ ሆነው በጐበኙሽ ጊዜ ምን ትያለሽ? እንደ ወላድ ሴት ምጥ አይዝሽምን? 22 በልብሽም፦ እንዲህ ያለ ነገር ስለ ምን ደረሰብኝ? ብትዪ፥ ከኀጢአትሽ ብዛት የተነሣ ልብስሽ በስተኋላሽ ተገፎአል፤ ተረከዝሽም ተገልጦአል። 23 በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያ ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁን? 24 ነፋስ በምድረ በዳ እንደሚበትነው እብቅ እበትናችኋለሁ። 25 ረስተሽኛልና፥ በሐሰትም ታምነሻልና ዕጣሽና እድል ፈንታሽ ይህ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር። 26 ስለዚህም የልብስሽን ዘርፍ በስተኋላሽ ወደ ፊትሽ እገልጣለሁ እፍረትሽም ይታያል። 27 አስጸያፊ ሥራሽን፥ ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የዝሙትሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ፥ በሜዳም ላይ አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ! ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል፤ ይህስ እስከ መቼ ነው? |