ዘፀአት 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእስራኤል ከግብፃውያን አርነት መውጣት እንደ ተረጋገጠ 1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “በጸናች እጅ ይለቅቃቸዋልና፥ በተዘረጋችም ክንድ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋልና አሁን በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ።” 2 እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 3 ለአብርሃምም፥ ለይስሐቅም፥ ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር። 4 የነበሩባትንም የከነዓንን ምድር እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን አቆምሁ። 5 ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ።” 6 ስለዚህም ፈጥነህ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብፃውያንም ተገዥነት አወጣችኋለሁ፤ ከባርነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ፤ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፤ 7 ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፤ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 8 ለአብርሃምና ለይስሐቅ፥ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ እጄን ወደ ዘረጋሁባት ምድር አገባችኋለሁ፤ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” 9 ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከሰውነታቸው መጨነቅ፥ ከሥራቸውም ክብደት የተነሣ ቃሉን አልሰሙትም። 10 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 11 “ግባ፤ የእስራኤልን ልጆች ከሀገሩ ይለቅቅ ዘንድ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገረው።” 12 ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት፥ “እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? እኔም አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም” ብሎ ተናገረ። 13 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ተናገራቸው፤ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ እንዲያወጣቸው ይነግሩት ዘንድ አዘዛቸው። የሙሴና የአሮን ትውልድ 14 የአባቶቻቸውም ቤት አለቆች እነዚህ ናቸው። የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች ሄኖኅ፥ ፍሉስ፥ አስሮን፥ ከርሚ፤ እነዚህ የሮቤል ትውልድ ናቸው። 15 የስምዖንም ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ አኡድ፥ ያኪን፥ ሱሐር፥ የፊኒቃዊቱም ልጅ ሳኡል፤ እነዚህ የስምዖን ትውልድ ናቸው። 16 እነዚህም እንደ ወገኖቻቸው የሌዊ ልጆች ስሞች ናቸው፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ ናቸው። የሌዊም የሕይወት ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። 17 የጌድሶንም ልጆች በየአባታቸው ወገን ሎቤኒ፥ ሰሜኢ ናቸው። 18 የቀዓትም ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል ናቸው፤ የቀዓትም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነው። 19 የሜራሪ ልጆች ሞሖሊ፥ ሐሙሲ ናቸው። እነዚህም እንደ ትውልዳቸው የሌዊ ትውልድ ናቸው። 20 እንበረምም የአባቱን ወንድም ልጅ ዮካብድን አገባ፤ አሮንንና ሙሴን፥ እኅታቸውንም ማርያምን ወለደችለት፤ የእንበረምም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። 21 የይስዓርም ልጆች ቆሬ፥ ናፌግ፥ ዝክሪ ናቸው። 22 የዑዝኤልም ልጆች ሚሳኤል፥ ኤልሳፋን፥ ሴትሪ ናቸው። 23 አሮንም የአሚናዳብን ልጅ የነአሶንን እኅት ኤልሳቤጥን አገባ። እርስዋም ናዳብንና አብዩድን፥ አልዓዛርንና ኢታምርን ወለደችለት። 24 የቆሬ ልጆች አሴር፥ ሕልቃና፥ አብያሳፍ ናቸው፤ እነዚህ የቆሬ ልጆች ትውልድ ናቸው። 25 የአሮንም ልጅ አልዓዛር ከፋትኤል ልጆች ሚስትን አገባ፤ እርስዋም ፊንሐስን ወለደችለት። እነዚህም በየወገኖቻቸው የሌዋውያን አባቶች አለቆች ናቸው። 26 እነዚህ አሮንና ሙሴ እግዚአብሔር፥ “ከግብፅ ምድር ከሠራዊቶቻቸው ጋር የእስራኤልን ልጆች አውጡ” ያላቸው ናቸው። 27 እነዚህ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ያወጡ ዘንድ ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር የተነጋገሩ ናቸው፤ እነዚህም ሙሴና አሮን ናቸው። እግዚአብሔር ለሙሴና አሮን የሰጠው ትእዛዝ 28 እግዚአብሔርም በግብፅ ሀገር ሙሴን በተናገረው ቀን እንዲህ ሆነ፤ 29 እግዚአብሔር ሙሴን፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እኔ የምነግርህን ሁሉ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር” ብሎ ተናገረው። 30 ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት፥ “እነሆ፥ እኔ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል?” አለ። |