ዘሌዋውያን 20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሕግ መተላለፍ ቅጣት 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “ደግሞ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ከእስራኤል ልጆች ወይም በእስራኤል ዘንድ ከሚቀመጡ እንግዶች ማናቸውም ሰው ዘሩን ለሞሎክ አገልግሎት ቢሰጥ ፈጽሞ ይገደል፤ የሀገሩ ሕዝብ በድንጋይ ይውገሩት። 3 መቅደሴን ያረክስ ዘንድ፥ የቅዱሳኔንም ስም ያጐስቍል ዘንድ ዘሩን ለሞሎክ አገልግሎት ሰጥቶአልና እኔ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብዳለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይች አጠፋዋለሁ። 4 ዘሩንም ለሞሎክ ሲሰጥ፥ የሀገሩ ሕዝብ ያን ሰው ቸል ቢሉት፥ አይተው እንዳላዩ ቢሆኑ፥ ባይገድሉትም፥ እኔ በዚያ ሰውና በቤተ ሰቡ ላይ ፊቴን አከብዳለሁ። 5 እርሱንና ከሞሎክ ጋር ያመነዝሩ ዘንድ የሚከተሉትን ሁሉ ከሕዝባቸው መካከል ለይች አጠፋለሁ። 6 “እነርሱን ተከትሎ ያመነዝር ዘንድ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን የሚከተል ሰው ቢኖር፥ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብዳለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይች አጠፋዋለሁ። 7 እንግዲህ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ። 8 ሕጌንና ትእዛዜን ጠብቁ፤ አድርጉትም፤ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና። 9 ማናቸውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን ቢሰድብ ፈጽሞ ይገደል፤ አባቱንና እናቱን ሰድቦአልና በደለኛ ነው። 10 “ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ወይም ከባልንጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር አመንዝራውና አመንዝራዪቱ ፈጽመው ይገደሉ። 11 ማናቸውም ሰው ከአባቱ ሚስት ጋር ቢተኛ የአባቱን ኀፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ሁለቱም ፈጽመው ይገደሉ፤ በደለኞች ናቸው። 12 ማናቸውም ሰው ከምራቱ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ፈጽመው ይገደሉ፤ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ በደለኞች ናቸው። 13 ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ በደለኞች ናቸው። 14 ማናቸውም ሰው እናቲቱንና ልጂቱን ቢያገባ ኀጢአት ነው፤ በመካከላቸው ኀጢአት እንዳይሆን እርሱንና እነርሱን በእሳት ያቃጥሉአቸው። 15 ማናቸውም ሰው ከእንስሳ ጋር ቢገናኝ ፈጽሞ ይገደል፤ እንስሳዪቱንም ግደሉአት። 16 ማንኛዪቱም ሴት ወደ እንስሳ ብትቀርብ፥ ከእርሱም ጋር ብትገናኝ፥ ሴቲቱንና እንስሳውን ግደሉ፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ በደለኞች ናቸው። 17 “ማናቸውም ሰው የአባቱን ልጅ ወይም የእናቱን ልጅ እኅቱን ቢያገባ፥ ኀፍረተ ሥጋዋንም ቢያይ፥ እርስዋም ኀፍረተ ሥጋውን ብታይ፥ ይህ ጸያፍ ነገር ነው፤ በሕዝባቸውም ልጆች ፊት ይገደሉ፤ የእኅቱን ኀፍረተ ሥጋ ገልጦአልና ኀጢአቱን ይሸከማል። 18 ማናቸውም ሰው ከባለ ግዳጅ ሴት ጋር ቢተኛ ኀፍረተ ሥጋዋንም ቢገልጥ፥ ፈሳሽዋን ገልጦአልና፥ እርስዋም የደምዋን ፈሳሽ ገልጣለችና ሁለቱ ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ። 19 የአባትህን ወይም የእናትህን እኅት ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ ይህን የሚያደርግ የዘመድን ኀፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ኀጢአታቸውን ይሸከማሉ። 20 ሰውም ከቅርብ ዘመዱ ሚስት ጋር ቢተኛ የቅርብ ዘመዱን ኀፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ያለ ልጅ ይሞታሉ። 21 ሰውም የወንድሙን ሚስት ቢያገባ ርኵሰት ነው፤ የወንድሙን ኀፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ያለ ልጅም ይሙቱ። 22 “እንግዲህ ትቀመጡባት ዘንድ የማገባችሁ ምድር እንዳትተፋችሁ ትእዛዜን ሁሉ፥ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ፤ አድርጉትም። 23 ከፊታችሁ በማወጣቸው ሕዝብ ሕግ አትሂዱ፤ ይህን ሁሉ አድርገዋልና ተጸየፍኋቸው 24 ነገር ግን እናንተ፦ ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ትወርሱአትም ዘንድ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣችኋለሁ አልኋችሁ፤ እኔ ከአሕዛብ የለየኋችሁ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ። 25 እንግዲህ በንጹሕና በርኩስ እንስሳ መካከል፥ በንጹሕና በርኩስም ወፍ መካከል ለየሁላችሁ፤ ርኩሳን ናቸው ብዬ በለየኋቸው በእንስሳና በወፍ፥ በምድርም ተንቀሳቃሽ ሁሉ ነፍሳችሁን አታርክሱ። 26 እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፥ ለእኔም ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁና ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ። 27 “ወንድ ወይም ሴት መናፍስትን ቢጠሩ፥ ወይም ጠንቋዮች ቢሆኑ ፈጽመው ይገደሉ፤ በድንጋይም ይውገሩአቸው፤ በደለኞች ናቸውና።” |