ሐዋርያት ሥራ 14:22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የደቀ መዛሙርትንም ልቡና አጽናኑ፤ በሃይማኖትም እንዲጸኑ፦“ በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል” እያሉ መከሩአቸው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የደቀ መዛሙርቱንም ልብ በማበረታታትና በእምነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ በመምከር፣ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ማለፍ አለብን” አሏቸው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በእነዚያም አገሮች ሁሉ አማኞች በእምነታቸው እንዲጸኑ በማበረታታትና በመምከር “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ብዙ መከራ መቀበል አለብን” እያሉ አስተማሩአቸው። |
አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።
ዐይንህ ብታሰናክልህ አውጣት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነመ እሳት ከመጣል አንዲት ዐይን ኖራህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል።
እኔ፦ ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም ያልኋችሁን ቃሌን ዐስቡ፤ እኔን ካሳደዱ እናንተንም ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ቢሆንስ ቃላችሁንም በጠበቁ ነበር።
በእኔም ሰላምን እንድታገኙ ይህን ነገርኋችሁ፤ በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ፤ እኔ ዓለሙን ድል ነሥቼዋለሁና።”
ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።
በደረሰ ጊዜም የእግዚአብሔርን ጸጋ አየና ደስ አለው፤ በፍጹም ልባቸውም በእግዚአብሔር ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው።
በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት አብረው ተቀመጡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተብለው ተጠሩ።
ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርት እያንዳንዳቸው የሚችሉትን ያህል አወጣጥተው በይሁዳ ሀገር ለሚኖሩት ወንድሞቻቸው ርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ።
ጉባኤውም በተፈታ ጊዜ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ከተመለሱት ከደጋጉ ሰዎች ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ጸጋ ይድኑ ዘንድ እያስረዱ ነገሯቸው።
ደቀ መዛሙርቱም ከበቡት፤ ነገር ግን ተነሥቶ አብሮአቸው ወደ ከተማ ገባ፤ በማግሥቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ሄደ።
የእግዚአብሔርም ቃል ከፍ ከፍ አለ፤ በኢየሩሳሌምም ምእመናን እጅግ በዙ፤ ከካህናትም መካከል ያመኑ ብዙዎች ነበሩ።
እና የእግዚአብሔር ልጆች ከሆን ወራሾቹ ነን፤ የእግዚአብሔር ወራሾች ከሆንም የክርስቶስ ወራሾቹ ነን፤ በመከራ ከመሰልነውም በክብር እንመስለዋለን።
ይህንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቶአችኋል፤ ነገር ግን ስለ እርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም።
እንግዲህ ከሰማችሁት ከሰማይ በታች በመላው ዓለም ከተሰበከው እኔ ጳውሎስም አዋጅ ነጋሪና መልእክተኛ ሆኜ ከተሾምሁለት፥ ከወንጌል ትምህርት ተስፋ የመሠረታችሁ አቅዋም ሳይናወጥ ጨክናችሁ በሃይማኖት ብትጸኑ፥
እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኀይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ፥ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችሁማል፤ ያበረታችሁማል።
ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።
እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ።
ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ እንድፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፤ ዐሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።