ሐዋርያት ሥራ 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጳውሎስና በርናባስ በኢቆንዮን ስለ አስተማሩት ትምህርት 1 ኢቆንዮን በምትባል ከተማም እንደ ሁልጊዜው ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ ከአይሁድና ከአረማውያንም ብዙ ሰዎች እስኪያምኑ ድረስ አስተማሩ። 2 ማመንን እንቢ ያሉት የአይሁድ ወገኖች ግን የአሕዝብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ፤ አስከፉም። 3 በጌታም ፊት ደፍረው እያስተማሩ፥ እርሱም የጸጋውን ቃል ምስክር እያሳየላቸው፥ በእጃቸውም ድንቅ ሥራና ተአምራትን እያደረገላቸው ብዙ ወራት ኖሩ። 4 የከተማውም ሕዝብ ሁሉ ተለያዩ፤ እኩሌቶቹ ወደ አይሁድ፥ እኩሌቶቹም ወደ ሐዋርያት ሆኑ። 5 አሕዛብና አይሁድ ግን ከአለቆቻቸው ጋር ሊያንገላትዋቸውና በድንጋይ ሊደበድቧቸው ተነሡ። 6 ሐዋርያትም ይህን ዐውቀው ወደ ሊቃኦንያ ከተሞች ወደ ልስጥራንና ወደ ደርቤን፥ ወደየአውራጃውም ሸሹ። 7 በዚያም ወንጌልን ሰበኩ። ቅዱስ ጳውሎስ ሽባውን ስለ መፈወሱ 8 በልስጥራንም እግሩ የሰለለ፥ ከእናቱም ማኅፀን ጀምሮ ሽባ የሆነ፥ ከቶም ሂዶ የማያውቅ አንድ ሰው ተቀምጦ ነበር። 9 እርሱም ጳውሎስን ሲያስተምር ሰማው፤ ጳውሎስም ትኩር ብሎ ተመለከተው፤ እምነት እንዳለውና እንደሚድንም ተረዳ። 10 ድምፁንም ከፍ አድርጎ፥ “ተነሥና ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም እልሃለሁ” አለው፤ ወዲያውኑም ተነሥቶ ተመላለሰ። 11 ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፥ “አማልክት ሰዎችን መስለው ወደ እኛ ወረዱ” እያሉ በሊቃኦንያ ቋንቋ ጮኹ። 12 በርናባስን ድያ አሉት፤ ጳውሎስንም የትምህርቱ መሪ እርሱ ነበርና ሄርሜን ብለው ጠሩት። 13 በከተማውም ፊት ለፊት ቤተ መቅደስ ያለው የድያ ካህን ኮርማዎችንና የአበባ አክሊሎችን ወደ ደጃፍ አመጣ፤ ከሕዝቡም ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ወደደ። 14 ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስም በሰሙ ጊዜ፥ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ፈጥነውም እየጮኹ ወደ ሕዝቡ ሄዱ። 15 እንዲህም አሉአቸው፥ “እናንተ ሰዎች፥ ይህን ነገር ለምን ታደርጋላችሁ? እኛስ እንደ እናንተ የምንሞት ሰዎች አይደለንምን? ነገር ግን ይህን ከንቱ ነገር ትታችሁ ሰማይና ምድርን፥ ባሕርንም በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ትመለሱ ዘንድ ወንጌልን እናስተምራችኋለን። 16 አሕዛብን ሁሉ በቀድሞ ዘመን እንደ ነበሩበት እንደ ጠባያቸው ሊኖሩ ተዋአቸው። 17 ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራን እየሠራ ከሰማይ ዝናምን፥ ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” 18 ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በግድ አስተዉአቸው። 19 አይሁድም ከአንጾኪያና ከኢቆንያ መጡ፤ ልባቸውንም እንዲያጠኑባቸው አሕዛብን አባበሉአቸው፤ ጳውሎስንም እየጐተቱ ከከተማ ውጭ አውጥተው በድንጋይ ደበደቡት፤ የሞተም መሰላቸው። 20 ደቀ መዛሙርቱም ከበቡት፤ ነገር ግን ተነሥቶ አብሮአቸው ወደ ከተማ ገባ፤ በማግሥቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ሄደ። ወደ አንጾኪያ ስለ መመለሳቸው 21 በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰበኩ፤ ብዙ ሰዎችንም ደቀ መዛሙርት አድርገው ወደ ልስጥራን፥ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። 22 የደቀ መዛሙርትንም ልቡና አጽናኑ፤ በሃይማኖትም እንዲጸኑ፦“ በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል” እያሉ መከሩአቸው። 23 ለቤተ ክርስቲያንም ቀሳውስትን ሾሙ፤ ጾሙ፤ ጸለዩም፤ ለሚታመኑበት ለእግዚአብሔርም አደራ ሰጡአቸው። 24 ከጲስድያም ዐልፈው ጵንፍልያ ደረሱ። 25 ጴርጌን በተባለችው ከተማም ቃሉን ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢጣሊያ ወረዱ። 26 ከዚያም ስለሚሠሩት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ። 27 አንጾኪያም በደረሱ ጊዜ ምእመናኑን ሁሉ ሰብስበው እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ሁሉ፥ ለአሕዛብም የሃይማኖትን በር እንደ ከፈተላቸው ነገሩአቸው። 28 ከደቀ መዛሙርትም ጋር አያሌ ቀን ተቀመጡ። |