ፊልጵስዩስ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በፊልጵስዩስ ስላሉ ምእመናን 1 ከኢየሱስ ክርስቶስ ባርያዎች ከጳውሎስና ከጢሞቴዎስ፥ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ፤ ከቀሳውስትና ከዲያቆናት ጋር በኢየሱስ ክርስቶስ ላሉ ቅዱሳን ሁሉ፤ 2 ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን። የቅዱስ ጳውሎስ ጸሎት ለፊልጵስዩስ ሰዎች 3 እናንተን በማስብበት ጊዜ ሁሉ ዘወትር አምላኬን አመሰግነዋለሁ። 4 ስለ እናንተም ሁልጊዜ እጸልያለሁ፤ የደስታ ጸሎትም አደርጋለሁ። 5 ከመጀመሪያዪቱ ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ በወንጌል ትምህርት ከእኔ ጋር አንድ በመሆናችሁ፥ 6 እርሱ የጀመረላችሁን በጎውን ሥራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከሚመጣበት ቀን ድረስ እርሱ እንደሚፈጽምላችሁ አምናለሁ። 7 ስለ እናንተ ይህን ላስብ ይገባኛል፤ በምታሰርበትና በምከራከርበት፥ ወንጌልንም በማስተምርበት ጊዜ ከእኔ ጋራ በጸጋ ስለ ተባበራችሁ በልቤ ውስጥ ናችሁና። 8 በክርስቶስ ፍቅር ሁላችሁን እንደምወዳችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። 9 ስለዚህም በአእምሮና በልብ ጥበብ ሁሉ ፍቅራችሁ እንዲበዛ፥ እንዲጨምርም እጸልያለሁ፤ 10 የሚሻለውን ሥራ እንድትመረምሩና እንድትፈትኑ፥ ክርስቶስ በሚመጣበት ቀን ያለ ዕንቅፋት ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ፦ 11 ለእግዚአብሔር ምስጋናና ክብርም በኢየሱስ ክርስቶስ የጽድቅን ፍሬ ትሞሉ ዘንድ እጸልያለሁ፤ በቅዱስ ጳውሎስ መታሰር ወንጌል እንደ ተስፋፋ 12 ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወድዳለሁ። 13 ስለ ክርስቶስ ስም መታሰሬም በአደባባዩ ሁሉና በሰው ሁሉ ዘንድ ታውቆአል። 14 ከወንድሞቻችንም ብዙዎቹ በእስራቴ ምክንያት በጌታ ታመኑ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ያለ ፍርሀት ጨክነው ያስተምሩ ዘንድ እጅግ ተደፋፈሩ። 15 ከእነርሱ አንዳንዶች በቅናታቸውና በክርክራቸው፥ ሌሎችም በበጎ ፈቃድ ስለ ክርስቶስ ሊሰብኩና ሊያስተምሩ የወደዱ አሉ። 16 በፍቅር የሚያስተምሩም አሉ፤ ወንጌልን ለማስተማር እንደ ተሾምሁ ያውቃሉና። 17 በኵራት ስለ ክርስቶስ የሚያስተምሩ ግን፥ ይህን አድርገው በእስራቴ ላይ መከራ ሊጨምሩብኝ መስሎአቸው ነው እንጂ በእውነት አይደለም፤ በቅንነትም አይደለም። 18 ነገር ግን ምን አለ? በየምክንያቱ በእውነትም ቢሆን፥ በሐሰትም ቢሆን፥ ስለ ክርስቶስ ይናገራሉ፤ ሰውንም ሁሉ ወደ እርሱ ይጠራሉ፤ በዚህም ደስ ብሎኛል፤ ወደፊትም ደስ ይለኛል። ክርስቶስን ለማገልገል መኖር 19 እኔም ይህቺ ሥራ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ወደ ሕይወት እንደምታደርሰኝ አውቃለሁ። 20 በምንም እንደማላፍር ተስፋ እንደ አደረግሁና እንደታመንሁ እንደ ወትሮው በልብ ደስታ በግልጥነት፥ አሁንም የክርስቶስ ክብር በሕይወቴም ቢሆን፥ በሞቴም ቢሆን በሰውነቴ ይገለጣል። 21 እኔ በሕይወት ብኖርም ክርስቶስን ለማገልገል ነው፤ ብሞትም ዋጋ አለኝ። 22 ነገር ግን በሥጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆንም ምን እንደምመርጥ አላውቅም። 23 በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ እኔስ ከዚህ ዓለም ልለይ፥ በከክርስቶስም ዘንድ ልኖር እወዳለሁ፤ ይልቁንም ለእኔ ይህ ይሻለኛል፤ ይበልጥብኛልም። 24 ደግሞም ስለ እናንተ በሕይወተ ሥጋ ብኖር ይሻላል። 25 ይህንም ዐውቄ ለማደጋችሁና በሃይማኖትም ለምታገኙት ደስታ እንደምኖር አምናለሁ። 26 ዳግመኛ ወደ እናንተ በመምጣቴ በእኔ ምክንያት በኢየሱስ ክርስቶስ የምታገኙት ክብር ይበዛላችሁ ዘንድ። 27 ነገር ግን ምናልባት የመጣሁ እንደ ሆነ፥ ሳልኖርም ቢሆን በወንጌል ሃይማኖት እየተጋደላችሁ በአንድ መንፈስና በአንድ አካል ጸንታችሁ እንደምትኖሩ አይና እሰማ ዘንድ ሥራችሁ ለክርስቶስ ትምህርት እንደሚገባ ይሁን። 28 የእነርሱ ጥፋት፥ የእናንተም ሕይወት ይታወቅ ዘንድ የሚቃወሙን ሰዎች በማናቸውም አያስደንግጧችሁ። 29 ይህንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቶአችኋል፤ ነገር ግን ስለ እርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም። 30 እንዲሁም እኔን እንዳያችሁኝ፥ የእኔንም ነገር እንደ ሰማችሁ ምንጊዜም ተጋደሉ። |