ሐዋርያት ሥራ 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጴጥሮስን ስለ ተቃወሙት ባልንጀሮች 1 ሐዋርያትና በይሁዳ የነበሩ ወንድሞችም አሕዛብ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ። 2 ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከአይሁድ ወገን የሆኑት ወንድሞች ተቃወሙት። 3 “ወደ አልተገረዙት ሰዎች ቤት ገብተህ አብረሃቸው በልተሃል” አሉት። 4 ጴጥሮስም ከመጀመሪያ ጀምሮ ይነግራቸው ጀመረ፤ እንዲህም አላቸው። 5 “በኢዮጴ ከተማ ሳለሁ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝና ራእይ አየሁ፤ ታላቅ መጋረጃ የመሰለ ዕቃ በአራቱ ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደ፤ ወደ እኔም መጣ። 6 በውስጡም አራት እግር ያላቸው እንስሳንና አራዊትን፥ ተንቀሳቃሾችንም፥ የሰማይ ወፎችንም አየሁ። 7 ‘ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሥና አርደህ ብላ’ የሚለኝንም ቃል ሰማሁ። 8 ‘አቤቱ፥ ከቶ አይሆንም፤ ንጹሕ ያልሆነ ርኩስ ነገር ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም’ አልሁ። 9 ደግሞም፦ ‘እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ አታርክሰው’ የሚል ቃል ከሰማይ መለሰልኝ። 10 እንዲህም መላልሶ ሦስት ጊዜ ነገረኝ፤ ዳግመኛም ሁሉ ተጠቅልሎ ወደ ሰማይ ተመለሰ። 11 በዚያችም ሰዓት ከቂሳርያ ወደ እኔ የተላኩ ሦስት ሰዎች መጡ፤ እኔ ባለሁበት ግቢ በርም ቆሙ። 12 መንፈስ ቅዱስም፦ ‘ሳትጠራጠር አብረሃቸው ሂድ’ አለኝ፤ እነዚህ ስድስቱ ወንድሞቻችንም ተከትለውኝ መጡና ወደዚያ ሰው ቤት ገባን። 13 እርሱም በቤቱ ቆሞ ሳለ የእግዚአብሔርን መልአክ እንዳየ ‘ወደ ኢዮጴ ከተማ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን ይጥሩልህ። 14 አንተና ቤተ ሰቦችህ ሁሉ የምትድኑበትን ነገር እርሱ ይነግርሃል’ እንደ አለው ነገረን። 15 ላስተምራቸው በጀመርሁ ጊዜም ቀድሞ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱም ላይ ወረደ። 16 ‘ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን፤ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’ ያለውን የጌታችንን ቃል ዐሰብሁ። 17 እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለአመንነው ለእኛ እንደ ሰጠን፥ ያን ጸጋውን እንደ እኛ አስተካክሎ ከሰጣቸው እግዚአብሔርን ልከለክል የምችል እኔ ማነኝ?” 18 ይህንም በሰሙ ጊዜ ዝም አሉ፥ “እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሓን ሰጣቸው እንጃ” እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። በእስጢፋኖስ ሞት ስለ ተበተኑት ምእመናን 19 በእስጢፋኖስ ሞት ምክንያት የተበተኑት ግን፤ ወደ ፊንቄ ወደ ቆጵሮስና ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለአንድስ እንኳ አይናገሩም ነበር። 20 ከመካከላቸውም ወደ አንጾኪያ ሄደው ለአረማውያን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ነገር ያስተማሩ የቆጵሮስና የቄሬና ሰዎች ነበሩ። 21 የእግዚአብሔርም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ወደ ጌታም ተመልሰው ያመኑ ሰዎች ቍጥራቸው በዛ። 22 ስለ እነርሱ የተነገረውም ይህ ነገር በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተሰማ፤ በርናባስንም ወደ አንጾኪያ ላኩት። 23 በደረሰ ጊዜም የእግዚአብሔርን ጸጋ አየና ደስ አለው፤ በፍጹም ልባቸውም በእግዚአብሔር ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው። 24 ደግ ሰው፥ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት፥ ሃይማኖተኛም ነበርና፤ በጌታችንም አምነው ብዙዎች አሕዛብ ተጨመሩ። ደቀ መዛሙርት ክርስቲያን ስለ መባላቸው 25 ከዚህም በኋላ በርናባስ ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ ሄደ፤ በአገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ ወሰደው። 26 በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት አብረው ተቀመጡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተብለው ተጠሩ። 27 ያንጊዜም ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ። 28 ከመካከላቸውም አጋቦስ የተባለ አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ጽኑ ረኃብ እንደሚመጣ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ተናገረ፤ ይህም በቄሣር ቀላውዴዎስ ዘመን ሆነ። 29 ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርት እያንዳንዳቸው የሚችሉትን ያህል አወጣጥተው በይሁዳ ሀገር ለሚኖሩት ወንድሞቻቸው ርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ። 30 እንደዚህም አድርገው በበርናባስና በሳውል እጅ ወደ ቀሳውስት ላኩት። |