ሐዋርያት ሥራ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሳውል እንደ ተጠራ 1 ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ። 2 ምንአልባት በመንገድ የሚያገኘው ሰው ቢኖር ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች የሥልጣን ደብዳቤ ከሊቀ ካህናቱ ለመነ። 3 ሲሄድም ወደ ደማስቆ ከተማ አቅራቢያ በደረሰ ጊዜ መብረቅ ድንገት ከሰማይ ብልጭ አለበት። 4 በምድር ላይም ወደቀ፤ ወዲያውም፥ “ሳውል፥ ሳውል፥ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚለውን ቃል ሰማ። 5 ሳውልም፥ “አቤቱ፥ አንተ ማነህ?” አለው፤ እርሱም፥ “አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ በሾለ ብረት ላይ ብትቆም ለአንተ ይብስሃል” አለው። 6 እርሱም እየፈራና እየተንቀጠቀጠ፥ “አቤቱ፥ ምን እንዳደርግ ትሻለህ?” አለው፤ ጌታም፥ “ተነሣና ወደ ከተማ ግባ፤ በዚያም ልታደርገው የሚገባህን ይነግሩሃል” አለው። 7 ከእርሱም ጋር የነበሩት ሰዎች ድምፅ እየሰሙ ማንንም ሳያዩ ተደንቀው ቆሙ። 8 ሳውልም ከምድር ተነሣ፤ ነገር ግን ዐይኖቹ ተገልጠው ሳሉ የሚያየው ነገር አልነበረም፤ እየመሩም ወደ ደማስቆ አገቡት። 9 በዚያም ሳያይ ሳይበላና ሳይጠጣ ሦስት ቀን ቈየ። 10 በደማስቆም ስሙን ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታም በራእይ ተገልጦ፥ “ሐናንያ” ብሎ ጠራው፤ እርሱም፥ “አቤቱ፥ እነሆኝ” አለ። 11 ጌታም፥ “ተነሣና ቅን በምትባለው መንገድ ሂድ፤ በይሁዳ ቤትም ከጠርሴስ ሀገር የመጣ ሳውል የሚባል ሰው ፈልግ፤ እርሱ አሁን ይጸልያልና” አለው። 12 ሳውልም በራእይ ሐናንያ የሚባል ሰው ወደ እርሱ ገብቶ ያይ ዘንድ እጁን ሲጭንበት አየ። 13 ሐናንያ ግን መልሶ እንዲህ አለ፥ “አቤቱ፥ ስለዚህ ሰው በኢየሩሳሌም በቅዱሳኖችህ ላይ የሚያደርገውን ክፉ ነገር ሁሉ ከብዙ ሰዎች ሰምቻለሁ። 14 ወደዚህም ከካህናቱ አለቃ አስፈቅዶ የመጣ ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ሊያስር ነው።” 15 ጌታችንም እንዲህ አለው፥ “ተነሥና ሂድ፤ በአሕዛብና በነገሥታት፥ በእስራኤል ልጆችም ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ አድርጌዋለሁና። 16 እኔም ስለ ስሜ መከራን ይቀበል ዘንድ እንዳለው አሳየዋለሁ።” 17 ያንጊዜም ሐናንያ ሄደ፤ ወደ ቤትም ገባ፤ እጁንም ጫነበትና፥ “ወንድሜ ሳውል፥ በመንገድ ስትመጣ የታየህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታይና መንፈስ ቅዱስ ይመላብህ ዘንድ ወደ አንተ ልኮኛል” አለው። 18 ያንጊዜም ፈጥኖ እንደ ቅርፊት ያለ ነገር ከዐይኖቹ ላይ ተገፎ ወደቀ፤ ዐይኖቹም ተገለጡ፤ ወዲያውም አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ። 19 እህልም በላ፤ በረታም፤ ጥቂት ቀንም ከደቀ መዛሙርት ጋር በደማስቆ ሰነበተ። 20 ወዲያውኑም “የእግዚአብሔር ልጅ ነው” ብሎ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በየምኵራቦቹ ሰበከ፥ አስተማረም። 21 የሰሙትም ሁሉ አደነቁ፤ እንዲህም አሉ፥ “በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሁሉ ይጠላቸው የነበረው ይህ አይደለምን? ስለዚህ ወደዚህ የመጣው እያሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሊወስዳቸው አይደለምን?” 22 ሳውል ግን እየበረታ ሔደ፤ በደማስቆም ለነበሩት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደ ሆነ እያስረዳ መልስ አሳጣቸው። 23 ከብዙ ቀንም በኋላ አይሁድ ሳውልን ይገድሉት ዘንድ ተማከሩ። 24 ሳውል ግን በእርሱ ላይ ሊያደርጉት የሚሹትን ዐወቀባቸው፤ ሊገድሉትም በቀንና በሌሊት የከተማውን በር ይጠብቁ ነበር። 25 ደቀ መዛሙርትም በሌሊት ወሰዱት፤ በቅርጫትም አድርገው በቅጽሩ ድምድማት ላይ አወረዱት። 26 ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ሊገናኛቸው ደቀ መዛሙርትን ፈለጋቸው። ሁሉም ፈሩት፤ የጌታችን ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ አላመኑትም ነበርና። 27 በርናባስም አግኝቶ ወደ ሐዋርያት ወሰደው፤ ጌታችንም በመንገድ እንደ ተገለጠለትና እንደ አነጋገረው፥ በደማስቆም በኢየሱስ ስም እንደ አስተማረ ነገራቸው። 28 በኢየሩሳሌምም አብሮአቸው ይገባና ይወጣ ነበረ፤ በጌታችን በኢየሱስ ስምም በግልጥ ያስተምር ነበር። 29 ከግሪክ ሀገር መጥተው የነበሩትንም አይሁድ ይከራከራቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ ሊገድሉት ፈለጉ። 30 ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ ወደ ቂሳርያ አወረዱት፤ ከዚያም ወደ ጠርሴስ ላኩት። 31 በይሁዳ፥ በሰማርያና በገሊላ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በሰላም ኖሩ፤ ታነጹም፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ጸንተው ኖሩ፤ ሕዝቡም በመንፈስ ቅዱስ አጽናኝነት በዙ። ቅዱስ ጴጥሮስ ኤንያን እንደ ፈወሰ 32 ከዚህም በኋላ ጴጥሮስ በየቦታዉ ሲዘዋወር በልዳ ወደሚኖሩት ቅዱሳን ዘንድ ደረሰ። 33 በዚያም ኤንያ የተሰኘ ሰውን አገኘ፤ እርሱም ታሞ በአልጋ ከተኛ ስምንት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ ሽባ ነበርና። 34 ጴጥሮስም፥ “ኤንያ ሆይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስህ፤ ተነሥና አልጋህን አንጥፍ” አለው፤ ያንጊዜም ተነሣ። 35 በልዳና በሳሮና የሚኖሩም ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታችን ተመለሱ። ስለ ጣቢታ 36 በኢዮጴ ሀገርም ጣቢታ የምትባል አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፤ በትርጓሜውም ዶርቃስ ይሉአታል፤ ፌቆ ማለት ነው፤ እርስዋም ብዙ ደጋግ ሥራ ትሠራ ነበር፤ ምጽዋትም ትሰጥ ነበር። 37 ያንጊዜም ታማ ሞተችና በድንዋን አጥበው በሰገነት አስተኙአት። 38 ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ነበርና ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው ወደ እነርሱ መምጣት እንዳይዘገይ ይማልዱት ዘንድ ሁለት ሰዎችን ወደ እርሱ ላኩ። 39 ጴጥሮስም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በደረሰም ጊዜ ወደ ሰገነት አወጡት፤ ባልቴቶችም ሁሉ ወደ እርሱ መጥተው በፊቱ ቆሙ፤ ያለቅሱላትም ነበር፤ ዶርቃስም በሕይወት ሳለች የሠራችውን ቀሚሱንና መጐናጸፊያውን አሳዩት። 40 ጴጥሮስም ሁሉን ካስወጣ በኋላ ተንበርክኮ ጸለየ፤ ወደ በድንዋም መለስ ብሎ፥ “ጣቢታ ሆይ፥ ተነሽ” አላት፤ እርስዋም ዐይኖችዋን ገለጠች፤ ያንጊዜም ጴጥሮስን አየችው፤ ቀና ብላም ተቀመጠች። 41 እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና ባልቴቶችንም ጠርቶ እርስዋን አድኖ ሰጣቸው። 42 በኢዮጴም ያሉ ሁሉ ይህን ሰሙ፤ ብዙዎችም በጌታችን አመኑ። 43 ጴጥሮስም በኢዮጴ በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት ብዙ ቀን ተቀመጠ። |