ሮሜ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኦሪት ሕግ ሰውን ማዳን እንደ ተሳነው 1 እንግዲህ በኢየሱስ ክርስቶስ ላሉት በመንፈስ እንጂ በሥጋ ለማይመላለሱ ፍርድ የለባቸውም። 2 በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠን ሕይወት የሚገኝበት የመንፈስ ሕግ እርሱ ከኀጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቶናልና። 3 ስለ ሥጋ ደካማነት የኦሪት ሕግ ከሞት ማዳን በተሳነው ጊዜ እግዚአብሔር በኀጢኣተና ሥጋ ምሳሌ ልጁን ላከ፤ ያችንም ኀጢአት በሥጋው ቀጣት። 4 እናን ያጸድቀን ዘንድ፥ የኦሪትንም ሕግ ሠርቶ እንደ ፈጸመ ሰው ያደርገን ዘንድ፤ ይህም በመንፈሳዊ ሕግ ጸንተው ለሚኖሩ ነው እንጂ በሥጋ ሕግ ለሚሠሩ አይደለም። 5 እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። 6 የሥጋ ዐሳብ ሞትን ያመጣብናል፤ የመንፈስ ዐሳብ ግን ሰላምንና ሕይወትን ይሰጠናል። 7 የሥጋ ዐሳብ ለእግዚአብሔር ጠላቱ ነውና፤ ለእግዚአብሔርም ሕግ ስለማይገዛ፥ መፈጸም አይቻለውም። 8 ለሥጋዊ ፈቃዳቸው የሚሠሩ ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም። 9 እናንተ ግን ለመንፈሳዊ ሕግ እንጂ ለሥጋችሁ ፈቃድ የምትሠሩ አይደላችሁም፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ አድሮ ይኖራልና፤ የክርስቶስ መንፈስ ያላደረበት ግን እርሱ የእርሱ ወገን አይደለም። 10 ክርስቶስ ካደረባችሁ ግን ሰውነታችሁን ከኀጢአት ሥራ ለዩ፤ መንፈሳችሁንም ለጽድቅ ሥራ ሕያው አድርጉ። 11 ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ለይቶ ያስነሣው የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረባችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ለይቶ ያስነሣው እርሱ አድሮባችሁ ባለ መንፈሱ ለሟች ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣታል። ሥጋዊ ሥራን ማዘውተር የማይገባ ስለ መሆኑ 12 ወንድሞቻችን፥ አሁንም በሥጋችን ሳለን በሥጋ ፈቃድ እንኖር ዘንድ አይገባም። 13 እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሥራ የሥጋችሁን ፈቃድ ብትገድሉ ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራላችሁ። 14 በእግዚአብሔር መንፈስ የሚሠሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። 15 ዳግመናም አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደ ገና ለፍርሀት የባርነት መንፈስን አልተቀበላችሁምና። 16 እና የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆን ለልቡናችን ምስክሩ እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። 17 እና የእግዚአብሔር ልጆች ከሆን ወራሾቹ ነን፤ የእግዚአብሔር ወራሾች ከሆንም የክርስቶስ ወራሾቹ ነን፤ በመከራ ከመሰልነውም በክብር እንመስለዋለን። ስለ መንግሥተ ሰማያት 18 ነገር ግን የዚህ ዓለም መከራ ለእና ሊገለጥ ከአለው ክብር ጋር እንደማይተካከል ዐስቡ። 19 የዓለም ተስፋው የእግዚአብሔርን ልጅ መምጣት ይጠባበቅ ነበርና። 20 ዓለም ባለማወቅ ለከንቱ ነገር ተገዝቶአልና በተስፋ ስለ አስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም። 21 ነገር ግን አስቶ በባርነት ከሚገዛው ከዚህ ወጥቶ የእግዚአብሔር ልጆች ወደ አገኙአት የነጻነት ክብር ይገባ ዘንድ ተስፋ አለው። 22 እስካሁን ዓለም ሁሉ ያዘነና የተከዘ እንደ ሆነ እናውቃለን። 23 ነገር ግን የሚተክዝ ዓለም ብቻ አይደለም፤ የመንፈስ ቅዱስን ፈለማ የተቀበልነው እናም ደግሞ እናዝናለን እንጂ፤ የነፍሳችንን ድኅነት እናገኝ ዘንድ የልጅነትን ክብር ተስፋ እናደርጋለንና፤ በእምነትም ድነናልና። 24 የሚታየውን ተስፋ ማድረግ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ እንዴት ተስፋ ያደርጋል? እንዴትስ ይጠብቃል? 25 የማይታየውን ተስፋ ብናደርግ ግን እርሱን ተስፋ አድርገን በእርሱ እንደ ጸናን መጠን ትዕግሥታችን ይታወቃል። 26 መንፈስ ቅዱስም ከድካማችን ይረዳናል፤ እንግዲያስ ተስፋችንን ካላወቅን ጸሎታችን ምንድነው? ነገር ግን እርሱ ራሱ መንፈስ ቅዱስ ስለ መከራችንና ስለ ችግራችን ይፈርድልናል። 27 እርሱም ልባችንን ይመረምራል፤ ልብ የሚያስበውንም እርሱ ያውቃል፤ ስለ ቅዱሳንም በእግዚአብሔር ዘንድ ይፈርዳል። 28 እግዚአብሔር የሚወዱትን ምርጦቹን በበጎ ምግባር ሁሉ እንደሚረዳቸው እናውቃለን። 29 ልጁ በብዙዎች ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸውንና የመረጣቸውን እነርሱን ልጁን ይመስሉ ዘንድ አዘጋጅቶአቸዋል። 30 ያዘጋጃቸውን እነርሱን ጠራ፤ የጠራቸውንም እነርሱን አጸደቀ፤ የአጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ። 31 እንግዲህ ስለዚህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእና ጋር ከሆነ ማን ይችለናል? 32 ለልጁ ስንኳ አልራራም፤ ስለ ሁላችን ቤዛ አድርጎ አሳልፎ ሰጠው እንጂ፥ እንግዲህ እርሱ ሁሉን እንዴት አይሰጠንም? 33 እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማነው? 34 የሚፈርድስ ማነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን ተለይቶ የተነሣው፥ በእግዚአብሔርም ቀኝ የተቀመጠው፥ ደግሞ ስለ እና የሚፈርደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 35 ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ራብ ነውን? መራቆት ነውን? ጭንቀት ነውን? ሾተል ነውን? 36 መጽሐፍ እንዳለ፥ “ስለ አንተ ዘወትር ይገድሉናል፤ እንደሚታረዱ በጎችም ሆነናል።” 37 ነገር ግን በወደደን በእርሱ ሁሉን ድል እንነሣለን። 38 ነገር ግን ሞትም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ አለቆችም ቢሆኑ፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንደማይችል አምናለሁ። 39 ኀይልም ቢሆን፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ሌላ ፍጥረትም ቢሆን ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል የለም። |