ዮሐንስ 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በሃይማኖት ስለ መጽናት 1 “እንዳትሰናከሉ ይህን ነገርኋችሁ። 2 ከምኵራባቸው ያስወጡአችኋል፤ ደግሞም እናንተን የሚገድላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሚያቀርብ የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። 3 ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንም፥ እኔንም ስላላወቁ ነው። 4 ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ነገርኋችሁ። አስቀድሜ ግን ይህን አልነገርክኋችሁም ነበር፤ ከእናንተ ጋር ነበርሁና። 5 አሁን ግን ወደ ላከኝ ወደ አብ እሄዳለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እንኳ፦ ‘ወዴት ትሄዳለህ?’ ብሎ አይጠይቀኝም። 6 ነገር ግን ይህን ስለ ነገርኋችሁ በልባችሁ ኀዘን ሞላ። መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ተስፋ ስለመስጠቱ 7 “እኔ በእውነት የሚሆነውን እነግራችኋለሁ፤ እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፤ እኔ ካልሄድሁ ጰራቅሊጦስ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ከሄድሁ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። 8 እርሱም በመጣ ጊዜ ዓለምን ስለ ኀጢአትና ስለ ጽድቅ፥ ስለ ፍርድም ይዘልፈዋል። 9 ስለ ኀጢኣት፥ በእኔ አላመኑምና ነው፤ 10 ስለ ጽድቅ፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፥ እንግዲህ ወዲህም አታዩኝምና ነው። 11 ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዢ ይፈረድበታልና ነው። 12 “የምነግራችሁ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። 13 ያ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ግን ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ እርሱ ከራሱ አይናገርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። 14 እርሱም እኔን ያከብረኛል፤ ከእኔ ወስዶ ይነግራችኋልና። 15 ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህም ከእኔ ወስዶ ይነግራችኋል አልኋችሁ። 16 “ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ፤ ወደ አብ እሄዳለሁና።” 17 ደቀ መዛሙርቱም እርስ በርሳቸው፥ “ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ፥ ወደ አብ እሄዳለሁና የሚለን ይህ ነገር ምንድነው?” ተባባሉ። 18 “ይህ ጥቂት የሚለን ምንድነው? የሚናገረውን አናውቅም” አሉ። 19 ጌታችን ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደሚሹ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፥ “ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ” ስለ አልኋችሁ፥ ስለዚህ ነገር እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን? ስለ ኀዘንና ስለ ደስታ 20 “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝኑማላችሁ፤ ዓለምም ደስ ይለዋል፤ እናንተ ግን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። 21 ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራቷ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ልጅዋን ከወለደች በኋላ ስለ ደስታዋ ከዚያ ወዲያ ምጥዋን አታስበውም፤ በዓለም ወንድ ልጅን ወልዳለችና። 22 እናንተም ዛሬ ታዝናላችሁ፤ እንደገናም አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። 23 ያንጊዜም እኔን የምትለምኑኝ አንዳች የለም፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በስሜ አብን ብትለምኑት ሁሉን ይሰጣችኋል። 24 እስካሁን ምንም በስሜ አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም ይሆን ዘንድ ለምኑ፤ ታገኙማላችሁ። ዓለምን ድል ስለ መንሣት 25 “ዛሬስ በምሳሌ ነገርኋችሁ፤ ነገር ግን የአብን ነገር ገልጬ እነግራችኋለሁ እንጂ ለእናንተ በምሳሌ የማልናገርበት ጊዜ ይመጣል። 26 ያንጊዜ በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እለምነዋለህ አልላችሁም፤ 27 እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ፤ ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣሁ ስለ አመናችሁብኝ እርሱ ራሱ አብ ወድዷችኋልና። 28 ከአብ ወጣሁ፤ ወደ ዓለምም መጣሁ፤ ዳግመኛም ዓለምን እተወዋለሁ፤ ወደ አብም እሄዳለሁ።” 29 ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉት፥ “እነሆ፥ ዛሬ ገልጠህ ትናገራለህ፤ ምንም በምሳሌ የተናገርኸው የለም። 30 አሁን አንተ ሁሉን እንደምታውቅ፥ ማንም ሊነግርህ እንደማትሻ ዐወቅን፤ በዚህም ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን።” 31 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “አሁን ታምናላችሁን? 32 እያንዳንዳችሁ በየቦታዉ የምትበታተኑበት፥ እኔንም ብቻዬን የምትተዉበት ጊዜ ይደርሳል፤ ደርሶአልም፤ እኔ ግን ብቻዬን አይደለሁም፤ አብ ከእኔ ጋር ነውና። 33 በእኔም ሰላምን እንድታገኙ ይህን ነገርኋችሁ፤ በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ፤ እኔ ዓለሙን ድል ነሥቼዋለሁና።” |