ሐዋርያት ሥራ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ሰብዐቱ ዲያቆናት መሾም 1 በዚያም ወራት ደቀ መዛሙርት በበዙ ጊዜ ከግሪክ የመጡ ደቀ መዛሙርት በአይሁድ ምእመናን ላይ አንጐራጐሩባቸው፤ የዕለት የዕለቱን ምግብ ሲያካፍሉ ባልቴቶቻቸውን ቸል ይሉባቸው ነበርና። 2 ዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ሕዝቡን ሁሉ ጠርተው እንዲህ አሉአቸው፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ አይደለም። 3 ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከእናንተ ወገን በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎችን ምረጡ፤ ለዚህ ሥራም እንሾማቸዋለን። 4 እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማስተማር እንተጋለን።” 5 ይህም ነገር በእነርሱ ዘንድ የተወደደ ሆነ፤ ሃይማኖቱ የቀናና መንፈስ ቅዱስ ያደረበትን ሰው እስጢፋኖስን፥ ፊልጶስን፥ ጵሮኮሮስን፥ ኒቃሮናን፥ ጢሞናን፥ ጰርሜናን፥ ወደ ይሁዲነት የተመለሰውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ። 6 በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፤ ጸልየውም እጃቸውን በራሳቸው ላይ ጫኑ። 7 የእግዚአብሔርም ቃል ከፍ ከፍ አለ፤ በኢየሩሳሌምም ምእመናን እጅግ በዙ፤ ከካህናትም መካከል ያመኑ ብዙዎች ነበሩ። አይሁድ እስጢፋኖስን እንደ ተቃወሙት 8 እስጢፋኖስም የእግዚአብሔር ጸጋና ኀይል የመላበት ሰው ነበር፤ በሕዝቡም መካከል ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን ይሠራ ነበር። 9 የነጻ ወጭዎች ከምትባለው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያ፥ ከቂልቅያና ከእስያ የሆኑ ሰዎችም ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር። 10 ነገር ግን ይቃወሙት ዘንድ አልቻሉም፤ በጥበብና በመንፈስ ቅዱስ ይከራከራቸው ነበርና። 11 ከዚህም በኋላ “ይህን ሰው በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አስነሡበት፤ 12 ሕዝቡን፥ ሽማግሌዎችንና ጸሓፊዎችንም አነሳሡአቸው፤ ከበውም እየጐተቱ ወደ ሸንጎ አቀረቡት። 13 የሐሰት ምስክሮችንም አቆሙበት፤ እነርሱም እንዲህ አሉ፥ “ይህ ሰው በዚህ ቤተ መቅደስ ላይና በኦሪት ላይ የስድብ ቃል እየተናገረ ዝም በል ቢሉት እንቢ አለ፤ 14 የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ቤተ መቅደስ ያፈርሰዋል፤ ሙሴም የሰጠንን ኦሪታችንን ይሽራል ሲል ሰምተነዋል።” 15 በሸንጎም ተቀምጠው የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ተመለከቱት፤ ፊቱንም እንደ እግዚአብሔር መልአክ ፊት ሆኖ አዩት። |