ኢያሱ 3:16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ውሃው መውረዱን አቆመ፤ በጻርታን አጠገብ አዳም ተብላ እስከምትጠራው ከተማ ድረስ ተከመረ፤ ወደ ሙት ባሕር ይፈስ የነበረውም ጐርፍ በፍጹም ተቋረጠ፤ ስለዚህም ሕዝቡ ወደ ማዶ ወደ ኢያሪኮ ተሻገሩ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከላይ የሚወርደው ውሃ ቆመ፤ በጻርታን አጠገብ “አዳም” ተብላ እስከምትጠራው ሩቅ ከተማ ድረስ በመከማቸት እንደ ክምር ተቈለለ፤ ቍልቍል ወደ ዓረባ ጨው ባሕር የሚወርደውም ውሃ ፈጽሞ ተቋረጠ፤ ሕዝቡም ከኢያሪኮ ትይዩ ባለው አቅጣጫ ተሻገሩ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፤ በጻርታን አጠገብ ባለችው አዳም በምትባል ከተማ በሩቅ ቆሞ በአንድ ክምር ተነሣ፤ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃ ፈጽሞ ተቋረጠ፤ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ተሻገሩ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፤ እስከ ቀርያትያርም አውራጃ እጅግ ርቆ እንደ ግድግዳ ቆመ፤ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃም ፈጽሞ ደረቀ፤ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ቆሙ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፥ በጻርታን አጠገብ ባለችው አዳም በምትባል ከተማ በሩቅ ቆሞ በአንድ ክምር ተነሣ፥ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃ ፈጽሞ ተቋረጠ፥ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ተሻገሩ። |
በዓና የተባለው የአሒሉድ ልጅ፦ የታዕናክና የመጊዶ ከተሞች፥ እንዲሁም በቤትሻን አጠገብ ያለው ግዛት በሙሉ፥ በጻርታን ከተማ አጠገብ ያለው ግዛትና በኢይዝራኤል ከተማ በስተደቡብ ያለው ግዛት፥ እንዲሁም አቤልመሖላና ዮቅመዓም ተብለው እስከሚጠሩት ከተሞች ድረስ ያለው ግዛት ሁሉ አስተዳዳሪ፤
ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በብርቱ የምሥራቅ ነፋስ ባሕሩን ወደ ኋላ መለሰው፤ ነፋሱም ሌሊቱን ሙሉ በመንፈሱ፥ ባሕሩን ወደ ደረቅ ምድር ለወጠው፤ ውሃውም ከሁለት ተከፈለ፤
“እኔ በመጣሁ ጊዜ ማንም ሰው አለመኖሩ ለምንድን ነው? በጠራሁም ጊዜ ማንም ሰው መልስ ያልሰጠኝ ለምንድን ነው? እኔ ለመታደግ አልችልምን? ለማዳንስ ኀይል የለኝምን? በተግሣጼ ብቻ ባሕርን አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ወደ ምድረ በዳነት እለውጣለሁ፤ ዓሣዎቻቸውም ውሃ ከማጣት የተነሣ ሞተው ይበሰብሳሉ።
እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ ውሃ በምድሪቱ ውስጥ ወደ ምሥራቅ፥ ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆና ወደ ሙት ባሕር ይፈስሳል፤ ወደ ሙት ባሕር በሚፈስበት ጊዜ የጨዉ ባሕር ታድሶ ጥሩ ውሃ ይሆናል።
እግዚአብሔር ሆይ! ፈረሶችህንና ሠረገላዎችህን ወደ ድል በመራኸቸው ጊዜ፥ ኀይለኛው ቊጣህ በወንዞች ላይ ነበርን? ወይስ በባሕሩ ላይ ተቈጥተህ ነበርን?
የደቡብ ድንበር ከጺን ምድረ በዳ ተነሥቶ የኤዶምን ጠረፍ እያዋሰነ ያልፋል፤ ይኸውም በስተ ምሥራቅ በኩል የሚጀምረው ከሙት ባሕር በስተ ደቡብ ጫፍ ላይ ነው።
ከዮርዳኖስ ማዶ አራባ በሚባል ምድረ በዳ በሱፍ ፊት ለፊት በአንድ በኩል ፋራን፥ በሌላ በኩል ጦፌል፥ ላባን፥ ሐጼሮትና ዲዛሃብ መካከል ሳሉ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገው ንግግር ይህ ነው።
በስተ ምዕራብ በኩል ያለው ግዛታቸው አራባን ዮርዳኖስንና በአካባቢው ያለውን ምድር ያጠቃልላል፤ በስተምሥራቅ በኩል ከገሊላ ባሕር በፒስጋ ተራራ ግርጌ እስካለው እስከ ጨው ባሕር ድረስ ይደርሳል።
እርሱም በምሥራቅ በኩል ከዮርዳኖስ ሸለቆ የገሊላ ባሕር ድረስ፥ በቤት የሺሞት አቅጣጫ እስከ ጨው ባሕር ድረስ፥ ከጨው ባሕር ወደ ደቡብ እስከ ፒስጋ ተራራ ታች ድረስ ያለውን ያጠቃልላል።
የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮች ውሃውን በሚነኩበት ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ መውረዱን ያቆማል፤ ከላይ እየጐረፈ የሚመጣውም ውሃ በአንድ ቦታ ተሰብስቦ ይቈለላል።”
ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ ያሉ የአሞራውያን ነገሥታትና በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ ጠረፉን ተከትለው የሚኖሩ የከነዓናውያን ነገሥታት ሁሉ የእስራኤል ሕዝብ እስኪሻገሩ ድረስ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ወንዝ ውሃ እንዳደረቀላቸው በሰሙ ጊዜ፤ በፍርሃት ልባቸው ቀለጠ፤ ከዚያም በኋላ እስራኤላውያንን ለመቋቋም ድፍረት አጡ።
ሦስት መቶው የጌዴዎን ሰዎች እምቢልታቸውን በሚነፉበት ጊዜ እግዚአብሔር እያንዳንዱን የጠላት ወታደር በጓደኛው ላይና በሠራዊቱ ላይ ሰይፉን እንዲያነሣ አደረገ፤ ሠራዊቱም ፊታቸውን ወደ ጽሬራ በመመለስ እስከ ቤትሺጣ፥ ከዚያም አልፎ በጣባት አጠገብ እስካለው አቤልመሖላ ድረስ ሸሽተው ሄዱ።