ኢያሱ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ ያሉ የአሞራውያን ነገሥታትና በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ ጠረፉን ተከትለው የሚኖሩ የከነዓናውያን ነገሥታት ሁሉ የእስራኤል ሕዝብ እስኪሻገሩ ድረስ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ወንዝ ውሃ እንዳደረቀላቸው በሰሙ ጊዜ፤ በፍርሃት ልባቸው ቀለጠ፤ ከዚያም በኋላ እስራኤላውያንን ለመቋቋም ድፍረት አጡ። በጌልገላ የተደረገ ግዝረት 2 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ኢያሱን “ከባልጩት የተሠራ መቊረጫ አዘጋጅተህ እስራኤላውያንን እንደገና ግረዛቸው” አለው። 3 ኢያሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው በማድረግ “የግዝረት ኮረብታ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ እስራኤላውያንን ገረዘ። 4 ኢያሱ እነርሱን የገረዘበት ምክንያት ከግብጽ ምድር የወጡት ለወታደርነት ብቃት የነበራቸው ወንዶች ሁሉ በበረሓው ጒዞ ጊዜ ሞተው ስለ ነበረ ነው። 5 በመጀመሪያ ከግብጽ ምድር የወጡት ወንዶች ሁሉ ተገርዘው የነበሩ ቢሆኑም እንኳ በበረሓው ጒዞ ጊዜ የተወለዱት ወንዶች አልተገረዙም ነበር። 6 ከግብጽ ምድር የወጡት ለወታደርነት ብቃት የነበራቸው ወንዶች የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማታቸው ሁሉም እስኪያልቁ ድረስ እስራኤላውያን በበረሓ ለአርባ ዓመት ተጓዙ። ለልጅ ልጆቻቸው ሊሰጥ ለቀድሞ አባቶቻቸው ቃል ገብቶ የነበረውን በማርና በወተት የበለጸገውን ምድር በምድረ በዳ ያለቁት ልጆቻቸው እንደማያዩት አረጋግጦ ነበር። 7 ኢያሱ የገረዛቸው እግዚአብሔር በእነርሱ ቦታ ያስነሣቸውን ልጆቻቸውን ነው፤ እነርሱ በጉዞ ላይ በነበሩ ጊዜ ስላልተገረዙ ሸለፈታሞች ነበሩ። 8 ሰዎች ሁሉ ከተገረዙ በኋላ ቊስላቸው እስኪድን ድረስ በሰፈር ቈዩ። 9 እግዚአብሔር ኢያሱን፦ “እነሆ፥ ዛሬ እኔ ከእናንተ ላይ የግብጽን ነውር አስወግጄላችኋለሁ” አለው። ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ጌልጌላ ተብሎ ይጠራል። 10 እስራኤላውያን ከኢያሪኮ አጠገብ ባለው ሜዳ በጌልገላ ሰፍረው ሳሉ፥ ከወሩ በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ 11 በከነዓን የበቀለውን እህል መብላት የጀመሩትም በዚያን ቀን ማግስት ነበር፤ የተመገቡትም የተጠበሰ እሸትና ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ነበር። 12 ከምድሪቱ የሚገኘውን ምግብ መብላት ከጀመሩበት ቀን አንሥቶ መና መዝነቡን አቋረጠ፤ እስራኤላውያንም ከዚያን በኋላ ያን መና ማግኘት አልቻሉም፤ ከዚያን ጊዜ አንሥቶ በከነዓን የበቀለውን እህል መብላት ጀመሩ። ኢያሱና ሰይፍ የያዘው ጐልማሳ 13 ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ሰይፍ የያዘ አንድ ጐልማሳ በድንገት በፊቱ ቆሞ ታየው፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ “አንተ የእኛ ወገን ነህ ወይስ የጠላቶቻችን?” አለው። 14 ጐልማሳውም “የእናንተም ሆነ የጠላት ወገን አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሠራዊት አዛዥ እንደ መሆኔ መጠን እነሆ፥ መጥቻለሁ” አለ። ኢያሱም ወደ መሬት ወድቆ ሰገደለትና “ጌታዬ ሆይ፥ እኔ አገልጋይህ ምን ልታዘዝ?” አለው። 15 የእግዚአብሔር ሠራዊት አዛዥም “የቆምክባት ምድር የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማህን አውልቅ” አለው፤ ኢያሱም እርሱ እንዳዘዘው አደረገ። |