መዝሙር 33 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየምስጋና መዝሙር 1 ጻድቃን ሆይ! በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ቅኖች ሊያመሰግኑት ይገባል። 2 እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፤ ዐሥር አውታር ባለውም በገና ዘምሩለት። 3 አዲስ መዝሙር ዘምሩለት! ባማረ ስልት በገና ደርድሩ፤ በደስታም “እልል” በሉ። 4 የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው፤ ሥራውም ሁሉ የታመነ ነው። 5 እግዚአብሔር ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል፤ ዘለዓለማዊ ፍቅሩም ምድርን ይሞላል። 6 እግዚአብሔር ሰማያትን በቃሉ፥ በሰማይ የሚገኙትን ፍጥረቶች በትእዛዙ ፈጠረ። 7 ባሕርን ሁሉ በአንድ ቦታ ሰበሰበ፤ ጥልቅ ለሆኑት ውቅያኖሶችም መከማቻ ስፍራ አዘጋጀላቸው። 8 በምድርም የምትኖሩ ሁሉ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔርን አክብሩ። 9 እርሱ በተናገረ ጊዜ ዓለም ተፈጠረ፤ በትእዛዙም ሁሉ ነገር ጸንቶ ቆመ። 10 እግዚአብሔር የአሕዛብን ዕቅድ እንዳይሳካ ያደርጋል፤ የሕዝቦችንም ዓላማ ዋጋቢስ ያደርጋል። 11 የእግዚአብሔር ዕቅድ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዓላማውም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። 12 እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለትና እግዚአብሔር የራሱ አድርጎ የመረጠው ሕዝብ የተባረከ ነው! 13 እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ይመለከታል፤ የሰውንም ዘር ሁሉ ያያል፤ 14 በዙፋኑ ላይ ሆኖ በምድር ላይ ያሉትን ሁሉ ያያል። 15 የሁላቸውንም ልብ የሠራ እርሱ ነው የሚያደርጉትን ሁሉ ይመለከታል። 16 ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፤ አርበኛም በከፍተኛ ኀይሉ አያመልጥም። 17 ፈረስ ለማዳን ከንቱ ተስፋ ነው፤ ከዚያ ሁሉ ኀይሉ ጋር ሊያድን አይችልም። 18 እግዚአብሔር የሚፈሩትንና ዘለዓለማዊ ፍቅሩ ተስፋቸው የሆነውን ይመለከታል። 19 ይህም የሚሆነው ከሞት ሊያድናቸውና ከራብም ሊጠብቃቸው ነው። 20 እግዚአብሔርን በተስፋ እንጠብቀዋለን ረዳታችንና ጋሻችን እርሱ ነው። 21 በቅዱስ ስሙም ስለምንታመን በእርሱ ደስ ይለናል። 22 እግዚአብሔር ሆይ! ተስፋችንን በአንተ እንዳደረግን ዘላቂ ፍቅርህ በእኛ ላይ ይሁን። |