Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢያሱ 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ለኤፍሬምና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት ሆኖ የተመደበላቸው ምድር

1 ለዮሴፍ ዘሮች የተመደበው የምድሪቱ ደቡባዊ ክፍል በኢያሪኮ አጠገብ ከዮርዳኖስ ወንዝ ይጀምራል፤ ይኸውም ከኢያሪኮ ምንጮች ምሥራቃዊ ጫፍ በመነሣት ወደ በረሓው ይዘልቃል፤ ከኢያሪኮም ተነሥቶ ወደ ኮረብታማው አገር በመውጣት እስከ ቤትኤል ይደርሳል።

2 ከቤትኤልም ተነሥቶ አርካውያን የሚኖሩበትን ዐጣሮትአዳርን በማለፍ ወደ ሎዛ ይዘልቃል።

3 ከዚያም በምዕራብ በኩል ወደሚገኙት ወደ ያፍሌጣውያን ይዞታ በመዝለቅ እስከ ታችኛው ቤትሖሮን ይደርሳል፤ ከዚያም ወደ ጌዜር ያልፍና መጨረሻው የሜድትራኒያን ባሕር ይሆናል።

4 የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ርስታቸውን እንደሚከተለው ተቀበሉ።


የኤፍሬም ድርሻ

5 የኤፍሬም ነገድ የርስት ድርሻ በየወገናቸው ይህ ነው፤ ድንበራቸው ከዐጣሮትአዳር በምሥራቅ በኩል ወደ ላይኛው ቤትሖሮን ይወጣል።

6 ከዚያም አልፎ እስከ ሜዲቴራኒያን ባሕር ይደርሳል፤ ሰሜናዊ ድንበራቸውም ሚክመታት ነው፤ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ታአናት ሺሎ ታጥፎ በምሥራቅ በኩል በማለፍ ወደ ያኖሐ ይሄዳል።

7 ከያኖሐም ተነሥቶ ወደ ዐጣሮትና ወደ ናዓራት በመዘቅዘቅ ኢያሪኮ ደርሶ መመለሻው የዮርዳኖስ ወንዝ ይሆናል።

8 ይኸው ድንበር በምዕራብ በኩል ከታፑሐ ተነሥቶ እስከ ቃና ወንዝ ይደርስና መጨረሻው የሜድትራኒያን ባሕር ይሆናል፤ ለኤፍሬም ነገድ በየወገኑ ርስት ሆኖ የተሰጠው ምድር ይህ ነበር።

9 እርሱም በምናሴ ርስት ክልል ውስጥ ያሉትንና ለኤፍሬማውያን የተሰጡትን ከተሞችና መንደሮችንም ይጨምራል፤

10 እነዚህ ኤፍሬማውያን ግን በጌዜር የሚኖሩ ከነዓናውያንን አላስወጡም ነበር፤ ስለዚህም ከነዓናውያን እስከ አሁን ድረስ በኤፍሬማውያን መካከል ይኖራሉ፤ ሆኖም ለኤፍሬማውያን የጒልበት ሥራ ለመሥራት ይገደዳሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos