ዘዳግም 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእስራኤላውያን የባሳን ንጉሥ ዖግን ድል ማድረጋቸው ( ዘኍ. 21፥31-35 ) 1 “ቀጥለንም በስተሰሜን በኩል ወደ ባሳን ግዛት ተጓዝን፤ ንጉሥ ዖግም ሕዝቡን ሁሉ አሰልፎ በኤድረዒ ከተማ ከእኛ ጋር ለመዋጋት ወጣ፤ 2 እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፤ ‘እርሱን አትፍራው፤ እርሱን ሕዝቡንና ምድሩን ሁሉ ለአንተ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ በሐሴቦን ተቀምጦ ይገዛ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ ሲሖን ላይ እንዳደረግህ ሁሉ በዚህም ላይ አድርግበት።’ 3 “ስለዚህም እግዚአብሔር አምላካችን የባሳንን ንጉሥ ዖግንና ሕዝቡን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን፤ እኛም ከእነርሱ አንድ እንኳ ሳናስቀር ሁሉንም አጠፋን። 4 በዚያኑ ጊዜ ከተሞቹን ሁሉ ያዝን፤ ያልወሰድነው ምንም ከተማ አልነበረም፤ በዚህም ዐይነት የባሳን ንጉሥ ዖግ በአርጎብ ግዛት ያስተዳድራቸው የነበሩትን ሥልሳ ከተሞች ወሰድን። 5 እነዚህም ሁሉ ከተሞች ከፍ ያለ ቁመት ባላቸው ቅጽሮች የተመሸጉ ነበሩ፤ የቅጽሮቹም በሮች በመወርወሪያ የሚዘጉ ነበሩ፤ ቅጽር የሌላቸው ብዙ መንደሮችም ነበሩ። 6 ከሐሴቦን ንጉሥ ሲሖን በወሰድናቸው ከተሞች ላይ ባደረግነው ዐይነት እነዚህን ከተሞች ሁሉ ደመሰስን፤ ወንዶችንና ሴቶችን፥ ሕፃናትም ሳይቀሩ አጠፋን። 7 ከብቱን ሁሉ ማርከን ወሰድን፤ ከተሞችንም በዘበዝን። 8 “በዚያን ጊዜ ከእነዚህ ከሁለቱ አሞራውያን ነገሥታት በዮርዳኖስ ምሥራቅ፥ ከአርኖን ወንዝ እስከ ሔርሞን ተራራ ያለውን ምድር ሁሉ ያዝን። 9 የሔርሞንን ተራራ ሲዶናውያን ሢርዮን ብለው ሲጠሩት፥ አሞራውያን ‘ሠኒር’ ብለው ሰይመውታል። 10 በዚህም ዐይነት የባሳን ንጉሥ የዖግ ግዛቶች የሆኑትን በደጋ የሚገኙትን ሳለካና ኤድረዒ ተብለው የሚጠሩትን ከተሞችና እንዲሁም የገለዓድንና የባሳንን አውራጃዎች ሁሉ ያዝን። 11 ከረፋያውያን ወገን ንጉሥ ዖግ የመጨረሻው ነበር፤ አልጋው ከብረት የተሠራ ሆኖ በይፋ በታወቀው መለኪያ ቁመቱ አራት ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ሁለት ሜትር ያኽል ነበር። እርሱም ራባ ተብላ በምትጠራው በዐሞናውያን ከተማ እስከ አሁን ይታያል። ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሰፈሩ ነገዶች ( ዘኍ. 32፥1-42 ) 12 “ምድሪቱን ከወረስን በኋላ በአርኖን ወንዝ አጠገብ ካለችው ከዓሮዔር ከተማ ጀምሮ በስተ ሰሜን በኩል ያለውን ግዛትና የኮረብታማይቱን የገለዓድን እኩሌታ ከነከተሞችዋ ለሮቤልና ለጋድ ነገዶች ሰጠሁ፤ 13 ለምናሴ ነገድ እኩሌታም ከገለዓድ የተረፈውንና ዖግ ይገዛው የነበረውን ባሳንን በሙሉ ሰጠሁ፤ ይኸውም መላው የአርጎብ ግዛት መሆኑ ነው።” ባሳን የረፋያውያን ምድር በመባል ይታወቅ ነበር፤ 14 ከምናሴ ነገድ ወገን የሆነው ያኢር መላውን የአርጎብ ምድር ወረሰ፤ ይህችውም እስከ ገሹርና እስከ ማዕካ ጠረፍ የምትደርሰው ባሳን ናት፤ መንደሮቹንም በእርሱ ስም እንዲጠሩ አደረገ፤ ስለዚህ እነርሱ የያኢር መንደሮች ተብለው እስከ ዛሬ ይጠራሉ። 15 “ገለዓድንም ከምናሴ ነገድ ወገን ለሆነው ለማኪር ቤተሰብ ሰጠሁ፤ 16 ለሮቤልና ለጋድ ነገዶችም ከገለዓድ እስከ አርኖን ወንዝ አጠገብ ያለውን ግዛት ሰጠሁ፤ የደቡብ ወሰናቸውም የአርኖን ወንዝ አጋማሽ ሲሆን የሰሜን ወሰናቸው የዐሞናውያን ጠረፍ ክፍል የሆነው የያቦቅ ወንዝ ነው። 17 በስተ ምዕራብ በኩል ያለው ግዛታቸው አራባን ዮርዳኖስንና በአካባቢው ያለውን ምድር ያጠቃልላል፤ በስተምሥራቅ በኩል ከገሊላ ባሕር በፒስጋ ተራራ ግርጌ እስካለው እስከ ጨው ባሕር ድረስ ይደርሳል። 18 “በዚህም ጊዜ የሚከተለውን መመሪያ ሰጠኋቸው፤ ‘እግዚአብሔር አምላካችን ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያለውን ይህን ምድር ትወርሱ ዘንድ ሰጥቶአችኋል፤ እንግዲህ የጦር ሰዎቻችሁን አስታጥቃችሁ ሌሎቹ የእስራኤል ነገዶች ምድራቸውን እስኪወርሱ ድረስ እነርሱን ለመርዳት ግንባር ቀደም ሆነው እንዲዘምቱ አድርጉ። 19 ብዙ ከብት እንዳላችሁ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም እዚህ መቅረት የሚችሉት ሚስቶቻችሁ፥ ልጆቻችሁና ከብቶቻችሁ ብቻ ናቸው፤ ስለዚህም እነርሱን እኔ በሰጠኋችሁ ከተሞች ወደ ኋላ ትታችሁ ትሄዳላችሁ። 20 እግዚአብሔር ለእናንተ በዚህ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ ለእነርሱም ከዮርዳኖስ በስተምዕራብ በኩል የሚያወርሳቸውን ምድር ሰጥቶ በሰላም እስካሳረፋቸው ድረስ ወገኖቻችሁን እስራኤላውያንን እርዱ፤ ከዚያም በኋላ እኔ ወደ ሰጠኋችሁ ወደዚህች ምድር መመለስ ትችላላችሁ።’ 21 “ከዚህም ቀጥሎ ኢያሱን እንዲህ ስል መከርኩት፤ ‘እግዚአብሔር አምላካችሁ ሲሖንና ዖግ ተብለው በሚጠሩት በሁለት ነገሥታት ያደረገውን በዐይናችሁ አይታችኋል፤ ምድሩን በምትወርሱበት በማንኛውም ሕዝብ ላይ ይህንኑ ተመሳሳይ ድርጊት ይደግመዋል። 22 የሚዋጋላችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ ስለ ሆነ እነርሱን አትፍሩ።’ ሙሴ ወደ ከነዓን እንዳይገባ መከልከሉ 23 “በዚያን ጊዜ እንዲህ ስል አጥብቄ ጸለይኩ፤ 24 ‘ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! ወደ ፊት ከምታደርጋቸው ታላላቅና አስደናቂ ነገሮች ሁሉ ያሳየኸኝ የመጀመሪያውን ክፍል ብቻ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ አንተ የምታደርጋቸውን ታላላቅ ነገሮች የሚያደርግ ሌላ አምላክ በሰማይም ሆነ በምድር የለም። 25 ጌታ ሆይ! የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሬ ከወንዙ ማዶ ያለችውን ውብና ኮረብታማ የሆነችውን ለምለሚቱን ምድርና የሊባኖስን ተራራ ማየት እንድችል ፍቀድልኝ።’ 26 “ነገር ግን በእናንተው በሕዝቡ ምክንያት እግዚአብሔር ተቈጣኝ፤ ልመናዬንም ማዳመጥ አልፈለገም፤ ይልቁንም በዚህ ፈንታ እንዲህ አለኝ፤ ‘እንግዲህስ በቃህ! ዳግመኛ ይህን ነገር አታንሣ! 27 ይልቅስ ተነሥና ወደ ፒስጋ ተራራ ላይ ውጣ፤ በዚያም ላይ ሆነህ ዐይንህ የቻለውን ያኽል የአገሪቱን ሰሜንና ደቡብ፥ ምሥራቅና ምዕራብ አሻግረህ ተመልከት፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ መሄድ ከቶ አይፈቀድልህም። 28 ይልቅስ ለኢያሱ አስፈላጊውን መመሪያ ስጠው፤ በማበረታታትም አጠንክረው፤ ሕዝቡ ተሻግረው ይህችን የምታያትን ምድር ይወርሱ ዘንድ የሚመራቸው እርሱ ነው።’ 29 “ከዚህም የተነሣ በቤትፔዖር ከተማ ፊት ለፊት ባለው ሸለቆ ውስጥ ቈየን።” |