ኤርምያስ 14:16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህንንም የተነበዩላቸው ሕዝብ ሁሉ በራብና በጦርነት ይሞታሉ፤ ሬሳቸውም ሁሉ በኢየሩሳሌም ውስጥ በየመንገዱ ይወድቃል፤ የሚቀብራቸውም አይኖርም፤ ይህም በሚስቶቻቸው፥ በወንዶች ልጆቻቸውና በሴቶች ልጆቻቸው ሳይቀር በሁሉም ላይ ይፈጸማል፤ በበደላቸውም መጠን ተገቢ ቅጣታቸውን እሰጣቸዋለሁ።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም ትንቢቱ የተነገረለትም ሕዝብ ከሰይፍና ከራብ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባዮች ይወድቃል፤ እነርሱንም ሆነ ሚስቶቻቸውን ወይም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቀብራቸው አይገኝም። ለበደላቸው የሚገባውንም ቅጣት በላያቸው አወርዳለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባይ ይጣላሉ፤እነርሱንና ሚስቶቻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም፤ ክፋታቸውንም በእነርሱ ላይ አወርድባቸዋለሁ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም መንገዶች ይበተናሉ፤ ክፋታቸውንም አፈስስባቸዋለሁና እነርሱንና ሚስቶቻቸውን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባይ ይበተናሉ፥ ክፋታቸውንም አፈስስባቸዋለሁ እነርሱንና ሚስቶቻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም። |
ልጆችሽ በወጥመድ ውስጥ እንደ ተያዘ ድኩላ በየመንገዱ አደባባይ ተዝለፍልፈው ወድቀዋል፤ በእነርሱም ላይ የአምላክሽ የእግዚአብሔር ተግሣጽና ቊጣ ወርዶባቸዋል።
ሁሉም በአሠቃቂ በሽታ ያልቃሉ፤ የሚያለቅስላቸውም ሆነ የሚቀብራቸው እንኳ አያገኙም፤ ሬሳቸው እንደ ጒድፍ በሜዳ ላይ ይከመራል፤ በጦርነትና በራብ ያልቃሉ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ምግብ ይሆናል።
አምላክ ሆይ! አሁን ግን ልጆቻቸው በራብ እንዲያልቁ፥ እነርሱም በጦርነት እንዲወድቁ አድርግ፤ ሴቶቻቸው ያለ ባልና ያለ ልጅ ይቅሩ፤ ወንዶቻቸው በበሽታ ወጣቶቻቸውም በጦርነት ይደምሰሱ።
ፓሽሑር ሆይ! አንተም ራስህና ቤተሰብህ በሙሉ ተማርካችሁ ወደ ባቢሎን ትወሰዳላችሁ፤ በሐሰት ከተነበይክላቸው ከወዳጆችህ ሁሉ ጋር ሞተህ በዚያው ትቀበራለህ።’ ”
እርሱ ያልላካቸው መሆኑንና እነርሱ በስሙ የሚነግሩአችሁ ሁሉ ውሸት መሆኑን እግዚአብሔር ራሱ ነግሮአችኋል። ስለዚህ እርሱ ያሳድዳችኋል፤ እናንተና ይህን ውሸት የሚነግሩአችሁ ነቢያት ሁሉ ትጠፋላችሁ።”
ይሁዳ ሆይ! ይህ ሁሉ የደረሰብሽ በአካሄድሽና በክፉ ሥራሽ ምክንያት ነው፤ ይህም ሁሉ የመረረ መከራ የመጣብሽ በኃጢአትሽ ምክንያት ስለ ሆነ ወደ ሰውነትሽ ዘልቆ ልብሽን አቊስሎታል።
ነቢያት ነን የሚሉት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ ካህናቱ በነቢያት ምክር ያስተዳድራሉ፤ ሕዝቡም ይህን ሁሉ አይቃወሙም፤ ታዲያ የዚህ ሁሉ ፍጻሜ በሚደርስበት ጊዜ ምን ይበጃችሁ ይሆን?”
“በዚያን ጊዜ የይሁዳ ነገሥታትና የመኳንንት ዐፅሞች እንዲሁም የካህናቱና የነቢያቱ የሌላውም የኢየሩሳሌም ነዋሪ ሕዝብ ዐፅሞች ሁሉ ከየመቃብሩ ተለቅመው ይወጣሉ።
ዐፅሞቻቸው ተሰብስበው በመቀበር ፈንታ፥ እንደ ጒድፍ የትም ይጣላሉ፤ እነርሱም፥ ሕዝቡ በማምለክና ምክር በመጠየቅ በፍቅር ያገለግሉአቸው በነበሩት በፀሐይ፥ በጨረቃና በከዋክብት ፊት ይበተናሉ።
እኔም እንዲህ አልኩ፦ “እናንተ ሴቶች፥ እግዚአብሔር የሚለውን አድምጡ፤ ቃሉንም ለመቀበል የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ እንዴት ማልቀስ እንደሚገባቸው ሴቶች ልጆቻችሁን አስተምሩ፤ ሙሾ የማውጣትንም ዘዴ ለወዳጆቻችሁ አስጠኑ።
የሰው ሬሳ የትም እንደሚጣል ቈሻሻ በየስፍራው ተበትኖአል፤ አጫጆች ቈርጠው እንደ ጣሉትና ማንም እንደማይሰበስበው ቃርሚያ ሆኖአል፤ እግዚአብሔር እንድናገር ያዘዘኝ ይህ ነው።”
ስለዚህም አሜስያስ ሆይ! እግዚአብሔር ስለ አንተ እንዲህ ይላል፦ ‘ሚስትህ በከተማይቱ አመንዝራ ትሆናለች፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በጦርነት ይሞታሉ፤ ርስትህንም ባዕዳን በገመድ ለክተው ይከፋፈሉታል፤ አንተም በአሕዛብ ምድር ትሞታለህ፤ የእስራኤልም ሕዝብ ያለ ጥርጥር ተማርከው ከአገራቸው ይወሰዳሉ።’ ”
ከዚህ በኋላ ሰባቱን መላእክት “ሂዱ! የእግዚአብሔርን ቊጣ የያዙትን ሰባቱን ጽዋዎች በምድር ላይ አፍስሱ!” የሚል ከፍ ያለ ድምፅ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ሰማሁ።