ኤርምያስ 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ስለ ተገደሉት ሕዝቤ ቀንና ሌሊት አለቅስ ዘንድ፥ ራሴ የውሃ ጒድጓድ፥ ዐይኖቼም የእንባ ምንጭ በሆኑ እንዴት በወደድሁ ነበር! 2 ሕዝቤ እምነተ ቢሶችና አታላዮች ስለ ሆኑ፥ ከእነርሱ ተለይቼ በምድረ በዳ ውስጥ የምኖርበት የመንገደኞች ማደሪያ ቦታ ባገኝ፥ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር! 3 እነርሱ በአንደበታቸው ሐሰት ለመናገር ዘወትር የተዘጋጁ ናቸው፤ ስለዚህም በምድሪቱ ላይ በእውነት ፈንታ ሐሰት ነግሦአል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤ ከአንዱ ኃጢአት ወደ ሌላው ኃጢአት ይተላለፋሉ፤ የእኔንም አምላክነት ዐውቀው አላከበሩኝም።” 4 እያንዳንዱ ከባልንጀራው ተንኰል ይጠንቀቅ፤ ወንድሙን እንኳ ቢሆን ማመን የለበትም፤ ወንድም የተባለ ሁሉ (እንደ ያዕቆብ) አታላይ ሆኖአል፤ ወዳጅ የተባለም ሁሉ የባልንጀራውን ስም ያጠፋል። 5 ሁሉም ባልንጀራውን በማሞኘት ያሳስታል፤ እውነት የሚናገርም የለም፤ አንደበታቸው ውሸት መናገርን እንዲለማመድ አድርገውታል፤ ኃጢአት በመሥራት ሰውነታቸውን ያደክማሉ። 6 ግፍን በግፍ ላይ ማታለልንም በማታለል ላይ እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ “እኔም አምላካቸው መሆኔን ለመቀበል እምቢ ብለዋል” ይላል እግዚአብሔር። 7 ከዚህም የተነሣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤን ለማጥራት እንደ ብረት እፈትናቸዋለሁ፤ ሕዝቤ ክፉ ነገር ስለ ፈጸሙ ይህን ከማድረግ በቀር ሌላ ምን አደርጋቸዋለሁ? 8 አንደበታቸው ዘወትር ተንኰል ስለሚናገር፥ እንደ አደገኛ ፍላጻ ነው፤ እያንዳንዱ ባልንጀራውን በፍቅር ቃል ያነጋግረዋል፤ ነገር ግን በስውር ወጥመድ ይዘረጋበታል። 9 ታዲያ በዚህ ሁሉ ነገር እነርሱን ልቀጣቸውና እንደነዚህ ያሉትንስ ሕዝብ ልበቀላቸው አይገባኝምን? እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” 10 እኔም እንዲህ አልኩ፦ “ሁሉም ወና ስለ ሆኑና በእነርሱም ላይ የሚዘዋወርባቸው ስለሌለ፥ ስለ ተራራዎች አዝናለሁ፤ ስለ ሜዳዎችም አለቅሳለሁ፤ የከብቶች ድምፅ ዳግመኛ አይሰማም፤ የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት ሁሉ ሸሽተው ጠፍተዋል።” 11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ኢየሩሳሌምን የፍርስራሽ ክምር አደርጋታለሁ፤ የቀበሮዎችም መፈንጫ ትሆናለች፤ የይሁዳንም ከተሞች ማንም የማይኖርባቸው ባድማ አደርጋቸዋለሁ።” 12 እኔም እንዲህ አልኩ፦ “ምድሪቱ ማንም ሊዘዋወርባት የማይችል ደረቅ በረሓና ጠፍ መሆንዋ ስለ ምንድን ነው? ይህንንስ የሚያስተውል ጥበበኛ ሰው ማን ነው? ለሌሎች ማስረዳት ይችል ዘንድ የገለጥክለትስ ማን ነው?” 13 እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ሕዝቤ እኔ የሰጠኋቸውን ሕግ በመተዋቸው ነው፤ እነርሱ ለእኔ አልታዘዙም፤ የነገርኳቸውንም ሁሉ አልፈጸሙም። 14 ይህን በማድረግ ፈንታ እልኸኞች ሆኑ፤ አባቶቻቸው ባስተማሩአቸውም መሠረት ለባዓል ምስሎች ሰገዱ። 15 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እኔ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የማደርገውን ነገር ልንገራችሁ፤ ይህ ሕዝብ ምግቡ መራራ መጠጡም የተመረዘ ውሃ እንዲሆንበት አደርጋለሁ። 16 እነርሱም ሆኑ የቀድሞ አባቶቻቸው በማያውቁአቸው አሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፤ እስከማጠፋቸውም ድረስ በሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ።” የኢየሩሳሌም ሕዝብ ርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙት ጩኸት 17 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “አሁንም አስቡ፥ አልቃሾችን በአንድነት ሰብስቡ፤ ሙሾ የሚያወጡ ሴቶችንም ጥሩ።” 18 ሕዝቡም እንዲህ አሉ፦ “ዐይናችን በእንባ እንዲርስ፥ በጉንጫችንም እንባው እንዲወርድ፥ አስለቃሾች በቶሎ ሙሾ እንዲያወጡ ንገሩአቸው።” 19 በጽዮን “ወዮልን ልንጠፋ ነው! ፈጽሞም ተዋረድን! ቤቶቻችን ስለ ፈራረሱ አገራችንን ለቀን መሄዳችን ነው” እየተባለ የሚያስተጋባውን የለቅሶ ጩኸት አድምጡ። 20 እኔም እንዲህ አልኩ፦ “እናንተ ሴቶች፥ እግዚአብሔር የሚለውን አድምጡ፤ ቃሉንም ለመቀበል የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ እንዴት ማልቀስ እንደሚገባቸው ሴቶች ልጆቻችሁን አስተምሩ፤ ሙሾ የማውጣትንም ዘዴ ለወዳጆቻችሁ አስጠኑ። 21 ሞት በየመስኮቶቻችን ገብቶአል፤ በየቤተ መንግሥታችንም ውስጥ ገብቷል፤ ልጆችን በየመንገዱ፥ ጐልማሶችንም በየአደባባዩ ቀሥፎአል። 22 የሰው ሬሳ የትም እንደሚጣል ቈሻሻ በየስፍራው ተበትኖአል፤ አጫጆች ቈርጠው እንደ ጣሉትና ማንም እንደማይሰበስበው ቃርሚያ ሆኖአል፤ እግዚአብሔር እንድናገር ያዘዘኝ ይህ ነው።” 23 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ጠቢብ በጥበቡ፥ ብርቱ ሰውም በኀይሉ፥ ባለጸጋም በሀብቱ አይመካ፤ 24 አንድ ሰው መመካት ካለበት በምድር ላይ ምሕረትን፥ ትክክለኛ ፍርድንና እውነትን የማስገኝ እኔ አምላክ መሆኔን በመረዳት ይመካ፤ እኔም ደስ የሚያሰኘኝ ይኸው ነው፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” 25 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ለስም ብቻ የተገረዙትን ሁሉ የምቀጣበት ጊዜ ይመጣል፤ 26 የግብጽ፥ የይሁዳ፥ የኤዶም፥ የአሞን፥ የሞአብና በበረሓ ጠረፍ የሚኖሩ የግንባራቸውን ግራና ቀኝ ጠጒር የተላጩ ሕዝቦች እንዲሁም የእስራኤል ሕዝብ ከልባቸው ያልተገረዙ ስለ ሆኑ ሁሉንም በአንድ ዐይነት እቀጣለሁ።” |