Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኤርምያስ ፖሽሑር ከተባለው ካህን ጋር ያደረገው ክርክር

1 የቤተ መቅደሱ አለቃ የሆነው የኢሜር ልጅ ፖሽሑር ይህን ስናገር በሰማ ጊዜ፥

2 ተይዤ እንድደበደብ አዘዘ፤ ከቤተ መቅደሱም በላይኛው በኩል ባለው በብንያም የቅጽር በር በእግር ግንድ እንድታሰር አደረገ።

3 በማግስቱም ከሰንሰለት እስራት ከፈታኝ በኋላ እንዲህ አልኩት፥ “ከእንግዲህ ወዲህ እግዚአብሔር ስምህን ፓሽሑር ብሎ አይጠራህም፤ ለአንተ ያወጣልህ ስም ‘ሽብር በየስፍራው’ የሚል ነው።

4 እግዚአብሔር ራሱ እንዲህ ብሎአል፦ ‘ለራስህና ለጓደኞችህም ጭምር አሸባሪ ላደርግህ ነው፤ እነርሱም ሁሉ በጠላቶቻቸው ሰይፍ ሲገደሉ ታያለህ፤ የይሁዳን ሕዝብ ሁሉ በባቢሎን ንጉሥ ሥልጣን ሥር አደርጋለሁ፤ እርሱ እኩሌቶቹን እስረኛ አድርጎ ወደ ባቢሎን ይወስዳቸዋል፤ እኩሌቶቹንም እዚሁ ይገድላቸዋል።

5 እንዲሁም ጠላቶቻቸው የዚህችን ከተማ ሀብት ሁሉ እንዲዘርፉት፥ ያካበተችውንም ሀብትና ንብረት አጋብሰው የይሁዳን ነገሥታት የሀብት መዛግብት እንኳ ሳይቀር ጠራርገው ወደ ባቢሎን እንዲወስዱት አደርጋለሁ፤

6 ፓሽሑር ሆይ! አንተም ራስህና ቤተሰብህ በሙሉ ተማርካችሁ ወደ ባቢሎን ትወሰዳላችሁ፤ በሐሰት ከተነበይክላቸው ከወዳጆችህ ሁሉ ጋር ሞተህ በዚያው ትቀበራለህ።’ ”


ኤርምያስ ለእግዚአብሔር የገለጠው ብሶት

7 እግዚአብሔር ሆይ! አታለልከኝ፤ እኔም ተታለልኩ፤ አንተ ከእኔ ትበረታለህ፤ ኀይልህም በእኔ ላይ እጅግ ከፍ ያለ ነው፤ ሰው ሁሉ በየዕለቱ በማሽሟጠጥ ይዘባበትብኛል።

8 እኔ በምናገርበት ጊዜ ሁሉ የምናገረው ዐመፅንና ጥፋትን ነው፤ አምላክ ሆይ! አንተ ያዘዝከኝን የትንቢት ቃል በመናገሬ፥ እኔ ዘወትር እሰደባለሁ፤ መላገጫም ሆኛለሁ።

9 ነገር ግን “ከእንግዲህ እግዚአብሔርን አላስታውስም፤ በስሙም አልናገርም” በምልበት ጊዜ፥ ከእርሱ የተሰጠኝ የትንቢት ቃል በውስጤ እንደ እሳት ይነዳል፤ በውስጤ ሰውሬ ልይዘው ብሞክርም፤ አፍኜ ላስቀረው አይቻለኝም።

10 ብዙ ሰዎች ፈርተው በሹክሹክታ እንዲህ ሲሉ ሰማሁ፤ “አሁን ኤርምያስን ለመክሰስ መልካም አጋጣሚ ነው!” ወዳጆቼ ናቸው የሚባሉት እንኳ ስሕተት እንዳደርግ ይጠባበቃሉ፤ “ኤርምያስ ሊታለል ይችል ይሆናል፤ ይህም ከሆነ እርሱን ይዘን እንበቀለዋለን፤” ይላሉ።

11 እግዚአብሔር ግን እንደ ጀግና ወታደር ከእኔ ጋር ነው፤ ስለዚህ አሳዳጆቼ በመደናቀፍ ኀይል አጥተው ይወድቃሉ። በሚወድቁበትም ጊዜ ክፉኛ ይዋረዳሉ፤ ውርደታቸውም ለረጅም ጊዜ ይታወሳል።

12 የሠራዊት አምላክ ሆይ! ጻድቅን ፈትነህ ታረጋግጣለህ፤ የልብንም ጥልቅ ሐሳብ ትመረምራለህ፤ አቤቱታዬን ለአንተ አቅርቤአለሁ፤ ስለዚህ ጠላቶቼን ስትበቀል እንዳይ አድርገኝ።

13 ለእግዚአብሔር ዘምሩ! ጌታን አመስግኑ! እርሱ ችግረኞችን ከክፉ ሰዎች ኀይል ይታደጋል።

14 የተወለድኩበት ቀን የተረገመ ይሁን! እናቴ እኔን የወለደችበትም ዕለት የተባረከ አይሁን!

15 ለአባቴ “ወንድ ልጅ ተወልዶልሃልና ደስ ይበልህ” ብሎ ያበሠረው ሰው የተረገመ ይሁን!

16 ያ ሰው፥ እግዚአብሔር ያለምሕረት እንደ ደመሰሳቸው ከተሞች ሆኖ ይቅር፤ በማለዳ የዋይታ ጩኸት ይስማ፤ በቀትርም በጦርነት ወሬ ይሸበር።

17 መቃብር እንድትሆነኝ ምነው በእናቴ ማሕፀን በገደለኝ ኖሮ! የእናቴ ማሕፀንም ለሁልጊዜ ትልቅ ሆኖ በኖረ ነበር።

18 ሐዘንና ልፋትን ለማየት፥ ዘመኔንም በዕፍረት ለመፈጸም ስለምን ተወለድኩ?

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos