Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 27 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኤርምያስ የተሸከመው ቀንበር

1 የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ በይሁዳ ከነገሠ በኋላ ወዲያውኑ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦

2 “የጠፍር ማሰሪያና ማነቆ ያለው ቀንበር ከእንጨት ሠርተህ በጫንቃህ ላይ ተሸከም።

3 በኢየሩሳሌም ወደሚኖረው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በመጡት መልእክተኞች በኩል ወደ ኤዶም፥ ሞአብ፥ ዐሞን፥ እንዲሁም ወደ ጢሮስና ሲዶና ነገሥታት መልእክት ላከ።

4 ለጌቶቻቸው የሚያደርሱትን ይህን የእኔን የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክን መልእክት እንዲያደርሱ ንገራቸው!

5 ‘በታላቁ ኀይሌና ብርታቴ ዓለምንና የሰውን ዘር እንዲሁም በምድር ላይ የሚኖሩ እንስሶችን ሁሉ ፈጠርኩ፤ ምድርንም የሚገዛ ማን እንደሚሆን እወስናለሁ።

6 እነዚህ ሕዝቦች ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ በሆነው በአገልጋዬ በናቡከደነፆር ሥልጣን ሥር እንዲገዙለት ያደረግኹ እኔ ነኝ፤ የምድር አራዊትም ሳይቀሩ ይገዙለታል።

7 ሕዝቦች ሁሉ ያገለግሉታል፤ እንዲሁም የገዛ ሕዝቡ የሚወድቅበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ ለልጁና ለልጅ ልጁ ጭምር ተገዢዎች ይሆናሉ፤ ከዚያም በኋላ የእርሱ ሕዝብ ለኀያላን ሕዝቦችና ለታላላቅ ነገሥታት አገልጋዮች ይሆናሉ።’

8 “ነገር ግን ማንኛውም ሕዝብ ወይም መንግሥት ‘እርሱን አላገለግልም፤ በቀንበሩም ሥር ሆኜ አልገዛም’ ቢል ናቡከደነፆር ራሱ እንዲደመስሰው እስከ ፈቀድኩለት ድረስ፥ በጦርነት፥ በራብና በወረርሽኝ እንዲቀጡ አደርጋለሁ።

9 ነቢያታችሁንና በጥንቈላ፥ በመተት፥ ወይም የሙታን መናፍስትን በመሳብና ሕልም በማየት ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ እናውቃለን የሚሉትን ሁሉ አትስሙአቸው፤ እነርሱ ሁሉ የሚመክሩአችሁ ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም ብለው ነው፤

10 እነርሱ ለእናንተ የሚናገሩት ትንቢት የሐሰት ትንቢት ነው፤ ከትውልድ አገራችሁ ወደ ሩቅ አገር ትወሰዳላችሁ፤ እኔም ስለማሳድዳችሁ ትጠፋላችሁ።

11 ነገር ግን በባቢሎን ንጉሥ ቀንበር ሥር ሆኖ የሚገዛለትና የሚያገለግለው ሕዝብ በገዛ ምድሩ እያረሰ እንዲኖር እፈቅድለታለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

12 ለይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስም ይህንኑ ቃል እንዲህ ብዬ ነገርኩት፦ “ለባቢሎን ንጉሥ ብትገብር፥ እርሱንና ሕዝቡንም ብታገለግል በሕይወት መኖር ትችላለህ፤

13 ለምንስ አንተና ሕዝብህ በጦርነት፥ በራብና በቸነፈር ታልቃላችሁ? ለባቢሎን ንጉሥ በማይገዛ በማናቸውም ሕዝብ ላይ ይደርስበታል ብሎ እግዚአብሔር የተናገረውም ይህንኑ ነው።

14 ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም፥ ብለው የሚነግሩአችሁን የነቢያት ቃል አትስሙ፤ እነርሱ የሚናገሩት የሐሰት ትንቢት ነው።

15 እርሱ ያልላካቸው መሆኑንና እነርሱ በስሙ የሚነግሩአችሁ ሁሉ ውሸት መሆኑን እግዚአብሔር ራሱ ነግሮአችኋል። ስለዚህ እርሱ ያሳድዳችኋል፤ እናንተና ይህን ውሸት የሚነግሩአችሁ ነቢያት ሁሉ ትጠፋላችሁ።”

16 ከዚህ በኋላ ለካህናቱና ለሕዝቡ እንዳስታውቅ እግዚአብሔር የሚከተለውን ነገረኝ፤ እንዲህ ብዬም ነገርኳቸው፦ “ ‘የቤተ መቅደሱ ዕቃ ሁሉ ከባቢሎን ተመልሶ በፍጥነት ይመጣል’ እያሉ የሚነግሩአችሁን ነቢያት ሁሉ አትስሙአቸው፤ እነርሱ የሚናገሩት የሐሰት ትንቢት ነው፤

17 ስለዚህ እነርሱን መስማት ትታችሁ ለባቢሎን ንጉሥ ብትገዙለት በሕይወት ትኖራላችሁ፤ ይህችስ ከተማ ስለምን የፍርስራሽ ክምር ሆና ትቀራለች?

18 እነርሱ ነቢያት ከሆኑና እኔም የሰጠኋቸው የትንቢት ቃል በእነርሱ ዘንድ ካለ፥ ገና ያልተወሰደው በቤተ መቅደስ፥ በይሁዳ ቤተ መንግሥትና በኢየሩሳሌም የቀረው ዕቃ ሁሉ ወደ ባቢሎን እንዳይወሰድ አደርግ ዘንድ እየተማጠኑ ሁሉን ቻይ የሆንኩትን እኔን እግዚአብሔርን ይጠይቁኝ።”

19-20 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳ ንጉሥ የሆነውን የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ታላላቅ ሰዎች ጋር ወደ ባቢሎን ማርኮ በወሰደው ጊዜ ዐምዶችን፥ ከነሐስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ፥ የብረት ማስቀመጫዎችንና ሌሎችንም የቤተ መቅደስ ዕቃዎች በኢየሩሳሌም ትቶአቸው ሄዶ ነበር።

21 “በኢየሩሳሌም፥ በቤተ መቅደሱና በቤተ መንግሥቱ ስለ ቀሩት ዕቃዎች ሁሉ የእስራኤል አምላክ የሆንኩ እኔ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የምናገረውን ቃል ስሙ፤

22 ሐሳቤን ወደ እነርሱ እስከምመልስበት ጊዜ ድረስ፥ እነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ወደ ባቢሎን ተወስደው በዚያ ይኖራሉ። ከዚያም በኋላ እንደገና መልሼ ወደዚህ ስፍራ አመጣቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos