ኤርምያስ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 “በዚያን ጊዜ የይሁዳ ነገሥታትና የመኳንንት ዐፅሞች እንዲሁም የካህናቱና የነቢያቱ የሌላውም የኢየሩሳሌም ነዋሪ ሕዝብ ዐፅሞች ሁሉ ከየመቃብሩ ተለቅመው ይወጣሉ። 2 ዐፅሞቻቸው ተሰብስበው በመቀበር ፈንታ፥ እንደ ጒድፍ የትም ይጣላሉ፤ እነርሱም፥ ሕዝቡ በማምለክና ምክር በመጠየቅ በፍቅር ያገለግሉአቸው በነበሩት በፀሐይ፥ በጨረቃና በከዋክብት ፊት ይበተናሉ። 3 ከዚህም ክፉ ትውልድ የተረፉትና እኔ በበተንኳቸው ቦታ የሚኖሩትም ሕዝብ ከመኖር ይልቅ መሞትን ይመርጣሉ።” ኃጢአት ያስከተለው ቅጣት 4 እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ተናገር አለኝ፦ “የወደቀ ሰው እንደገና መነሣት አይችልምን? መንገድ ተሳስቶት የጠፋ ሰው አይመለስምን? 5 ታዲያ ሕዝቤ ወደ እኔ በመመለስ ፈንታ እንደ ራቃችሁ የምትቀሩት ስለምንድነው? ወደ እኔ መመለስን እምቢ ብላችሁ ወደ ጣዖት አዘነበላችሁ። 6 እኔ በጥንቃቄ አዳመጥኩ፤ እናንተ ግን እውነት አልተናገራችሁም፤ ከእናንተ መካከል ስለ ክፉ ሥራው የተጸጸተ አንድም የለም፤ ‘የፈጸምኩት በደል ምንድን ነው?’ ብሎ የጠየቀም የለም፤ እያንዳንዳችሁም ወደ ጦርነት እንደሚሮጥ ፈረስ በየፊናችሁ ትሮጣላችሁ። 7 ሽመላዎች እንኳ የሚመለሱበትን ጊዜ ያውቃሉ፤ ዋኖሶች፥ ጨረባዎች፥ ዋርዳዎችም በኅብረት የሚሰደዱበትን ጊዜ ያውቃሉ፤ እናንተ ሕዝቤ ግን እንድትተዳደሩበት የሰጠኋችሁን ሕግ አታውቁም። 8 ታዲያ ‘እኛ ጠቢባን ነን፤ የእግዚአብሔርንም ሕግ እናውቃለን’ የምትሉት ስለምንድን ነው? ሐሰተኞች ጸሐፊዎች ሕጌን እንዳዛቡ አትመለከቱምን? 9 ጥበበኞቻችሁ ኀፍረት ደርሶባቸዋል፤ በወጥመድ ተይዘውም ግራ ገብቶአቸዋል፤ እነርሱ ቃሌን ትተዋል፤ ታዲያ ምን ዐይነት ጥበብ ሊኖራቸው ይችላል? 10 ስለዚህ እርሻቸውን ሁሉ ለሌሎች ርስት አድርጌ እሰጣለሁ፤ ሚስቶቻቸውንም ሌሎች ወንዶች እንዲቀሙአቸው አደርጋለሁ፤ ታላላቆችም ሆኑ ታናናሾች እያንዳንዱ ሰው በማታለል ጥቅምን ያግበሰብሳል፤ ነቢያትና ካህናት ሳይቀሩ ሕዝቡን ያታልላሉ፤ 11 የሕዝቤንም የስብራት ቊስል እንደ ቡጭራት በመቊጠር በሚገባ አያክሙትም፤ እንዲሁም ሰላም ሳይኖር ‘ሰላም ነው ሰላም ነው’ ይላሉ። 12 ሕዝቤ ሆይ! ይህን ሁሉ አጸያፊ ነገር ስታደርጉ ጥቂት ኀፍረት ተሰምቶአችሁ ነበርን? ኀፍረት ሊሰማችሁ ቀርቶ ዐይናችሁ እንኳ ሰበር አላለም፤ ስለዚህ ሌሎች እንደ ወደቁ እናንተም ትወድቃላችሁ፤ እኔ በምቀጣችሁ ጊዜ ፍጻሜአችሁ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 13 “ገበሬ ሰብሉን እንደሚሰበስብ ሕዝቤን ልሰበስብ ፈለግኹ፤ እነርሱ ግን ዘለላ እንደሌለው የወይን ተክል ፍሬ አልባ እንደ ሆነ የበለስ ዛፍና ቅጠሉ እንደ ረገፈ ተክል ሆኑብኝ፤ በዚህ ምክንያት የሰጠኋቸውን ምድር ባዕዳን እንዲወስዱባቸው አደረግሁ።” 14 የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዲህ ይላሉ፦ “ዝም ብለን መቀመጣችን ለምንድን ነው? አምላካችን እግዚአብሔር ሞት ፈርዶብናል፤ እርሱን ስለ በደልን የተመረዘ ውሃ እንድንጠጣ አድርጎናል። ኑ! ወደተመሸጉ ከተሞች ሮጠን እዚያ እንሙት፤ 15 ሰላምና ፈውስ የምናገኝበት ጊዜ ይመጣልናል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፤ በዚህ ፈንታ ሽብር በመምጣቱ ምኞታችን ከንቱ ሆኖ ቀረ። 16 ጠላቶቻችን እስከ ዳን ከተማ ደርሰዋል፤ ፈረሶቻቸው ሲያንኮራፉ ድምፃቸው ይሰማል፤ ሰንጋ ፈረሶቻቸውም ሲያሽካኩ ምድር ትናወጣለች፤ ጠላቶቻችን የመጡት ምንም ሳያስቀሩ ሕዝባችንንና ከተሞቻችንን እንዲሁም በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ ለማጥፋት ነው።” 17 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ተጠንቀቁ! እነሆ የአስማተኛ ድግምት ሊገታቸው የማይችል መርዘኛ እባቦችንና እፉኝቶችን በመካከላችሁ እልካለሁ፤ እነርሱም ይነድፉአችኋል።” ኤርምያስ ስለ ሕዝቡ ማዘኑ 18 መጽናናት የማይገኝለት ብርቱ ሐዘን ደርሶብኛል፤ ልቤም እጅግ ዝሎአል። 19 እስቲ አድምጡ! “እግዚአብሔር ዳግመኛ በጽዮን አይገኝምን? የጽዮን ንጉሥ ዳግመኛ በዚያ አይኖርምን?” እያሉ ሕዝቤ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ሲጮኹ እሰማለሁ። ንጉሣቸው እግዚአብሔርም፦ “ጣዖቶቻችሁን በማምለክና ለባዕድ አማልክታችሁም በመስገድ የምታስቈጡኝ ስለምንድን ነው?” ሲል ይመልስላቸዋል፤ 20 ሕዝቡም “እነሆ የመከር ወራት አለፈ፤ በጋውም ተፈጸመ፤ እኛ ግን አልዳንም!” በማለት ይጮኻሉ። 21 ሕዝቤ በመሰበሩ የእኔም ልብ ተሰብሮአል፤ ፍርሀትም ይዞኝ አለቅሳለሁ። 22 በገለዓድ የቅባት መድኃኒት የለምን? ሐኪሞችስ በዚያ አይገኙምን? ታዲያ ሕዝቤ የማይፈወሱት ስለምንድን ነው? |