ኢሳይያስ 43:7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እነርሱ በስሜ የተጠሩና ለክብሬ የፈጠርኳቸው በእጄም የአበጀኋቸውና የሠራኋቸው ሕዝቤ ናቸው።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ ያበጀሁትንና የሠራሁትን አምጡ።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ።” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ” እለዋለሁ። |
የዛፍ ቅርንጫፎች በሚደርቁበትም ጊዜ ይሰባበራሉ፤ ሴቶችም ለእሳት ማገዶ ይለቅሙአቸዋል፤ ሕዝቡ ማስተዋል ስለ ጐደለው ፈጣሪ አምላኩ አይራራለትም፤ ምንም ምሕረት አያደርግለትም።
የእጄ ሥራ የሆኑትን ልጆቻቸውን በመካከላቸው ባዩ ጊዜ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የእስራኤልን ቅዱስ ያከብራሉ፤ በእስራኤልም አምላክ ፊት በፍርሃት ይቆማሉ።
የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ! የፈጠራችሁ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የታደግኋችሁ ስለ ሆነ አትፍሩ፤ እናንተ የእኔ ናችሁ፤ በስማችሁም ጠርቼአችኋለሁ።
ሰማያት ሆይ! እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን በማዳን ክብሩን ገልጦአልና በደስታ ዘምሩ፤ ምድርም ከታች እልል በዪ፤ ተራራዎች፥ ጫካዎችና በውስጣቸው የምትገኙ ዛፎች ሁሉ የደስታ ድምፅ እያሰማችሁ ፈንድቁ።
ለእነርሱ በቤተ መቅደሴና በግቢዬ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የተሻለ መታሰቢያ እንዲኖራቸው አደርጋለሁ፤ የማይረሳ ዘላቂ መታወቂያም እሰጣቸዋለሁ።”
ለምን ግራ እንደ ተጋባ ሰውና ሌላውን መርዳት እንደማይችል ኀይለኛ ወታደር ትሆናለህ? እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን በመካከላችን ነህ፤ በስምህም እንጠራለን፤ እባክህ አትተወን።’ ”
አምላክ ሆይ! እባክህ አድምጠኝ፤ የእኛን ችግርና በስምህ የምትጠራውን ከተማ ጥፋት ተመልከት፤ ወደ አንተ የምንጸልየው የአንተን ምሕረት በመተማመን እንጂ በእኛ መልካም ሥራ በመመካት አይደለም።
እግዚአብሔር ሆይ! ስማን! እግዚአብሔር ሆይ! ይቅር በለን! እባክህ አድምጠን! ሥራህንም ግለጥ! አምላክ ሆይ! አትዘግይ፤ ይህች ከተማና ይህ ሕዝብ በስምህ የተጠሩ ናቸው።”
ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው፤ ሁለቱም አንድ ዓመት ሙሉ ከቤተ ክርስቲያን ጋር በአንድነት ሆነው ብዙ ሰዎችን አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ “ክርስቲያን” ተብለው ተጠሩ።
እኛ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጃቸውን መልካም ሥራዎች እንድንሠራ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንደገና የተፈጠርን የእግዚአብሔር ፍጡሮች ነን።
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚያስደንቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን አስደናቂ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ እግዚአብሔር ለራሱ ያደረጋችኹ ቅዱስ ሕዝብ ናችሁ።
የሚያስተምር፥ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚያስተምር ያስተምር፤ የሚያገለግልም እግዚአብሔር በሚሰጠው ኀይል ያገልግል፤ በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሁሉ ነገር ይመሰገናል፤ ክብርና ሥልጣን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን።
ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፤ ይህችም ከተማ ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ናት፤ የእኔንም አዲስ ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።