ራእይ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም(5) የሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን 1 “ለሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ “ይህ፥ ሰባቱን የእግዚአብሔር መንፈሶችና ሰባቱን ኮከቦች ከያዘው የተነገረ ነው፤ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ በስም ሕያው ነህ፤ ነገር ግን ሞተሃል። 2 ንቃ፤ ሊሞት የተቃረበውንና የቀረልህን ትንሽ ኀይል አጠናክር፤ በአምላኬ ፊት ሥራህን ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም። 3 እንግዲህ ምን ዐይነት ትምህርት እንደ ተቀበልክና እንደ ሰማህ አስታውስ፤ ጠብቀውም፤ ንስሓም ግባ፤ ባትነቃ ግን እንደ ሌባ በድንገት እመጣብሃለሁ፤ በምን ሰዓት ወደ አንተ እንደምመጣ አታውቅም። 4 ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፤ እነርሱ ነጭ ልብስ መልበስ የሚገባቸው ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ። 5 ድል የሚነሣ እንደ እነርሱ ነጭ ልብስ ይለብሳል፤ ስሙን በአባቴና በመላእክቱም ፊት አስታውቅለታለሁ፤ የሕያዋን ስም ከሚመዘገብበት ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስሰውም። 6 “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ! (6) የፊላደልፍያ ቤተ ክርስቲያን 7 “ለፊላደልፍያ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ “ይህ፥ ቅዱስና እውነተኛ ከሆነው፥ የዳዊት ቤት ቊልፍ ከያዘው የተነገረ ነው፤ እርሱ የሚከፍተውን ማንም አይዘጋውም፤ እርሱ የሚዘጋውንም ማንም አይከፍተውም። 8 ሥራህን ዐውቃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም ሊዘጋው የማይችለውን የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌልሃለሁ፤ ኀይልህ ትንሽ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ቃሌን ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድክም። 9 እንግዲህ፥ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉትን እነዚያን ከሰይጣን ማኅበር የሆኑትን ውሸታሞች መጥተው በእግርህ ሥር እንዲወድቁ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኩህም እንዲያውቁ አደርጋቸዋለሁ። 10 ትዕግሥተኛ ሁን ያልኩህን ቃሌን ስለ ጠበቅህ እኔም በምድር ላይ የሚኖሩትን ሊፈትናቸው በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው ከመከራ ሰዓት እጠብቅሃለሁ። 11 እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፤ አክሊልህን ማንም እንዳይወስድብህ ያለህን አጥብቀህ ያዝ። 12 ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፤ ይህችም ከተማ ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ናት፤ የእኔንም አዲስ ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። 13 “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ! (7) የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን 14 “ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ “ይህ፥ አሜን ከሆነው፥ ታማኝና እውነተኛ ምስክር ከሆነው፥ የእግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ መገኛ ከሆነው የተነገረ ነው፤ 15 ሥራህን ዐውቃለሁ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ አይደለህም፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ ብትሆን ኖሮ መልካም በሆነ ነበር! 16 ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ ሳትሆን ለብ ያልክ ስለ ሆንክ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው፤ 17 ‘እኔ ሀብታም ነኝ፤ ብዙ ሀብት አለኝ፤ የሚጐድለኝ ምንም የለም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፥ ምስኪን፥ ድኻ፥ ዕውርና የተራቈትህ መሆንክን አታውቅም፤ 18 ሀብታም ለመሆን በእሳት የተፈተነውን ወርቅ ከእኔ እንድትገዛ፥ የራቊትነትህን ኀፍረት ለመሸፈን ነጭ ልብስ እንድትለብስ፥ ለማየትም እንድችል የዐይን መድኃኒት ገዝተህ እንድትቀባ እመክርሃለሁ። 19 እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ፤ እቀጣቸዋለሁም፤ ስለዚህ ትጋ፤ ንስሓም ግባ፤ 20 እነሆ! እኔ በበር ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከእርሱ ጋር እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል፤ 21 እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋር በዙፋኑ ላይ እንደ ተቀመጥኩ እንዲሁም ድል የነሣ ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ። 22 “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!” |