መዝሙር 50 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእውነተኛ አምልኮ 1 ኀያሉ እግዚአብሔር አምላክ ይናገራል፤ ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያዋ ድረስ፥ በምድር ያለውን ሰው ሁሉ ይጠራል። 2 እግዚአብሔር በውበትዋ ፍጹም ከሆነችው ከጽዮን ከተማ የደመቀ ብርሃንን ያበራል። 3 አምላካችን ይመጣል፤ ዝም አይልም፤ የሚያቃጥል እሳት በፊቱ ነው፤ ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስም በዙሪያው ነው። 4 በሕዝቡ ላይ ሲፈርድ ሰማይንና ምድርን ለምስክርነት ይጠራል። 5 “በመሥዋዕት ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን የገቡትን ታማኞች አገልጋዮቼን ሰብስቡልኝ” ይላል። 6 እግዚአብሔር ብቸኛ ዳኛ ስለ ሆነ ሰማያት የእርሱን ፍትሕ ያውጃሉ። 7 ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ሕዝቤ ሆይ! ቃሌን ስማ፤ እስራኤል ሆይ! በአንተ ላይ እመሰክራለሁ፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። 8 ስለ መሥዋዕትህና ዘወትር ስለምታቀርበው የሚቃጠል መባ አልወቅስህም። 9 እንዲሁም ከበረትህ ኰርማዎችን፥ ከጒሮኖህም አውራ ፍየሎችን ልወስድብህ አልፈልግም። 10 በዱር ያሉ አራዊትና በሺህ የሚቈጠሩ ተራራዎች ላይ የሚሰማሩት የእንስሶች መንጋዎች የእኔ ናቸው። 11 የተራራ ወፎችን ሁሉ ዐውቃቸዋለሁ በመስክ የሚገኙ እንስሶች ሁሉ የእኔ ናቸው። 12 “ዓለምና በውስጥዋ ያለው ነገር ሁሉ የእኔ ስለ ሆነ የምራብ ብሆን እንኳ ለአንተ አልነግርህም ነበር። 13 የኰርማዎችን ሥጋ እበላለሁን? ወይስ የፍየሎችን ደም እጠጣለሁን? 14 የምስጋና መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርብ፤ ስእለትህንም ለልዑል ስጥ። 15 መከራ በሚደርስብህ ጊዜ ጥራኝ፤ እኔም አድንሃለሁ፤ አንተም ታከብረኛለህ።” 16 ኃጢአተኛውን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይለዋል፤ “ሕጌን ለማንበብ፥ ቃል ኪዳኔን በአንደበትህ ለመግለጽ ምን መብት አለህ? 17 ስሕተትህን መታረም ትጠላለህ፤ ቃሎቼንም ትንቃለህ። 18 ሌባውን ስታይ ከእርሱ ጋር ትወዳጃለህ፤ ከአመንዝራዎችም ጋር በመስማማት ትተባበራለህ። 19 “ክፉ ነገር ለመናገር ለአንደበትህ ነጻነትን ሰጠኸው፤ ንግግርህም ሁሉ ሽንገላ ብቻ ነው። 20 በወንድምህ ላይ ሁልጊዜ ክፉ ነገር ትናገራለህ፤ የእናትህንም ልጅ ታማለህ። 21 ይህን ስታደርግ ዝም በማለቴ እኔም እንደ አንተ የሆንኩ መሰለህን? አሁን ግን ፊት ለፊት ነገሩን ገልጬ እገሥጽሃለሁ። 22 “ስለዚህ እናንተ እኔን የምትንቁ ሁሉ ይህን አስተውሉ፤ አለበለዚያ አጠፋችኋለሁ፤ የሚያድናችሁም የለም። 23 የምስጋና መሥዋዕት የሚያቀርብልኝ ያከብረኛል፤ መንገዴን ለሚከተል አዳኝነቴን አሳየዋለሁ።” |