ኤፌሶን 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገር 1 እናንተ በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ምክንያት በመንፈሳዊ ኑሮአችሁ የሞታችሁ ነበራችሁ፤ 2 በዚያን ጊዜ የዚህን ዓለም ክፉ አካሄድ ትከተሉ ነበር፤ እንዲሁም በአየር ላይ ያሉትን የመናፍስት ኀይሎች ለሚገዛው ትታዘዙ ነበር፤ እርሱ በማይታዘዙት ሰዎች ላይ የሚሠራ ርኩሱ መንፈስ ነው። 3 እኛም ሁላችን ከዚህ በፊት በእነርሱ መካከል የሥጋችንን ፈቃድና የአእምሮአችንን ሐሳብ እየተከተልን በሥጋችን ምኞት እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም በተፈጥሮአችን በእግዚአብሔር ቊጣ ሥር ነበርን። 4 ነገር ግን የእግዚአብሔር ምሕረቱ ብዙ ከመሆኑና ለእኛም ያለው ፍቅር ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ 5 በበደላችን የሞትን ብንሆንም እንኳ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር እንድንኖር አድርጎናል፤ እናንተም የዳናችሁት በጸጋው ነው። 6 እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ አማካይነት ከእርሱው ጋር ከሞት አስነሥቶ በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። 7 ይህንንም ያደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ የገለጠውን ቸርነትና ወደር የሌለውን የጸጋውን ብልጽግና በሚመጡት ዘመናት ሊያሳየን ብሎ ነው። 8 እናንተ የዳናችሁት በእምነት አማካይነት በጸጋው ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ በእናንተ ሥራ የተገኘ አይደለም። 9 ማንም ሰው እንዳይመካ፥ የመዳን ጸጋ የተገኘው በሥራ አይደለም፤ 10 እኛ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጃቸውን መልካም ሥራዎች እንድንሠራ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንደገና የተፈጠርን የእግዚአብሔር ፍጡሮች ነን። በክርስቶስ የሚገኝ አንድነት 11 ስለዚህ እናንተ ቀድሞ በትውልዳችሁ አሕዛብ የነበራችሁ፥ አይሁድ በሰው እጅ በመገረዛቸው እየተመኩ እናንተን ያልተገረዙ እያሉ ይሰድቡአችሁ እንደ ነበር አስታውሱ። 12 እናንተ ከእስራኤል ማኅበረሰብ ግንኙነት የሌላችሁ፥ ለተስፋው ቃል ኪዳን እንግዶች የሆናችሁ፥ በዚህ ዓለምም አንዳች ተስፋ የሌላችሁ፥ ያለ እግዚአብሔር የምትኖሩ፥ ከክርስቶስም የተለያችሁ እንደ ነበራችሁ አስታውሱ። 13 አሁን ግን እናንተ ከዚህ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁት በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በእርሱ ደም ቀርባችኋል። 14 ለያይቶን የነበረውን የጥል ግድግዳ ያፈረሰና አይሁድንና አሕዛብን አንድ ያደረገ ሰላማችን ክርስቶስ ነው። 15 ከሁለቱ ሕዝቦች ከእርሱ ጋር የሚተባበር አንድ አዲስ ሕዝብን ለመፍጠር የሕግን ትእዛዞችና ደንቦች በሥጋው ሽሮ ሰላምን አደረገ። 16 በመስቀል ላይ በመሞትም ጠላትነትን አስወገደ፤ ሁለቱንም አንድ አካል አድርጎ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቃቸው። 17 መጥቶም ለእናንተ ርቃችሁ ለነበራችሁትና ቀርበው ለነበሩት ለአይሁድም የሰላምን የምሥራች ቃል ሰበከ። 18 በእርሱ አማካይነት ሁላችንም በአንድ መንፈስ ተመርተን ወደ አብ እንቀርባለን። 19 ስለዚህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጎችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ናችሁ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም። 20 በሐዋርያትና በነቢያትም መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑም ራስ ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 21 ሕንጻው በሙሉ በእርሱ ተገጣጥሞ የጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን ያድጋል። 22 እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚያድርበት ሕንጻ ለመሆን እናንተም አብራችሁ በክርስቶስ ትታነጻላችሁ። |