ኢሳይያስ 2:2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተሠራበት ተራራ ከሌሎች ተራራዎች ሁሉ በልጦ ይታያል፤ ከኰረብቶችም ሁሉ እጅግ ከፍ ይላል፤ የብዙ መንግሥታት ሕዝቦች ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በዘመኑም ፍጻሜ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዘመኑም ፍጻሜ፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጎርፋሉ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በኋላ ዘመን እንዲህ ይሆናል፤ የእግዚአብሔር ቤት በተራሮች ራስ ላይ ይታያል፤ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛቡም ሁሉ ወደ እርሱ ይመጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ። |
በሰሜን በኩል የምትገኘው፥ በከፍታዋና በውበትዋ የምትደነቀው፥ የጽዮን ተራራ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ነች፤ እርስዋም በምድር ላሉ ሁሉ ደስታን ታጐናጽፋለች።
የሠራዊት አምላክ በዚህች በጽዮን ተራራ ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ ታላቅ ግብዣ ያዘጋጃል፤ በግብዣውም ላይ ምርጥ የወይን ጠጅና፥ የተሟላ ምግብ ይዘጋጃል።
በዚያም ዘመን ትልቅ መለከት ይነፋል፤ በአሦር ምድር ጠፍተው የነበሩትና ወደ ግብጽ ተሰደው የነበሩት እስራኤላውያንም ተመልሰው በኢየሩሳሌም በሚገኘው በተቀደሰው ተራራ ላይ ይሰግዳሉ።
እናንተ ግን ደስ ይላችኋል፤ በተቀደሰ በዓል ምሽት እንደምትዘምሩት ትዘምራላችሁ፤ የእስራኤል አምባ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሲሄዱ ዋሽንት እየነፉ እንደሚዘምሩት ሰዎች ትደሰታላችሁ።
እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ “የያዕቆብን ነገዶች ክብር እንደገና ለማንሣትና የተረፉትን እስራኤላውያን ለመመለስ አገልጋዬ ሆነህ መሥራት ብቻ አይበቃም። ከዚህ የበለጠ ግን አዳኝነቴ እስከ ምድር ዳርቻ ይደርስ ዘንድ አንተ ለሕዝቦች ሁሉ ብርሃን እንድትሆን አደርግሃለሁ።” ይላል።
ለእነርሱ በቤተ መቅደሴና በግቢዬ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የተሻለ መታሰቢያ እንዲኖራቸው አደርጋለሁ፤ የማይረሳ ዘላቂ መታወቂያም እሰጣቸዋለሁ።”
“እነርሱን ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አምጥቼ በጸሎት ቤቴም ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ፤ በመሠዊያዬም ላይ የሚያቀርቡትን የሚቃጠልና ሌሎችን መሥዋዕቶች ሁሉ እቀበላለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ቤቴ የሕዝቦች ሁሉ ጸሎት ቤት ተብሎ ስለሚጠራ ነው።”
“እኔን እግዚአብሔርን ትታችሁ የተቀደሰ ተራራዬን በመርሳት ‘መልካም አጋጣሚ’ ለተባለ ጣዖትም ማእድ ታዘጋጃላችሁ፤ ‘ዕድል ፈንታ’ ለተባለ ጣዖትም ዋንጫችሁን በተደባለቀ የወይን ጠጅ ትሞላላችሁ።
ወንድሞቻችሁን ሁሉ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቅዱስ ተራራዬ በፈረሶች፥ በሠረገሎች፥ በጋሪዎች፥ በበቅሎዎችና በግመሎች አድርገው ከተለያዩ አገሮች ለእግዚአብሔር እንደ መባ ያመጡአቸዋል፤ እነርሱንም የሚያመጡአቸው እስራኤላውያን የእህል ቊርባንን በሥርዓት በነጻ ዕቃ ለእኔ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሚያቀርቡ አድርገው ነው፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
ከወር መባቻ እስከ ሌላ የወር መባቻ በዓልና ከሰንበት እስከሚቀጥለው ሰንበት ሕዝብ ሁሉ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ሊሰግዱልኝ ይመጣሉ”፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
እግዚአብሔር ሆይ! የምትጠብቀኝና ብርታትን የምትሰጠኝ አንተ ነህ፤ በመከራም ጊዜ መጠጊያ አምባዬ ነህ፤ ሕዝቦች ከምድር ዳርቻ ሁሉ ወደ አንተ መጥተው እንዲህ ይላሉ፦ “የቀድሞ አባቶቻችን ከሐሰተኞች አማልክት በቀር ምንም አልነበራቸውም፤ ጣዖቶቻቸው ሁሉ የማይጠቅሙ ከንቱዎች ነበሩ፤
“ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን የሞሬሼቱ ነቢይ ሚክያስ የሠራዊት አምላክ የተናገረውን የትንቢት ቃል ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ዐውጆ ነበር፦ ‘ጽዮን እንደ ማሳ ትታረሳለች፤ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤ ቤተ መቅደሱም የተሠራበት ኰረብታ ዳዋ ይበቅልበታል።’
በዚያን ዘመን ኢየሩሳሌም ራስዋ ‘የእግዚአብሔር ዙፋን’ ተብላ ትጠራለች፤ ሕዝብም ሁሉ እኔን ለማምለክ በዚያ ይሰበሰባሉ። ከዚያን በኋላ እልኸኛና የክፉ ሐሳብ ምንጭ የሆነውን ልባቸውን አይከተሉም።
ስለዚህም ተመልሰው መጥተው በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤ በምሰጣቸውም የእህል፥ የወይን ጠጅ፥ የወይራ ዘይት፥ የበግና የቀንድ ከብት በረከት ሁሉ ተድላ ደስታ ያደርጋሉ፤ በቂ ውሃ እንዳገኘች የተክል ቦታ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ ወዲያም አያዝኑም።
የባቢሎን ጣዖት የሆነውን ቤልን እቀጣለሁ፤ የተሰረቁ ዕቃዎቹንም ከእጁ አስጥላለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህም አሕዛብ አይሰግዱለትም።” “የባቢሎን ቅጽሮች ወድቀዋል፤
በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ምድርን እንደሚሸፍን ደመና ትመጣባቸዋለህ፤ ጎግ ሆይ፥ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ እንድትመጣ አደርግሃለሁ፤ ይህንንም የማደርገው በአንተ አማካይነት ቅድስናዬን በፊታቸው በምገልጥበት ጊዜ ሕዝቦች እንዲያውቁኝ ነው።’ ”
በእግዚአብሔርም ራእይ ወስዶ በእስራኤል ምድር በአንድ ከፍተኛ ተራራ ላይ አኖረኝ፤ እዚያም አንድ ብዙ ቤቶች የተሠሩበትን ከተማ የሚመስል ከተራራው በስተደቡብ በኩል አየሁ።
እኔም የመጣሁት በወገኖችህ ላይ በመጨረሻው ዘመን የሚደርስባቸውን ነገር ላስረዳህ ነው፤ ስለዚህ ከዚህም በቀር ወደፊት የሚሆነውን ነገር የሚገልጥ ሌላ ራእይ አለ።”
ነገር ግን ምሥጢርን ሁሉ የሚገልጥ አንድ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱ ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ ለአንተ ገልጦልሃል፤ በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ ያየኸው ሕልምና በአእምሮህ የነበረው ራእይ የሚከተለው ነው።
ብረቱ፥ ሸክላው፥ ነሐሱ፥ ብሩና ወርቁ ሁሉ ወዲያውኑ ተንከታክቶ በበጋ ወራት በአውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅ ሆነ፤ ምንም ሳያስቀር ነፋስ ጠራርጎ ወሰደው፤ በምስሉ ላይ የወደቀው ድንጋይ ግን ምድርን ሁሉ እስኪሞላ ድረስ ከፍ ከፍ ብሎ ታላቅ ተራራ ሆነ።
የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ላይ ተፈንቅሎ በመውረድ ከብረት፥ ከነሐስ፥ ከሸክላ፥ ከብርና ከወርቅ የተሠራውን ምስል ያደቀቀውም ድንጋይ፥ ያ መንግሥት ነው፤ በዚህም ታላቁ አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ሁሉ አሳይቶሃል፤ እነሆ፥ ሕልሙ እውነት ነው፤ አስተማማኝ ትርጒሙም ይኸው ነው።”
ከዚህ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔርና ወደ ንጉሣቸው ወደ ዳዊት ይመለሳሉ፥ በኋለኛው ዘመን በፍርሃት ወደ እግዚአብሔር ይመጣሉ፤ በረከቱንም ይቀበላሉ።
በሰሜን ከጌባዕ አንሥቶ ኢየሩሳሌምን በደቡብ በኩል አልፎ እስከ ሪሞን ድረስ ያለው አውራጃ ደልዳላ ይሆናል፤ ኢየሩሳሌም በዙሪያዋ ካለው ምድር በላይ ከፍ ትላለች፤ ከተማይቱም ከብንያም በር አንሥቶ በቀድሞው በር አቅጣጫ እስከ ማእዘን በር እንዲሁም ከሐናንኤል ግንብ አንሥቶ እስከ ቤተ መንግሥቱ ወይን መጭመቂያው ድረስ ከፍ በማለት ጸንታ ትኖራለች።
በዚህ ዐይነት ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ለመስገድና የእርሱንም በረከት ያገኙ ዘንድ ለመጸለይ ብዙ ሰዎችና ታላላቅ ሕዝቦች ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ።
እኔ እንድኖርባት ወደ ተቀደሰችው ከተማዬ ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ፤ የታመነች ከተማ በመሆን ትታወቃለች፤ እኔ የሠራዊት አምላክ የምኖርበት ተራራ፥ የተቀደሰ ተራራ ተብሎ ይጠራል፤
በመጨረሻም በለዓም ባላቅን “እነሆ፥ እኔ ወደ ራሴ ሕዝብ ተመልሼ መሄዴ ነው፤ ነገር ግን ከመሄዴ በፊት የእስራኤል ሕዝብ ወደ ፊት በሕዝብህ ላይ የሚያደርጉትን በመግለጥ ላስጠነቅቅህ እወዳለሁ” ካለው በኋላ፥
‘እግዚአብሔር በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል፤ መንፈሴን በሰው ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጐልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ።
አሁን ግን በእነዚህ በኋለኞቹ ዘመናት ሁሉን ነገር ወራሽ ባደረገው በልጁ አማካይነት ለእኛ ተናገረን፤ ዓለምንም ሁሉ የፈጠረው በእርሱ ነው።
ሰባተኛውም መልአክ እምቢልታውን ነፋ፤ በሰማይም “የዓለም መንግሥት የጌታ የአምላካችንና የመሲሑ ሆናለች፤ እርሱ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል፤” የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ።
ከዚህ በኋላ ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ የመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ተቀምጠው አየሁ፤ ስለ ኢየሱስ በመመስከራቸውና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሶች አየሁ፤ እነርሱ ለአውሬውና ለምስሉ ያልሰገዱ፥ ምልክቱንም በግንባራቸውም ሆነ በእጃቸው ላይ ያላደረጉ ናቸው፤ እነርሱ ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ነገሡ።