መዝሙር 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበእግዚአብሔር የተመረጠ ንጉሥ 1 አሕዛብ ስለምን ያሤራሉ? ሕዝቦችስ ለምን በከንቱ ያድማሉ? 2 እግዚአብሔርንና መሲሑን ለመቃወም የዓለም ነገሥታት ተነሣሡ፤ ሹሞቻቸውም ከእነርሱ ጋር ተባበሩ። 3 “እግር ብረታቸውን ከእግራችን እንቊረጥ፤ ገመዳቸውን በጥሰን እንጣል” አሉ። 4 በሰማይ ዙፋኑ ላይ የሚቀመጠው ይስቅባቸዋል፤ በከንቱ ሐሳባቸውም ጌታ ያፌዝባቸዋል። 5 ከዚህ በኋላ በቊጣው ይገሥጻቸዋል፤ በመዓቱም ያስፈራራቸዋል። 6 “በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ ንጉሤን ሾምኩ” ይላቸዋል። 7 “የእግዚአብሔርን ዐዋጅ ዐውጃለሁ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ፤ 8 ለምነኝ፤ አሕዛብ ሁሉ እንዲገዙልህ አደርጋለሁ፤ ምድርም በሙሉ የአንተ ርስት ትሆናለች። 9 በብረት በትር ትሰብራቸዋለህ፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ቀጥቅጠህ ታደቃቸዋለህ’ ” አለኝ። 10 እናንተ ነገሥታት አስተውሉ፤ እናንተ የምድር ገዢዎች ተጠንቀቁ። 11 እግዚአብሔርን በፍርሃት አገልግሉት፤ በመንቀጥቀጥም ተገዙለት። 12 ቊጣው በቅጽበት ስለሚነድ በእናንተ ላይ ተቈጥቶ እንዳያጠፋችሁ በመንቀጥቀጥ ስገዱለት እርሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ የተባረኩ ናቸው። |