Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 30 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠው ተስፋ

1 ወደ ኤርምያስ የመጣው የእስራኤል አምላክ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦

2 “የነገርኩህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፍ።

3 ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን እንደገና የምመልስበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ ለቀድሞ አባቶቻቸው ወደ ሰጠኋቸው ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም እንደገና የራሳቸው ያደርጓታል። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

4 እግዚአብሔር ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ የሚለው ይህ ነው፤

5 “የሰላም ሳይሆን የመሸበርና የመርበድበድ ድምፅ ይሰማል፤

6 እስቲ ቆም ብላችሁ አስቡ! ወንድ አምጦ ልጅን መውለድ ይችላልን? ታዲያ ወንድ ሁሉ እንደ ወላድ ሴት በእጆቹ ወገቡን ይዞ የማየው ስለምንድን ነው? የእያንዳንዱስ ሰው ፊት ስለምን ገረጣ?

7 ያ ቀን ምንኛ አስጨናቂ ይሆናል! እርሱን የመሰለ ቀን የለም፤ ለያዕቆብ ልጆች ለእስራኤላውያን የመከራ ዘመን ይሆናል፤ ሆኖም እነርሱ ከዚያ ሁሉ ጭንቀት ይድናሉ።”

8 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ያ ቀን በደረሰ ጊዜ በሕዝቤ ጫንቃ ላይ የተጫነውን የአገዛዝ ቀንበር እሰብራለሁ፤ ሰንሰለታቸውንም አስወግዳለሁ፤ ከዚያን በኋላ ለባዕዳን ሕዝብ ባሪያዎች አይሆኑም፤

9 በዚህ ፈንታ ለእኔ ለአምላካቸው ይሰግዱልኛል፤ እኔ በዙፋን ላይ ለማስቀምጥላቸው የዳዊት ዘር ለሆነውም ንጉሣቸው ይገዛሉ።

10 የአገልጋዬ የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ፥ አትፍሩ ተስፋም አትቊረጡ፤ ከሩቅ አገር በደኅና እመልሳችኋለሁ፤ ልጆቻችሁንም ተማርከው ከተወሰዱበት አገር እመልሳቸዋለሁ፤ እስራኤላውያን እንደገና ሰላም አግኝተው ያለ ስጋት ይኖራሉ።

11 እኔ ራሴ ከእናንተ ጋር በመሆን አድናችኋለሁ፤ እናንተን የበተንኩባቸውን አሕዛብ ሁሉ እደመስሳለሁ፤ እናንተን ግን አላጠፋም፤ ሆኖም ያለ ቅጣት አልተዋችሁም፤ የምቀጣችሁ ግን እንደ ጥፋታችሁ ነው፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

12 እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ይላል፦ “ቊስላችሁ የማይፈወስ፥ ጒዳታችሁም ከባድ ነው።

13 ለእናንተ የሚከራከርላችሁ የለም፤ ለቊስላችሁም መድኃኒት አይገኝም፤ እናንተም አትድኑም።

14 ወዳጆቻችሁ ሁሉ ረስተዋችኋል፤ እነርሱ እናንተን አይፈልጉአችሁም፤ ኃጢአታችሁ የበዛ፥ ክፋታችሁም እጅግ ከፍ ያለ ስለ ሆነ፥ እንደ ጠላት መታኋችሁ፤ ያለ ርኅራኄም ቀጣኋችሁ።

15 ኃጢአታችሁ የበዛ ክፋታችሁም እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ ፈውስ ስለማይገኝላችሁ፥ ስለ ቊስላችሁ ሕመም አታጒረምርሙ፤ እኔ እንዲህ አድርጌ እቀጣችኋለሁ።

16 ነገር ግን እናንተን ግጠው የበሉአችሁ ሁሉ እነርሱም በፈንታቸው ተግጠው ይበላሉ፤ ጠላቶቻችሁ ሁሉ ተማርከው ይወሰዳሉ፤ ሲዘርፉአችሁ የነበሩት ሁሉ ይዘረፋሉ። የቀሙአችሁ ሁሉ እነርሱም በተራቸው እንዲቀሙ አደርጋለሁ።

17 ጠላቶቻችሁ ‘ጽዮን እንደ ተጣለች መቅረትዋ ነው፤ የሚጠነቀቅላትም የለም’ ቢሉም፥ እኔ ጤንነታችሁን እንደገና እመልስላችኋለሁ፤ ቊስላችሁንም እፈውሳለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

18 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤልን ልጆች ቤት መልሼ እሠራለሁ፤ ለያንዳንዱም ቤተሰብ ምሕረቴን እልካለሁ፤ የኢየሩሳሌም ከተማ እንደገና ትሠራለች፤ ቤተ መንግሥቱም በድሮ ቦታ ተመልሶ ይታነጻል።

19 በዚያም የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ፥ የምስጋና መዝሙር ይዘምራሉ፤ በደስታም እልል ይላሉ፤ አበዛቸዋለሁ እንጂ ቊጥራቸው አይቀንስም፤ ክብር እንዲኖራቸው አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ አይናቁም።

20 ልጆቻቸው እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው ተፈርተው ይኖራሉ፤ ይህም ማኅበራዊ ኑሮአቸው በፊቴ የጸና ይሆናል፤ ሲጨቊኑአቸው የነበሩትንም ሁሉ እቀጣለሁ።

21 የራሳቸው ወገን ከመካከላቸው ተነሥቶ መሪአቸው ይሆናል፤ እኔ ራሴ ስለማመጣው እርሱ ወደ እኔ ይቀርባል፤ አለበለዚያማ ማን ደፍሮ ሊቀርብ ይችላል?

22 እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

23 እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለው የእግዚአብሔር ቊጣ እንደ ኀይለኛ ነፋስ እየተገለባበጠ በክፉዎች ራስ ላይ ይወርዳል።

24 ኀይለኛው የእግዚአብሔር ቊጣ ሊያደርገው ያቀደውንም ነገር ሳይፈጽም አይመለስም፤ ጊዜው ሲደርስ ሕዝቡ ራሳቸው ይህን ሁሉ በግልጥ ይረዱታል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos