ዳንኤል 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዳንኤል በጤግሮስ ወንዝ አጠገብ ያየው ራእይ 1 የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ብልጣሶር ለተባለው ለዳንኤል ሌላ ራእይ ተገለጠለት፤ በራእዩም የተነገረው ቃል እውነት ነው፤ ነገር ግን ለማስተዋል እጅግ ከባድ ከመሆኑ የተነሣ ትርጒሙ በራእይ ተገለጠለት። 2 በዚያን ጊዜ እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ በሐዘን ላይ ነበርኩ። 3 ሥጋም ሆነ ሌላ ጥሩ ምግብ አልተመገብኩም፤ የወይን ጠጅም ፈጽሞ አልቀመስኩም፤ ሦስቱ ሳምንቶች እስኪያልፉ ድረስ ራሴን ቅባት አልተቀባሁም። 4 የዓመቱ የመጀመሪያ ወር በገባ በሃያ አራተኛው ቀን በታላቁ በጤግሮስ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። 5 ቀና ብዬ ስመለከት ቀጭን ሐር የለበሰና በወገቡም የወርቅ ቀበቶ የታጠቀ አንድ ሰው አየሁ። 6 የዚህ ሰው አካል እንደ ዕንቊ ያበራ ነበር፤ ፊቱም እንደ መብረቅ ያንጸባርቅ ነበር፤ ዐይኖቹም የእሳት ነበልባል ይመስሉ ነበር፤ እጆቹና እግሮቹ እንደ ተወለወለ ነሐስ ያበሩ ነበር፤ ድምፁም የብዙ ሰዎችን ድምፅ ያኽል ያስተጋባ ነበር። 7 ራእዩን ያየሁ እኔ ዳንኤል ብቻ ነበርኩ፤ አብረውኝ የነበሩት ሰዎች ግን ምንም ነገር አላዩም፤ ሆኖም እጅግ ስለ ደነገጡ ሮጠው ተደበቁ። 8 እኔም ይህን አስደናቂ ራእይ እየተመለከትኩ ብቻዬን ቀረሁ፤ የነበረኝን ኀይል ሁሉ በማጣት ደክሜ ነበር፤ ፊቴም በጣም ገረጣ። 9 የሰውዬውን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ በመደንገጥ ኅሊናዬን ስቼ በመሬት ላይ ወደቅኹ፤ በግንባሬም እንደ ተደፋሁ ቀረሁ። 10 ከዚያ በኋላ አንዳች እጅ ዳሰሰኝ፤ ገና እየተንቀጠቀጥኩ ስለ ነበር ደግፎ በእጄና በጒልበቴ እንድቆም አደረገኝ። 11 መልአኩም “በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተወደድክ ዳንኤል ሆይ! እነሆ፥ እኔ ወደ አንተ ተልኬ መጥቼአለሁ፤ ባለህበት ቀጥ ብለህ ቁም፤ የምነግርህንም በጥንቃቄ አስተውል!” አለኝ። ይህን በነገረኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥኩ ቆምኩ። 12 ደግሞም እንዲህ አለኝ፦ “ዳንኤል ሆይ! አትፍራ! ማስተዋልን ለማግኘት ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ለማዋረድ ከወሰንክበት ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ ጸሎትህ ተሰምቶአል፤ እኔም ተልኬ ወደ አንተ የመጣሁት ጸሎትህ መልስ ከማግኘቱ የተነሣ ነው። 13 የፋርስ መንግሥት አለቃ የሆነው መንፈስ ኻያ አንድ ቀን ሙሉ ተቃወመኝ፤ በፋርስ ብቸኛ መሆኔን አይቶ ከመላእክት አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ። 14 እኔም የመጣሁት በወገኖችህ ላይ በመጨረሻው ዘመን የሚደርስባቸውን ነገር ላስረዳህ ነው፤ ስለዚህ ከዚህም በቀር ወደፊት የሚሆነውን ነገር የሚገልጥ ሌላ ራእይ አለ።” 15 ይህንንም በነገረኝ ጊዜ የምናገረውን አጥቼ ወደ መሬት አቀርቅሬ መናገር አቃተኝ። 16 ከዚህ በኋላ ሰውን የሚመስለው እጁን ዘርግቶ ከንፈሮቼን ዳሰሰ፤ እኔም እንዲህ አልኩት፦ “ጌታዬ ሆይ! ይህ ራእይ በጣም ስላሳመመኝ ሰውነቴ ዛለ። 17 እኔ አገልጋይህ ስሆን ከአንተ ከጌታዬ ጋር መነጋገር እንዴት እችላለሁ? መተንፈስ እስከሚያቅተኝ ድረስ እጅግ ደክሜአለሁ።” 18 ያ ሰው የሚመስለው መልአክ እንደገና በዳሰሰኝ ጊዜ ብርታት አገኘሁ። 19 እርሱም “አንተ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደድክ ሰው ሆይ! መልካም ይሆንልሃል፤ አትፍራ! አይዞህ በርታ!” አለኝ። እርሱም በተናገረኝ ጊዜ ብርታት አገኘሁና “ጌታዬ ሆይ፥ ብርታት ስለ ሰጠኸኝ እነሆ፥ ተናገር” አልኩት። 20-21 እንደገናም እንዲህ አለኝ፦ “ወደ አንተ የመጣሁት ለምን እንደ ሆነ ታውቃለህን? እኔ ወደ አንተ የመጣሁት በእውነት መጽሐፍ የተጻፈውን ልገልጥልህ ነው፤ አሁንም ተመልሼ የፋርስ መንግሥት አለቃ ከሆነው መንፈስ ጋር ጦርነት አደርጋለሁ፤ እኔ ከሄድኩ በኋላ የግሪክ መንግሥት አለቃ የሆነው መንፈስ ይመጣል፤ ይሁን እንጂ የእስራኤል ጠባቂ መልአክ ከሆነው ከሚካኤል በቀር እኔን የሚረዳ የለም። |