ኤርምያስ 48 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሞአብ መጥፋት 1 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ ሞአብ የሚለው ይህ ነው፦ “ነቦ ስለምትደመሰስ፥ ለነቦ ሕዝብ ወዮላቸው! ቂርያታይም በጠላት እጅ ትወድቃለች፤ ብርቱ የሆኑ ምሽጎችዋም ይደመሰሳሉ፤ ሕዝብዋም በዕፍረት ላይ ይወድቃሉ። 2 የሞአብ ክብር ያልፋል፤ ሰዎች ሐሴቦንን ለመጣል ያሤራሉ፤ ‘ኑ ከእንግዲህ በሕዝብነት እንዳትታወቅ እናጥፋት’ ይላሉ፤ እናንተም የማድሜን ሰዎች ሆይ! ሰይፍ ስለሚያሳድዳችሁ ጸጥ እንድትሉ ትደረጋላችሁ። 3 በሖሮናይም ላይ በሚደርሰው ውድመትና ጥፋት የሚሰማውን ጩኸት አድምጡ። 4 “ሞአብ ተደምስሳለች፤ ልጆችዋም ጩኸትን ያሰማሉ። 5 ወደ ሉሒት ሲወጡ ምርር ብለው እያለቀሱ ይወጣሉ፤ ወደ ሖሮናይም ቊልቊለት ሲወርዱ በውድመቱ ምክንያት የጭንቀት ድምፅ ያሰማሉ። 6 እርስ በርሳቸውም ‘ሕይወታችሁን ለማትረፍ በፍጥነት ሩጡ! በበረሓም እንደሚኖር የሜዳ አህያ ብረሩ!’ ይባባላሉ። 7 “የሞአብ ሕዝብ ሆይ! በኀይላችሁና በሀብታችሁ ብዛት ተማምናችሁ ነበር፤ አሁን ግን እነሆ እናንተ ራሳችሁ እንኳ ትማረካላችሁ፤ ከሞሽ ተብሎ የሚጠራው ጣዖት ከልዑላን መሳፍንትና ከካህናቱ ጋር ተማርኮ ይወሰዳል። 8 እግዚአብሔር እንደ ተናገረ አጥፊው በከተሞች ሁሉ ላይ ይመጣል፤ አንድም የሚያመልጥ ከተማ የለም። ሸለቆውንና ሜዳውን እንዳልነበሩ ያደርጋል። 9 ጠፍ እንድትሆን በሞአብ አገር ላይ ጨው ነስንሱባት፤ ከተሞችዋም ሰው የማይኖርባቸው ባድማ ይሆናሉ።” 10 ቸል በማለት የእግዚአብሔርን ሥራ ከልብ የማይፈጽም ሰው የተረገመ ይሁን! እግዚአብሔር በሚያዘውም ጊዜ ሰይፉን ከደም የሚከለክል የተረገመ ይሁን! የሞአብ ከተሞች መደምሰሳቸው 11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከዕቃ ወደ ዕቃ ሳይገለባበጥ ከአተላው ጋር አብሮ የቈየ የወይን ጠጅ ጣዕሙ እንዳለ ይቈያል፤ መዓዛውም አይለወጥም፤ እንደዚሁም የሞአብ ሕዝብ አገራቸው ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ሳይታወኩ ኖረዋል፤ ተማርከውም አይታወቁም። 12 አንድ ሰው የወይን ጠጅን ከአንድ ዕቃ ወደ ሌላ ዕቃ ገልብጦ ባዶውን ዕቃ እንደሚሰብር፥ እኔም ሞአብን የሚያወድምና ሕዝብዋን የሚያፈልስ ሰው የምልክበት ጊዜ በእርግጥ ተቃርቦአል። 13 እስራኤላውያን ይታመኑበት በነበረው በቤቴል በተተከለው ጣዖት እንዳፈሩ፥ ሞአባውያንም ከሞሽ ተብሎ በሚጠራው ጣዖታቸው ያፍራሉ።” 14 “የሞአብ ሰዎች ሆይ! ‘እኛ ተዋጊ አርበኞችና በጦርነት የተፈተንን ወታደሮች ነን’ ብላችሁ ስለምን ትመካላችሁ? አጥፊው መጥቶአል፤ 15 ሞአብና ከተሞችዋማ እነሆ ተደምስሰዋል፤ የሚያስደስቱ ወጣቶችዋም ለመታረድ ወርደዋል። እኔ ንጉሡ ይህን ተናግሬአለሁ ስሜም ‘የሠራዊት አምላክ’ ነው። 16 የሞአብ ጥፋት ተቃርቦአል፤ የመፈራረሻዋም ጊዜ ፈጥኖ ይደርሳል። 17 “ዝናዋን የምታውቁና በአቅራቢያዋ የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ‘የሥልጣን ምልክት የሆነው የተከበረው ኀይልዋ፥ በትረ መንግሥትዋ እንዴት ተሰበረ’ በማለት ዋይ! ብላችሁ አልቅሱላት! 18 ምሽጎችዋም ፍርስራሽ ሆነው እንዲቀሩ የሚያደርግ ሞአብን የሚደመስሳት እነሆ እዚህ ስለ አለ፥ በዲቦን ከተማ የምትኖሩ ሁሉ ከክብር ቦታችሁ ወርዳችሁ በምድር ትቢያ ላይ ተቀመጡ፤ 19 በዓሮዔር የምትኖሩ ሁሉ፥ በመንገድ ዳር ቆማችሁ ተጠባበቁ፤ የሚሸሹትን ወንዶችና የሚያመልጡትን ሴቶች ሁሉ በመጠየቅ፥ የሆነውን ነገር ሁሉ ዕወቁ። 20 ሞአብ ፈራርሳ በዕፍረት ስለ ወደቀች ዋይ ዋይ ብላችሁ አልቅሱላት፤ ባድማ መሆንዋንም በአርኖን ወንዝ አጠገብ ተናገሩ። 21-24 “በደጋማ ቦታ በተቈረቈሩት፥ ሖሎን፥ ያህጻ፥ ሜፋዓት፥ ዲቦን፥ ነቦ፥ ቤትዲብላታይም፥ ቂርያታይም፥ ቤትጋሙል፥ ቤትመዖን፥ ቀሪዮትና ቦጽራ ተብለው በሚጠሩትና፥ በሩቅም በቅርብም በሚገኙት በሞአብ ከተሞች ሁሉ ላይ የቅጣት ፍርድ መጥቶአል፤ 25 የሞአብ መከላከያ ኀይል ተሰብሮአል፤ ሥልጣንዋም ተገፎአል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” የሞአብ መዋረድ 26 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በእኔ ላይ ስለ ታበየች ሞአብን አጠጥታችሁ አስክሩአት፤ በትፋቷ ላይ ትንከባለል፤ ሕዝብም ይሳቅባት፤ 27 ሞአብ ሆይ! እስራኤል ከሌቦች ጋር የተያዘች ባትሆንም እንኳ አንቺ እርስዋን መሳለቂያ አድርገሽ ስለ እርስዋ በተናገርሽ ቊጥር ራስሽን ትነቀንቂ ነበር። 28 “የሞአብ ነዋሪዎች ሆይ! ከተሞቻችሁን ለቃችሁ በገደል አፋፍ ጎጆዋን እንደምትሠራ እንደ ርግብ በመሆን በቋጥኞች መካከል ኑሩ። 29 ሞአብ በከፍተኛ ኲራት፥ ራሷን ከፍ ከፍ በማድረግ በትዕቢተኛነት፥ በመጀነንና በልበ ደንዳናነት የተወጠረች መሆንዋን ሰምቼአለሁ። 30 እኔ የእርስዋን ዕብሪተኛነት ዐውቃለሁ፤ ፉከራዋና ሥራዋ ከንቱ ናቸው። 31 ለሞአብ ዋይ፥ ዋይ እልላታለሁ፤ ለሞአባውያን ሁሉ ድምፄን ከፍ ከፍ አድርጌ እጮኻለሁ፥ ለቂርሔሬስ ሰዎች የሐዘን ለቅሶ አለቅሳለሁ። 32 ለያዕዜር ሕዝብ ከማለቅሰው ይበልጥ ለሲብማ ሕዝብ እየጮኽኩ አለቅሳለሁ፤ የሲብማ ከተማ ሆይ! እንቺ ቅርንጫፎችዋ ሙት ባሕርን አልፎ እስከ ያዜር እንደሚደርስ የወይን ተክል ነሽ፤ ነገር ግን በጐመራው ፍሬሽና በወይን ዘለላሽ ላይ አጥፊው መጥቷል። 33 ደስታና ሐሴት ለምለም ከሆነችው ከሞአብ ምድር ተወስደዋል፤ ከወይን መጭመቂያዎች ሁሉ የወይን ጠጅ እንዳይፈስስ አድርጌአለሁ፤ የደስታ ድምፅ እያሰማ የሚጨምቅ የለም፤ ድምፅ የሚሰማ ቢሆንም የሚሰማው ድምፅ ግን የደስታ ድምፅ አይደለም። 34 “የሐሴቦንና የዔልዓሌ ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይጮኻሉ፤ ጩኸታቸውም እስከ ያሀጽ ተሰምቶአል፤ ከጾዓር እስከ ሖሮናይምና ዔግላት ሺሊሺያ ድረስ ተሰምቶአል፤ የኒምሪም ውሃ እንኳ ደርቆአል። 35 በሞአብ መስገጃ ቦታዎች መሥዋዕት የሚያቀርቡትንና ለአማልክታቸው የሚያጥኑትን አጠፋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር። 36 “በሞአብና በቂርሔሬስ የሚኖሩ ሕዝብ የነበራቸውን ሁሉ በማጣታቸው ምክንያት በዋሽንት ተመርተው እንደሚያለቅሱ ሰዎች አለቅስላቸዋለሁ። 37 የሞአብ ሕዝብ በሰገነቶች ላይና በመንገዶች ላይ ሆነው ያለቅሳሉ፤ ወንዶች ጢማቸውን ይቈረጣሉ፤ ሕዝቡም ራሳቸውን ይላጫሉ፤ እጆቻቸውን ይበጣሉ፤ ማቅም ይለብሳሉ። 38 ሞአብን እንደማይፈለግ ዕቃ ስለ ሰበርኳት በቤት ሰገነቶች ላይና በሕዝብ አደባባዮች ሁሉ ከለቅሶ በቀር ሌላ የሚሰማ ነገር የለም። 39 በሞአብ ላይ ምን ዐይነት አስደንጋጭ ሁናቴ ደርሶ ነው የምታለቅሰው? እንዴትስ በዕፍረት ጀርባዋን ትሰጣለች? ስለዚህም ለጐረቤቶችዋ ሁሉ መሳለቂያና አስደንጋጭ ሆናለች።” 40 ክንፉን ዘርግቶ ወደ ታች እንደሚወረወር ንስር በሞአብ ላይ የሚያንዣብብ ጠላት መምጣቱን እግዚአብሔር ተናገረ፤ 41 ከተሞችና ምሽጎች ሁሉ ይያዛሉ፤ በዚያን ጊዜ የሞአብ ወታደሮች በምጥ እንደ ተያዘች ሴት ሆነው በፍርሃት ይጨነቃሉ፤ 42 ሞአብ በእኔ ላይ ስለ ታበየች ትደመሰሳለች፤ ከእንግዲህ ወዲህ በመንግሥትነት አትታወቅም። 43 የሞአብ ሕዝብ ሆይ፥ “ሽብር፥ የሚያሰናክል ጒድጓድና ወጥመድ ይጠብቃችኋል፤” ይላል እግዚአብሔር። 44 “ከሽብር የሚያመልጠው፥ ጒድጓድ ውስጥ ይገባል፤ ከጒድጓድ ዘሎ የሚወጣውም ሁሉ በወጥመድ ይያዛል፤ ሞአብን የምቀጣበትን ቀን አመጣባታለሁ” ይላል እግዚአብሔር። 45 በሽሽት የደከሙ ስደተኞች በሐሴቦን ጥላ ሥር ተጠልለዋል፤ ይህም የሆነው እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሲሆን ቤቶች ወጥቶ የሞአብን ግንባር ቀደም ሠራዊትና ደጋፊ መሪዎችዋን አቃጥሎአል። 46 ለሞአብ ሕዝብ ወዮላችሁ! ካሞሽ ለተባለው ጣዖት የሚሰግዱ ሕዝብ ተደመሰሱ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም ተማርከው ተወሰዱ። 47 “ሆኖም የሞአብን ንብረት የምመልስበት ጊዜ ይመጣል፤” ይላል እግዚአብሔር፤ ስለ ሞአብ የተወሰነው ፍርድ እዚህ ላይ ይጠናቀቃል። |