Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 49 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ያዕቆብ ልጆቹን ሲመርቅ የተናገረው ቃል

1 ያዕቆብ ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአንድነት ተሰብሰቡና ወደ ፊት የሚገጥማችሁን ነገር ልንገራችሁ፤

2 እናንተ የያዕቆብ ልጆች፥ በአንድነት ተሰብስባችሁ ስሙ፤ አባታችሁ እስራኤል የሚነግራችሁንም አድምጡ።

3 “ሮቤል፥ ኀይልና የጐልማሳነት ብርታት በነበረኝ ጊዜ፥ የወለድኩህ የበኲር ልጄ ነህ። ከልጆቼ ሁሉ በክብርና በኀይል የምትበልጥ አንተ ነህ።

4 ይሁን እንጂ እንደ ውሃ የምትዋልል ስለ ሆንክ፥ የበላይ አለቅነት ለአንተ አይገባም፤ ወደ አባትህ አልጋ ወጥተሃል፤ የአባትህንም ቁባት ደፍረሃል።

5 “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው፤ ዐመፅ ለመፈጸም የጦር መሣሪያቸውን ያነሣሉ።

6 እነርሱ በቊጣቸው ብዙ ወንዶችን ስለ ገደሉ፥ ከንቱ ምኞታቸውን ለማርካት ብዙ ኰርማዎችን ስለ ሰባበሩ፥ በእነርሱ ምክር አልገባም፤ የጉባኤውም ተካፋይ አልሆንም።

7 እጅግ አስፈሪ የሆነ ቊጣቸው፥ እጅግ ጨካኝ የሆነ መዓታቸው፥ የተረገመ ይሁን። በእስራኤል ምድር ሁሉ እበታትናቸዋለሁ፤ በሕዝቡም መካከል እከፋፍላቸዋለሁ።

8 “ይሁዳ፥ ወንድሞችህ ያመሰግኑሃል፤ እጅህ በጠላቶችህ አንገት ላይ ይበረታል፤ ወንድሞችህ በፊትህ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እጅ ይነሡሃል።

9 ይሁዳ እንደ ደቦል አንበሳ ነው፤ ልጄ መብል የሚሆነውን አድኖ፥ ወደ ዋሻው ይመለሳል፤ እንደ አንበሳ ተዝናንቶ ይተኛል፤ ሊቀሰቅሰው የሚደፍር ማነው?

10 ‘ሴሎ’ ተብሎ የሚጠራው፥ ሕዝቦች ሁሉ የሚታዘዙለትና ለዘለዓለም የሚነግሠው እስኪመጣ ድረስ፥ በትረ መንግሥት (የገዢነት ሥልጣን) ከይሁዳ እጅ አይወጣም።

11 አህያውን በወይን ግንድ ላይ፥ ውርንጫውን በወይን ሐረግ ላይ ያስራል፤ ልብሱን በወይን ጠጅ፥ መጐናጸፊያውን እንደ ደም በቀላ የወይን ጭማቂ ያጥባል።

12 ዐይኖቹ ከወይን ጠጅ ይልቅ ይቀላሉ፤ ጥርሶቹ ከወተት ይልቅ ይነጣሉ።

13 “ዛብሎን በባሕር ዳር ይኖራል፤ ወደቡም የመርከቦች ማረፊያ ይሆናል፤ የመኖሪያውም ወሰን እስከ ሲዶና ይደርሳል።

14 “ይሳኮር በበጎች መካከል እንደሚተኛ ብርቱ አህያ ነው።

15 ነገር ግን ማረፊያው መልካም ምድሩም አስደሳች መሆኑን ባየ ጊዜ፥ ጭነቱን ለመሸከም ትከሻውን ዝቅ ያደርጋል፤ እንደ አገልጋይ ሆኖም ከባድ የጒልበት ሥራ ይሠራል።

16 “ዳን፥ ከእስራኤል ነገዶች አንዱ ለሆነው ሕዝብ ፈራጅ ይሆናል።

17 ፈረሰኛው ሰው ወደኋላው ይወድቅ ዘንድ፥ ዳን እንደ ነዳፊ እባብ ሆኖ፥ በመተላለፊያው መንገድ ላይ የፈረሱን ሰኰና ይነክሳል።

18 “አምላክ ሆይ፥ አዳኝነትህን እጠባበቃለሁ።

19 “ጋድን ቀማኞች ያጠቁታል፤ እርሱም ዱካቸውን በመከተል መልሶ ያሳድዳቸዋል።

20 “አሴር ከምድሩ ብዙ ሀብት አግኝቶ ይበለጽጋል፤ በነገሥታት ፊት መቅረብ የሚችል ጥሩ ምግብ ያዘጋጃል።

21 “ንፍታሌም በነጻነት እየተዘዋወረች እንደምትኖር፥ ደስ የሚያሰኙ ግልገሎችን እንደምትወልድ ሚዳቋ ነው።

22 “ዮሴፍ፥ በውሃ ምንጭ አጠገብ ተተክሎ፥ ሐረጎቹ በግድግዳ ላይ እንደሚዘረጉ ፍሬያማ ዛፍ ነው።

23 ቀስተኞቹ በብርቱ ያጠቁታል፤ በቀስታቸውም እየነደፉ ያሳድዱታል።

24 ነገር ግን ብርቱ በሆነ በያዕቆብ አምላክ ኀይል፥ በእስራኤል እረኛና ጠባቂ ብርታት፥ የእርሱ ቀስት ጽኑ ይሆናል፤ ክንዱም ይበረታል።

25 የአባትህ አምላክ ይረዳሃል፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ከላይ ከሰማይ ዝናብን፥ ከምድርም ጥልቀት ውሃን በመስጠት ይባርክሃል፤ ብዙ ከብትና ብዙ ልጆችም ይሰጥሃል።

26 ከጥንት ጀምሮ ጸንተው ከሚኖሩት ተራራዎችና ዘለዓለማውያን ከሆኑት ኮረብታዎችም ከሚገኘው ደስ ከሚያሰኝ በረከት ሁሉ የአባትህ በረከት ይበልጣል። እንግዲህ ይህ ሁሉ በረከት በዮሴፍ ራስ ላይ ይሁን፤ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም በዮሴፍ አናት ላይ ይውረድ።

27 “ብንያም እንደ ነጣቂ ተኲላ ነው፤ በማለዳ ያደነውን ራሱ ይበላል፤ በምሽት ያደነውን ግን ያካፍላል።”

28 እንግዲህ እነዚህ ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው፤ አባታቸው በባረካቸው ጊዜ ለእያንዳንዱ ተስማሚ የሆነውን የበረከት ቃል የተናገረው በዚህ ሁኔታ ነበር።


የያዕቆብ መሞትና መቀበር

29 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልጆቹን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “እኔ በሞት ወደ ወገኖቼ የምሄድበት ጊዜ ደርሶአል፤ ስለዚህ በሒታዊው በዔፍሮን እርሻ ላይ ባለው ዋሻ ውስጥ ከአባቶቼ ጋር ቅበሩኝ፤

30 ይህም ዋሻ በከነዓን ምድር ከመምሬ በስተምሥራቅ በኩል በማክፌላ የሚገኘው ነው፤ አብርሃም ይህ ዋሻ የሚገኝበትን እርሻ ለመቃብር ቦታ የገዛው ከሒታዊው ከዔፍሮን ነው።

31 አብርሃምና ሚስቱ ሣራ፥ ይስሐቅና ሚስቱም ርብቃ የተቀበሩት እዚያ ነው፤ እኔም ልያን የቀበርኳት እዚያው ነው።

32 እርሻውና ዋሻው በአንድነት የተገዙት ከሒታውያን ነው፤ ስለዚህ እኔንም እዚያው ቅበሩኝ።”

33 ያዕቆብ ለልጆቹ ትእዛዝ መስጠቱን ካበቃ በኋላ፥ እግሮቹን በመኝታው ላይ ሰብሰብ አድርጎ ጋደም እንዳለ በሞት ወደ ወገኖቹ ተሰበሰበ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos