Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 26 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የኤርምያስ ለፍርድ መቅረብ

1-2 የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በይሁዳ እንደ ነገሠ ወዲያውኑ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቆመህ ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ ለስግደት ወደዚያ ለሚመጡት ሕዝብ እኔ ያዘዝኩህን ሁሉ አንድ ነገር እንኳ ሳታስቀር ንገራቸው።

3 ምናልባት ሕዝቡ አዳምጠው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ የሚመለሱም ከሆነ ከክፋታቸው ሁሉ የተነሣ በእነርሱ ላይ ላመጣ ያቀድኩትን ጥፋት እተዋለሁ።”

4 እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ተናገር አለኝ፦ “እኔ እግዚአብሔር የሰጠኋችሁን ሕግ ባትከተሉና ባትታዘዙኝ፥

5 እናንተ ባታዳምጡአቸውም እንኳ አገልጋዮቼን ነቢያትን ደጋግሜ ወደ እናንተ ልኬአለሁ፤

6 ባለመታዘዛችሁ የምትቀጥሉበት ከሆነ በሴሎ ያደረግኹትን ሁሉ በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ ደግሜ አደርጋለሁ፤ የዓለም ሕዝብ ሁሉ የዚህችን የከተማ ስም እንደ መራገሚያ ይቈጥራል።”

7 ካህናቱ፥ ነቢያቱና ሕዝቡም ሁሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ይህን ቃል ስናገር ሰምተውኛል፤

8 እግዚአብሔር እንድናገር ያዘዘኝን ሁሉ ተናግሬ እንደ ጨረስኩ በድንገት ያዙኝና “ሞት ይገባሃል!” ሲሉ ጮኹ፥

9 “ ‘ይህ ቤተ መቅደስ እንደ ሴሎ ይሆናል፥’ ብለህ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገርከው ለምንድን ነው? ደግሞስ ‘ይህች ከተማ ትጠፋለች፥ በውስጥዋም ነዋሪ አይገኝባትም’ ያልከውስ ስለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁ። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ በቤተ መቅደስ ተሰብስበው ዙሪያዬን ከበቡኝ።

10 የይሁዳ መሪዎችም የሆነውን ነገር በሰሙ ጊዜ ከቤተ መንግሥት ወጥተው ወደ ቤተ መቅደስ መጡ፤ በቤተ መቅደሱም በአዲሱ የቅጽር በር ስፍራቸውን ያዙ።

11 ካህናቱና ነቢያቱ ለመሪዎቹና ለሕዝቡ እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው የተናገረውን ሁሉ እናንተ ራሳችሁ ሰምታችሁታል፤ በከተማችን ላይ ክፉ የትንቢት ቃል በመናገሩ ሞት ይገባዋል።”

12 እኔም ኤርምያስ ለመሪዎቹና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አልኩ፦ “በዚህች ከተማና በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ ይህን እናንተ የሰማችሁትን ቃል እንዳውጅ የላከኝ እግዚአብሔር ነው።

13 አሁንም የአኗኗራችሁንና የሥራችሁን ሁኔታ ለውጣችሁ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይኖርባችኋል፤ ይህን ብታደርጉ በእናንተ ላይ ሊያመጣ ያቀደውን ጥፋት ይመልሰዋል።

14 ስለ እኔ ጉዳይ እንደ ሆነ እነሆ በእናንተ እጅ ነኝ፤ ትክክልና ቀና መስሎ የታያችሁን ሁሉ አድርጉብኝ፤

15 ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ በጥንቃቄ ልታረጋግጡ ይገባል፤ ይኸውም እኔን ብትገድሉኝ፥ እናንተና የዚህ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ ሁሉ ንጹሕ ሰው በመግደላችሁ በደለኞች ሆናችሁ ትገኛላችሁ፤ ይህን ማስጠንቀቂያ እንድሰጣችሁ ወደ እናንተ የላከኝ በእርግጥ ራሱ እግዚአብሔር ነው።”

16 ከዚህ በኋላ መሪዎቹና ሕዝቡ፦ “ይህ ሰው የተናገረን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ስለ ሆነ ሞት አይገባውም” ሲሉ ለካህናቱና ለነቢያቱ ተናገሩ።

17 ቀጥሎም ከሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ተነሥተው እዚያ ለተሰበሰበው ሕዝብ እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፦

18 “ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን የሞሬሼቱ ነቢይ ሚክያስ የሠራዊት አምላክ የተናገረውን የትንቢት ቃል ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ዐውጆ ነበር፦ ‘ጽዮን እንደ ማሳ ትታረሳለች፤ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤ ቤተ መቅደሱም የተሠራበት ኰረብታ ዳዋ ይበቅልበታል።’

19 ታዲያ ንጉሥ ሕዝቅያስና የይሁዳ ሕዝብ ሚክያስ እንዲገደል አደረጉን? አይደለም! ይልቁንም ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን በመፍራት ምሕረት እንዲያደርግለት ተማጠነ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ሊያመጣ ዐቅዶት የነበረውን መቅሠፍት መለሰ፤ እኛ ግን አሁን አሠቃቂ የሆነ መቅሠፍት በራሳችን ላይ ለማምጣት ተዘጋጅተናል።”

20 በቂርያትይዓሪም የሚኖር የሸማያ ልጅ ኡሪያ የተባለ ሌላም ሰው ነበር፤ ይህ ሰው ልክ እንደ ኤርምያስ በዚህች ከተማና በዚህች ምድር ላይ ጥፋት እንደሚመጣ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት ተናግሮ ነበር፤

21 ንጉሥ ኢዮአቄምና መኳንንቱ፥ እንዲሁም የጦር አዛዦቹ ኡሪያ የተናገረውን በሰሙ ጊዜ፥ ኡሪያ እንዲገደል ንጉሡ ፈለገ፤ ኡሪያ ግን ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ፈራ፤ ወደ ግብጽም ሸሽቶ አመለጠ፤

22 ይሁን እንጂ ንጉሥ ኢዮአቄም የዓክቦር ልጅ ኤልናታንና ሌሎችም ሰዎች ወደ ግብጽ ወርደው ኡሪያን ይዘው እንዲመጡ አዘዘ፤

23 እነርሱም ወደ ንጉሥ ኢዮአቄም ይዘውት መጡ፤ ንጉሡም ኡሪያ እንዲገደልና በሕዝብ መቃብር ስፍራ እንዲጣል አዘዘ።

24 እኔ ግን የሳፋን ልጅ አሒቃም ይከላከልልኝ ስለ ነበር ይገድሉኝ ዘንድ ለሕዝቡ ተላልፌ አልተሰጠሁም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos