ኤርምያስ 49 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ዐሞን የተነገረ ትንቢት 1 እግዚአብሔር ስለ ዐሞን እንዲህ ይላል፦ “እስራኤል ወንዶች ልጆች የሉትምን? ወራሾች የሉትምን? ታዲያ ሚልኮም የተባለውን ጣዖት የሚያመልኩ ወገኖች የጋድን ነገድ አስለቅቀው በከተሞቹ የሰፈሩት ለምንድን ነው? 2 ስለዚህ የአሞን ከተማ በሆነችው በራባ ላይ የጦርነት ክተት ጥሪ ድምፅ የማሰማበት ጊዜ ይመጣል፤ እርስዋ፥ በፍርስራሽ ክምር የተሞላች ባድማ ትሆናለች፤ መንደሮችዋም በእሳት ይቃጠላሉ፤ ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን አስቀድመው እነርሱን የበዘበዙአቸውን መልሰው ይበዘብዛሉ። 3 የዐይ ከተማ ስለ ፈረሰች አልቅሱ! በራባ ከተማ አካባቢ መንደሮች የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ጮክ ብላችሁ አልቅሱ! ሚልኮም የተባለው ጣዖት ከካህናቱና ከረዳቶቹ ጋር ተማርኮ የሄደ ስለ ሆነ ማቅ ለብሳችሁ በቅጥሮችዋ መካከል ወዲያና ወዲህ እያላችሁ አልቅሱ! 4 እየቀነሰ በሚሄደው ኀይላችሁ የምትመኩት ለምንድን ነው? እናንተ እምነተቢስ ሕዝብ ሆይ! ‘አደጋ የሚጥልብኝ ማነው?’ ብላችሁ በሀብታችሁ ክምችት ተመክታችኋል። 5 እኔ ከሁሉም አቅጣጫ ሽብር አመጣባችኋለሁ፤ ሁላችሁም ትሸሻላችሁ፤ ሁሉም ወደፊቱ ሸሽቶ ስለሚበታተን የሸሹትን ስደተኞች የሚሰበስብ አይገኝም። 6 ነገር ግን ከጊዜ በኋላ የአሞናውያንን ንብረት እመልሳለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” ስለ ኤዶም የተነገረ ቃል 7 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶም የተናገረው ይህ ነው፦ “የቴማን ከተማ ሕዝብ ከዚህ በፊት የነበራቸውን ጥበብ አጥተዋልን? አማካሪዎቻቸውስ ምክር መስጠት አቅቷቸዋልን? የነበራቸውስ ጥበብ የት ደረሰ? 8 የዔሳውን ዘር በምቀጣበት ጊዜ መከራን ስለማመጣባቸው፥ የደዳን ከተማ ሕዝብ ሆይ! ወደ ኋላ ተመልሳችሁ ሩጡ! በዋሻም ተሸሸጉ! 9 ሰዎች የወይን ዘለላ በሚለቅሙበት ጊዜ በወይኑ ተክል ላይ ጥቂት ቃርሚያ ይተዋሉ፤ ወንበዴዎችም በሌሊት በመጡ ጊዜ የሚፈልጉትን ያኽል ብቻ ይወስዳሉ፤ 10 እኔ ግን የዔሳውን ዘር በፍጹም አራቊታቸዋለሁ። የሚሸሸጉበትንም ስፍራ አጋልጣለሁ፤ ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ የሚሸሸጉበት ስፍራ ማግኘት አይችሉም፤ ልጆቻቸው፥ ዘመዶቻቸውና ጐረቤቶቻቸው ይጠፋሉ፤ እነርሱም አይኖሩም። 11 በመካከላችሁ ያሉትን አባቶቻቸውና እናቶቻቸው የሞቱባቸውን ልጆች ተዉአቸው እኔ በሕይወት አኖራቸዋለሁ። ባሎቻቸው የሞቱባቸውም ሴቶች በእኔ ይተማመኑ። 12 “እንግዲህ መቀጣት የማይገባቸው ሰዎች እንኳ የቅጣቱን ጽዋ ገፈት የሚቀምሱ ከሆነ እናንተ ያለ ቅጣት የምታመልጡ ይመስላችኋልን? አይደለም፤ እናንተም ከቅጣቱ ጽዋ መጠጣት አለባችሁ። 13 የቦጽራ ከተማ አስፈሪ ምድረ በዳ ሆና እንደምትቀር እኔ በራሴ ምዬአለሁ፤ ሕዝብ ሁሉ መቀለጃ ያደርጋታል፤ ስሟንም እንደ ርግማን ይቈጥሩታል። በአቅራቢያዋ ያሉ መንደሮች ሁሉ ለዘለዓለም ፍርስራሾች ሆነው ይቀራሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” 14 አንድ መልእክት ከእግዚአብሔር ሰምቼአለሁ፤ “በኤዶም ሕዝብ ላይ አደጋ ለመጣል ተሰብሰቡ! ለጦርነትም ተነሡ!” ብሎ የሚናገር መልእክተኛ ወደ ሕዝቦች ተልኮአል። 15 “አሁን እንግዲህ በመንግሥታት መካከል ታናሽ፥ በሰዎችም መካከል የተናቅሽ አደርግሻለሁ። 16 አለታማው ገደል ላይ የምትኖሪ፥ እስከ ተራራማው ጫፍ ድረስ የምትደርሽ ሆይ! ተፈሪነትሽና የልብሽ ኲራት አታለውሻል፤ ምንም እንኳ መኖሪያሽን እንደ ንስር ጎጆ ብታደርጊ እኔ ከዚያ ላይ አወርድሻለሁ ይላል እግዚአብሔር።” 17 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ኤዶም የምታስደነግጥ ትሆናለች፤ በዚያ በኩል ሲያልፍ የሚያያት ሁሉ ይደነግጣል፤ በደረሰባት ጥፋትም ይገረማል። 18 ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸው ከሚገኙ ከተሞች ጋር በተደመሰሱ ጊዜ የደረሰባቸው ጥፋት እንዲሁ በተመሳሳይ በኤዶምም ላይ ይደርሳል። ዳግመኛም በዚያ ሰፍሮ የሚኖር ከቶ አይገኝም። 19 አንበሳ ጥቅጥቅ ካለው ከዮርዳኖስ ጫካ ወጥቶ ለምለም ወደ ሆነው ወደ በጎች መሰማርያ መስክ እንደሚመጣ እኔም በድንገት መጥቼ የኤዶም መሪዎችን አባርራለሁ፤ ከዚህ በኋላ የምመርጠውን እሾማለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ሊጠይቀኝ የሚደፍር ማን ነው? በፊቴ ቆሞ የሚቋቋመኝስ መሪ ማን ነው? 20 ስለዚህም በኤዶም ሕዝብ ላይ ያቀድኩትንና በቴማን ከተማ ሕዝብ ላይ ላደርግ የፈለግኹትን ስሙ፤ ልጆቻቸው እንኳ እንደ በግ ግልገሎች እየተጐተቱ ይወሰዳሉ፤ በእነርሱም ምክንያት የሚያያቸው ሁሉ ይደነግጣል። 21 የኤዶም አወዳደቅ ዜና ሲሰማ ምድር ትናወጣለች፤ የድንጋጤውም ጩኸት ከዚያ አልፎ እስከ ቀይ ባሕር ይሰማል። 22 ጠላት በቦጽራ ላይ ክንፉን በስፋት ዘርግቶ ወደ ታች እንደሚወርድ ንስር በመሆን ጉብ ይልባታል፤ በዚያን ጊዜ የኤዶም ወታደሮች በምጥ ተይዛ በፍርሃት እንደምትጨነቅ ወላድ ሴት ይሆናሉ። ስለ ደማስቆ የተነገረ ትንቢት 23 “የሐማትና የአርፋድ ከተማ ነዋሪዎች የደማስቆን የጥፋት ወሬ ስለ ሰሙ ግራ ተጋቡ፤ ወደ ላይና ወደ ታች እንደሚናወጥ ባሕር የእነርሱም ልብ ተሸበረ። 24 የደማስቆ ሕዝብ ተዳከሙ፤ ለመሸሽ ወደ ኋላ ተመለሱ ፍርሀትም ያዛቸው፤ የምጥ ጣር እንደ ያዛትም ሴት ተጨነቁ። 25 ያቺ ዝነኛዋና አስደሳችዋ ከተማ እንዴት ባዶዋን ቀረች? 26 በዚያን ቀን የዚያች ከተማ ወጣቶች በከተማይቱ መንገዶች ላይ ይገደላሉ፤ ወታደሮችዋም ይደመሰሳሉ። 27 የደማስቆን ቅጽር ሁሉ በእሳት አጋያለሁ፤ የንጉሥ ቤንሀዳድንም ቤተ መንግሥት በእሳት አቃጥላለሁ፤ እኔ የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ።” በቄዳርና በሐጾር ነገዶች ላይ የተነገረ ትንቢት 28 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ድል ስላደረጋቸው ስለ ቄዳርና ስለ ሐጾር መንግሥታት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ተነሡ፤ በቄዳር ሕዝብ ላይ ዝመቱ፤ የምሥራቅንም ሕዝብ አጥፉ! 29 ድንኳኖቻቸውን፥ መንጋዎቻቸውን፥ መጋረጃዎቻቸውንና ዕቃዎቻቸውን ሁሉ ውሰዱ፤ ግመሎቻቸውን ለራሳችሁ ውሰዱ። ‘በዙሪያው ሽብር ተነሥቷል’ ብለው ይጮኻሉ።” 30 የሐጾር ነዋሪዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በእናንተ ላይ ስለ መከረባችሁና ክፉ ዕቅድ ስላቀደባችሁ ርቃችሁ ሽሹ፤ በጥልቁም ዋሻ ተደበቁ።” 31 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ተነሡ! መዝጊያና መወርወሪያ ሳይኖረው ብቸኛ ሆኖ ወደሚኖርና ተዝናንቶ በሰላም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ ዝመቱ። 32 ግመሎቻቸውና ከብቶቻቸው ይማረካሉ፤ የግንባራቸውን ግራና ቀኝ የተላጩትን ሁሉ በየአቅጣጫው እበትናቸዋለሁ፤ ከየአቅጣጫውም መከራ አመጣባቸዋለሁ።” 33 ስለዚህም ሐጾር ለዘለዓለሙ ቀበሮዎች ብቻ የሚኖሩባት ምድረ በዳ ሆና ትቀራለች፤ ዳግመኛም በዚያ ሰፍሮ የሚኖር ሕዝብ ከቶ አይገኝም። ስለ ዔላም የተነገረ ትንቢት 34 ሴዴቅያስ በይሁዳ ላይ እንደ ነገሠ ወዲያውኑ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ስለ ዔላም አገር ተናገረኝ፤ እንዲህም አለኝ፦ 35 “ዔላምን ይህን ያኽል ኀያል እንድትሆን ያደረጋችኹትን የዔላምን የጦር ኀይል እሰብራለሁ። 36 ከየአቅጣጫውም የሚመታት ነፋስ በዔላም ላይ አስነሣለሁ፤ ሕዝቧንም በየስፍራው እበትናለሁ፤ በዚህም ዐይነት የእርስዋ ስደተኞች የማይኖሩበት አገር አይገኝም። 37 የዔላም ሕዝብ ሕይወታቸውን ሊያጠፉ የሚፈልጉትን ጠላቶቻቸውን እንዲፈሩ አደርጋለሁ። በእነርሱም ላይ ለጥፋታቸው ምክንያት የሆነው ኀይለኛ ቊጣዬን አመጣባቸዋለሁ፤ እስኪያልቁ ድረስ በጦርነት እንዲሳደዱ አደርጋለሁ። 38 ንጉሣቸውንና መሪዎቻቸውን አጠፋለሁ፤ ዙፋኔንም በዚያ እዘረጋለሁ። 39 ሆኖም የዔላምን ንብረት የምመልስበት ጊዜ ይመጣል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” |