መዝሙር 87 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ኢየሩሳሌም የቀረበ ውዳሴ 1 እግዚአብሔር ከተማውን በተቀደሰው ተራራ ላይ መሠረተ። 2 እግዚአብሔር ከእስራኤል መኖሪያዎች ሁሉ ይልቅ የጽዮንን ደጆች ይወዳል። 3 አንቺ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! አስደናቂ ነገሮች ስለ አንቺ ተነግረዋል። 4 ለእኔ በመታዘዝ የሚያገለግሉኝን ሕዝቦች በምመዘግብበት ጊዜ ግብጽንና ባቢሎንን እጨምራለሁ፤ ከኢየሩሳሌም ተወላጆች ጋር የፍልስጥኤምን፥ የጢሮስንና የኢትዮጵያን ሕዝቦች እጨምራለሁ። 5 ልዑል እግዚአብሔር ራሱ ስለሚመሠርታት ስለ ጽዮን፦ “ይህም ሕዝብ፥ ያም ሕዝብ በእርስዋ ውስጥ ተወልደዋል” ይባላል። 6 እግዚአብሔር ሕዝቦችን ሁሉ ይመዘግባል፤ እያንዳንዱንም “በጽዮን የተወለደ” ብሎ ይጠራዋል። 7 ዘማሪዎችና ጨፋሪዎች “የበረከታችን ሁሉ መገኛ ጽዮን ናት” እያሉ በደስታ ይዘምራሉ። |