ዘዳግም 4:34 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ወይስ በፈተና፥ በተአምራትና በድንቅ ነገሮች፥ በጦርነት፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በሚያስፈራ ኀይል፥ በዐይናችሁ እያያችሁት እግዚአብሔር አምላካችሁ እናንተን ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ ያለ አንድን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ መካከል ወስዶ የራሱ ሕዝብ ለማድረግ የሞከረ ሌላ አምላክ አለን? አዲሱ መደበኛ ትርጒም አምላካችሁ እግዚአብሔር በዐይናችሁ እያያችሁ ለእናንተ በግብጽ እንዳደረገው ሁሉ በፈተና፣ በታምራዊ ምልክቶችና በድንቆች፣ በጦርነት፣ በጸናች እጅና በተዘረጋች ክንድ ወይም በታላቅና በአስፈሪ ሥራዎች ከሌላ ሕዝብ መካከል አንድን ሕዝብ የራሱ ለማድረግ የቻለ አምላክ አለን? መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ወይስ በፈተና፥ በተአምራት፥ በድንቅ፥ በጦርነት፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በሚያስፈራም ኃይል፥ በዐይናችሁ ፊት ጌታ አምላካችሁ እናንተን ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ፥ አንድን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ መካከል ወስዶ የራሱ ሕዝብ ለማድረግ የሞከረ ሌላ አምላክ አለን? የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አምላካችን እግዚአብሔር በዐይናችሁ ፊት በግብፅ ለእናንተ እንደ ሠራው ሁሉ ፥ በፈተናና በተአምራት፥ በድንቅና በሰልፍ፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በታላቅም ማስፈራራት እግዚአብሔር ከሌላ ሕዝብ መካከል ገብቶ ለእርሱ ሕዝብን ይወስድ ዘንድ ሞክሮ እንደ ሆነ፥ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አምላካችሁ እግዚአብሔር በዓይናችሁ ፊት በግብፅ ለእናንተ እንደ ሠራው ሁሉ፥ በፈተናና በተአምራት፥ በድንቅና በሰልፍ፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ በታላቅም ማስፈራት እግዚአብሔር ከሌላ ሕዝብ መካከል ገብቶ ለእርሱ ሕዝብን ይወስድ ዘንድ ሞክሮ ነበርን? |
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋው፤ በእጅ እስከሚዳሰስ ድረስ ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ የግብጽን ምድር ይሸፍናል” አለው።
መኳንንቱም ንጉሡን እንዲህ አሉት፤ “ይህ ሰው ለእኛ ወጥመድ ሆኖ የሚያስቸግረን እስከ መቼ ነው? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤላውያን ወገን ወንዶቹ ይሂዱ፤ አገሪቱ በመጥፋት ላይ መሆንዋ አይታወቅህምን?”
ሙሴም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “ይህ ቀን በባርነት ስትገዙ የኖራችሁበትን የግብጽን ምድር ለቃችሁ የወጣችሁበት ስለ ሆነ ይህን ቀን አስታውሱ፤ እግዚአብሔር በታላቅ ኀይሉ በመታደግ ያወጣችሁ በዚህ ቀን ነው፤ ስለዚህ በዚህ ቀን እርሾ የነካው እንጀራ አትብሉ።
“አምላክ ሆይ፥ ከአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅድስናስ እንደ አንተ ያለ ባለግርማ ማን ነው? አንተ ያደረግሃቸውን ተአምራትና አስገራሚ ሥራዎች ሊያደርግ የሚችልስ ማን አለ?
“ ‘እኔ እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረግኹትንና ንስር ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ እንደምትሸከም እኔም እናንተን እስከዚህ ስፍራ እንዴት ወደ እኔ እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል፤
ስለዚህም ለእስራኤላውያን የምለውን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ግብጻውያን ከሚያደርሱባችሁ የባርነት ጭቈና በማዳን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ አሠቃቂ ቅጣት አመጣባቸው ዘንድ የኀይል ክንዴን በእነርሱ ላይ አነሣለሁ፤ እናንተንም እታደጋችኋለሁ፤
እግዚአብሔር ሆይ! ተነሥ፤ ተነሥተህ ኀይልህን ግለጽ! በጥንት ዘመን በነበረው ትውልድ መካከል እንዳደረግኸው ተነሥ፤ ረዓብ የተባለውን የባሕር ዘንዶ ቈራርጠህ ያደቀቅከው አንተ ነህ።
እኛም ይረዳን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮኽን፤ እርሱም ጩኸታችንን ሰምቶ ከግብጽ የሚያወጣንን መልአክ ላከልን፤ እነሆ አሁን እኛ በግዛትህ ወሰን ላይ ባለችው በቃዴስ እንገኛለን።
ልጆቻችሁ ያላዩትና የማያውቁት ቢሆኑም እንኳ፥ እናንተ ዛሬ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ፥ ታላቅነቱን፥ ኀይሉንና ሥልጣኑን ያያችሁ መሆኑን አስታውሱ።
እስራኤል ሆይ! የእርዳታህ ጋሻ፥ የድልህ ሰይፍ መዳንን ከእግዚአብሔር ያገኘ፥ እንዳንተ ያለ ሕዝብ ከቶ የለም፤ ምንኛ የታደልክ ነህ! ጠላቶች እየተለማመጡ ወደ አንተ ሲመጡ ጀርባቸውን ትረግጣለህ።
በግብጽ ምድር ባሪያ የነበርክ መሆንህን አስታውስ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በታላቅ ኀይልና በብርቱ ሥልጣን ከዚያ አወጣህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ታከብር ዘንድ ያዘዘህ ስለዚህ ነው።
በገዛ ዐይኖችህ ያየሃቸውን ታላላቅ መቅሠፍቶች፥ ተአምራትንና ድንቅ ሥራዎችን፥ እንዲሁም እግዚአብሔር አምላክህ አንተን ነጻ ያወጣበትን ታላቅ ኀይሉንና ሥልጣኑን አስታውስ፤ ግብጻውያንን ባጠፋበት ዐይነት ዛሬ አንተ የምትፈራቸውን እነዚህንም ሕዝቦች ሁሉ ያጠፋቸዋል።
እረዳቸው ዘንድ ወደ እኔ ጮኹ፤ እኔም በእነርሱና በግብጻውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረግሁ። ባሕሩም እንዲከነበልባቸው አድርጌ ግብጻውያንን አሰጠምሁ፤ በግብጻውያን ላይ ምን እንዳደረግሁ በዐይኖቻችሁ አይታችኋል፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ለብዙ ጊዜ በበረሓ ኖራችሁ።