መዝሙር 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምታላቁ ንጉሥ 1 ምድርና በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ፥ የእግዚአብሔር ናቸው፤ ዓለምና በውስጥዋ ያሉት ሁሉ የእርሱ ናቸው። 2 ምድርን በባሕር ላይ የመሠረተው፥ ከውሃ በላይም ያጸናው እርሱ ነው። 3 ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል፤ በተቀደሰ ስፍራውስ ማን ይቆማል። 4 ይህን ማድረግ የሚችል፥ እጆቹ ከክፉ ሥራና ልቡም ከክፉ ሐሳብ ንጹሓን የሆኑ፥ ጣዖትን የማያመልክ፥ ዋሽቶ የማይምል ነው። 5 እንዲህ ዐይነቱ ሰው ከአዳኝ አምላኩ ከእግዚአብሔር በረከትንና ፍትሕን ይቀበላል። 6 ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡና የያዕቆብን አምላክ ፊት የሚሹ እንደዚህ ያሉት ሰዎች ናቸው። 7 እናንተ በሮች ራሳችሁን ከፍ አድርጉ፤ የክብር ንጉሥ ይገባ ዘንድ እናንተ ጥንታውያን በሮች ተከፈቱ። 8 ይህ የክብር ንጉሥ ማነው? እርሱ ብርቱና ኀያሉ እግዚአብሔር ነው። እርሱ በጦርነት ኀያሉ እግዚአብሔር ነው። 9 እናንተ በሮች ራሳችሁን ከፍ አድርጉ የክብር ንጉሥ ይገባ ዘንድ እናንተ ጥንታውያን በሮች ተከፈቱ። 10 ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? ይህ የክብር ንጉሥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው! |