ዘዳግም 34 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሙሴ አሟሟት 1 ሙሴም ከሞአብ ሜዳዎች ተነሥቶ ወደ ነቦ ተራራ ወጣ፤ ከኢያሪኮም በስተምሥራቅ ወዳለው ወደ ፒስጋ ተራራ ጫፍ ደረሰ፤ ከዚያም እግዚአብሔር ምድሪቱን በሙሉ አሻግሮ እንዲመለከት አደረገው፤ ይኸውም ከገለዓድ ግዛት አንሥቶ በስተ ሰሜን በኩል እስካለው እስከ ዳን ከተማ፥ 2 የንፍታሌምንም ግዛት በሙሉ፥ የኤፍሬምንና የምናሴን ግዛት፥ በስተምዕራብ እስከ ሜዲቴራኒያን ባሕር ጠረፍ ያለውን የይሁዳን ግዛት፥ 3 ኔጌብንና ሜዳውን፥ የኢያሪኮን ሸለቆ የዘንባባዎች ከተማ የምትባለውን ኢያሪኮን፥ እስከ ጾዓር ድረስ አሳየው። 4 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለዘሮቻቸው አወርሳት ዘንድ ለአብርሃም ለይስሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ቃል የገባሁላቸው የተስፋ ምድር ይህች ናት፤ እነሆ፥ እርስዋን በዐይንህ እንድታያት አድርጌአለሁ፤ ወደዚያች መግባት ግን አይፈቀድልህም።” 5 ስለዚህ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በሞአብ ምድር ሳለ እግዚአብሔር በተናገረው መሠረት በዚያ ሞተ። 6 እግዚአብሔርም ከቤትፐዖር ከተማ ፊት ለፊት በሞአብ አገር በሚገኘው ሸለቆ ቀበረው፤ ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ እርሱ የተቀበረበትን ትክክለኛ ቦታ ለይቶ የሚያውቅ የለም። 7 ሙሴም በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ኻያ ዓመት ነበር፤ ነገር ግን ዐይኑ ያልፈዘዘና ጒልበቱም ያልደከመ ገና ብርቱ ሰው ነበር። 8 የእስራኤልም ሕዝብ የሐዘኑ ጊዜ እስከሚያበቃ ድረስ ለሙሴ በማዘን ሠላሳ ቀን በሞአብ ሜዳ አለቀሱለት። 9 ሙሴ የእርሱ ተተኪ እንዲሆን እጆቹን በመጫን ሹሞት ስለ ነበር የነዌ ልጅ ኢያሱ በጥበብ የተሞላ ሆነ፤ የእስራኤልም ሕዝብ ለኢያሱ ታዘዘለት፤ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጣቸውንም ትእዛዝ ጠበቁ። 10 እግዚአብሔር ፊት ለፊት ያነጋገረው እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ በእስራኤል ከቶ ተነሥቶ አያውቅም፤ 11 እግዚአብሔር ሙሴን ወደ ግብጽ ንጉሥና ወደ መኳንንቱ እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ ልኮ በእርሱ አማካይነት እንዲፈጸሙ ያደረጋቸውን ተአምራትና ድንቅ ሥራዎች ያሳየ ሌላ ነቢይ ከቶ የለም። 12 ሙሴ በእስራኤላውያን ሁሉ ፊት ያደረገውን ዐይነት ታላቅና አስፈሪ ነገር ሁሉ ያደረገ ሌላ ነቢይ ከቶ የለም። |