ዘዳግም 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእስራኤልና የከነዓን ሕዝቦች ( ዘፀ. 34፥11-16 ) 1 “እግዚአብሔር አምላክህ ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር በሚያመጣህ ጊዜ በፊትህ ያሉትን ብዙ ሕዝቦች ያስወግድልሃል፤ እነርሱም ከአንተ በብዛትና በኀይል የሚበልጡት ሰባት የአሕዛብ ነገዶች ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ አሞራውያን፥ ከነዓናውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን ተብለው የሚጠሩት ናቸው። 2 እግዚአብሔር አምላክህ እነዚህን ሁሉ ሕዝቦች ለእናንተ አሳልፎ ሲሰጣቸውና እነርሱን ድል በምትነሣበት ጊዜ ሁሉንም መደምሰስ አለብህ፤ ከእነርሱ ጋር ምንም ዐይነት ውል አታድርግ፤ አትራራላቸውም። 3 ከእነርሱ አትጋባ፤ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆችህ ከእነርሱ ማንንም እንዲያገቡ አትፍቀድላቸው። 4 ይህን ብታደርግ ልጆችህን ከእግዚአብሔር አስኰብልለው ባዕዳን አማልክትን እንዲከተሉ ያደርጉአቸዋል፤ ይህም ከሆነ እግዚአብሔር በአንተ ላይ ተቈጥቶ ወዲያው ያጠፋሃል፤ 5 ነገር ግን በእነርሱ ላይ የምታደርጉት እንደዚህ ነው፦ መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ ከድንጋይ የተሠሩ የጣዖት ማምለኪያ ዐምዶቻቸውንም እያንከታከታችሁ ጣሉ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ሰባብሩ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ፤ 6 አንተ እግዚአብሔር አምላክህ የራሱ ወገን አድርጎ የመረጠህ ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ በምድር ላይ ካሉት ሕዝቦች ሁሉ አንተ ለእርሱ የተለየህ ምርጥ ሕዝብ እንድትሆን አድርጎሃል። 7 “እግዚአብሔር እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች ይበልጥ ብዙዎች በመሆናችሁ አይደለም፤ ይልቁንም እናንተ በምድር ላይ ከሁሉ በቊጥር ያነሳችሁ ሕዝብ ነበራችሁ። 8 ነገር ግን እግዚአብሔር እናንተን ስለ ወደደ ለቀድሞ አባቶቻችሁ የሰጠውን የተስፋ ቃል መጠበቅ ፈለገ፤ በታላቅ ኀይሉ ያዳናችሁና የግብጽ ንጉሥ ባርያዎች ከመሆን ነጻ ያወጣችሁም በዚህ ምክንያት ነበር። 9 ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችሁ በፍጹም የታመነ አምላክ መሆኑን አስታውሱ፤ እርሱ ቃል ኪዳኑን ይጠብቃል፤ ለሚወዱትና ትእዛዞቹንም ለሚፈጽሙ ሁሉ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ዘለዓለማዊ ፍቅሩን ያሳያል። 10 ነገር ግን የሚጠሉትን በማጥፋት ይበቀላል፤ እነርሱንም ከመበቀል ፈጽሞ አይዘገይም። 11 ስለዚህም ዛሬ እኔ ያዘዝኩህን ትእዛዝ፥ ሕግና ሥርዓት በጥንቃቄ ጠብቅ። ለእግዚአብሔር መታዘዝ የሚያስገኘው በረከት ( ዘዳ. 28፥1-14 ) 12 “እነዚህን ትእዛዞች ብታዳምጥና በታማኝነትም ብትፈጽማቸው፥ እግዚአብሔር አምላክህ ለቀድሞ አባቶችህ በመሐላ የሰጠውን ቃል ኪዳንና ዘለዓለማዊ ፍቅር ለአንተም ያጸናልሃል፤ 13 እርሱ አንተን ይወድሃል፤ ይባርክህማል፤ ስለዚህም በቊጥር ትበዛለህ፤ የምትወልዳቸው ልጆች ይባረካሉ፤ የምድርህም ፍሬ ይባረካል፤ ስለዚህም ብዙ እህል፥ ወይንና የወይራ ዘይት ታገኛለህ፤ ከዚህም ጋር ብዙ የከብትና የበግ መንጋ ያበዛልሃል፤ ለአንተ ይሰጥህ ዘንድ ለቀድሞ አባቶችህ ተስፋ በሰጠው ምድር ላይ ይህን ሁሉ በረከት ይሰጥሃል። 14 የአንተን ያኽል በብዙ የተባረከ ሕዝብ በዓለም ላይ ከቶ አይገኝም፤ ከአንተ መካከል ወንድም ሆነ ሴት እንዲሁም ከእንስሶችህ መካከል መኻን አይገኝም። 15 እግዚአብሔር ከበሽታ ሁሉ ይጠብቅሃል፤ በግብጽ አገር በነበርክ ጊዜ ካየኸው አሠቃቂ በሽታ ሁሉ ማንኛውንም በአንተ ላይ አያመጣም፤ ነገር ግን እነዚህን በሽታዎች በሚጠሉህ ላይ ያመጣባቸዋል። 16 እግዚአብሔር በእጅህ ላይ የጣለልህን ሕዝቦች ሁሉ ያለ ርኅራኄ ደምስስ፤ ጣዖቶቻቸውንም ለማምለክ ወጥመድ ውስጥ አትግባ። 17 “ ‘እነዚህ ሕዝቦች ከእኔ ይበልጣሉ፤ እንዴትስ አድርጌ እነርሱን ነቅዬ አወጣቸዋለሁ’ ብለህ በማሰብ 18 አትፍራቸው፤ አምላክህ እግዚአብሔር በግብጽ ንጉሥና በሕዝቡ ሁሉ ላይ ያደረገውን አስታውስ። 19 በገዛ ዐይኖችህ ያየሃቸውን ታላላቅ መቅሠፍቶች፥ ተአምራትንና ድንቅ ሥራዎችን፥ እንዲሁም እግዚአብሔር አምላክህ አንተን ነጻ ያወጣበትን ታላቅ ኀይሉንና ሥልጣኑን አስታውስ፤ ግብጻውያንን ባጠፋበት ዐይነት ዛሬ አንተ የምትፈራቸውን እነዚህንም ሕዝቦች ሁሉ ያጠፋቸዋል። 20 አምላክህ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ሽብር እንዲፈጠር ያደርጋል፤ ከአንተ ሸሽተው የተደበቁት እንኳ ይጠፋሉ። 21 ስለዚህም እነዚህን ሕዝቦች አትፍራ፤ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነው፤ እርሱ ታላቅና መፈራትም የሚገባው አምላክ ነው። 22 አምላክህ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ጥቂት በጥቂት እየነቃቀለ ያስወጣቸዋል፤ እነርሱን ሁሉ በአንድ ጊዜ ማጥፋት አትችልም፤ ይህን ብታደርግ አራዊት በምድሪቱ ላይ በዝተው ያስቸግሩሃል፤ 23 እግዚአብሔር ጠላቶችህን በእጆችህ ላይ ይጥልልሃል፤ እስኪደመሰሱም ድረስ በብርቱ ያሸብራቸዋል፤ 24 ንጉሦቻቸውን በእጅህ ይጥልልሃል፤ እነርሱንም ታጠፋና ስማቸው የተረሳ እንዲሆን ታደርጋለህ፤ ማንም ተቋቊሞ ሊገታህ አይችልም፤ ሁሉንም ታወድማለህ። 25 ጣዖቶቻቸውን በእሳት አቃጥል፤ በእነርሱ ላይ የተለበጠውን ብር ወይም ወርቅ የራስህ ንብረት አድርገህ ለመውሰድ ልብህ አይመኝ፤ ይህን ብታደርግ ወጥመድ ይሆንብሃል፤ እግዚአብሔርም አምልኮ ጣዖትን ስለሚጠላ ብርቱ ጥፋትን ያስከትልብሃል። 26 እነዚህንም የረከሱ ጣዖቶች ወደ ቤትህ አታስገባ፤ ብታስገባ ግን አንተም እንደ እነርሱ ትጠፋለህ፤ እነርሱ ለጥፋት የተገቡ ስለ ሆነ በጣም ልትጠላቸውና ልትጸየፋቸው ይገባል። |