ዘዳግም 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበእግዚአብሔር ላይ ማመፅ የሚያመጣው ችግር 1 “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! አድምጥ፤ ከአንተ የሚበልጡትንና በኀይልም ብርቱ የሆኑትን የአሕዛብ ምድርና ቅጽሮቻቸው እስከ ሰማይ የደረሱ ታላላቅ ከተሞቻቸውን ለመውረስ ትገባ ዘንድ ዛሬ ዮርዳኖስን ትሻገራለህ። 2 በዚያ የሚኖሩ ሕዝቦች ግዙፋን የሆኑ ቁመተ ረጃጅሞችና ብርቱዎች ናቸው፤ እነርሱም ‘ማንም ሊቋቋማቸው የማይችል የዔናቅ ዘሮች ናቸው’ ሲባል ሰምተሃል፤ 3 ነገር ግን እንደሚባላ እሳት የሆነ እግዚአብሔር አምላክህ በፊትህ የሚሄድ መሆኑን ዛሬ ታያለህ፤ አንተ ወደ ፊት በሄድህ መጠን እርሱ ድል ይነሣቸዋል፤ ስለዚህም እርሱ በሰጠው ተስፋ መሠረት እነርሱን ነቃቅለህ በማባረር በፍጥነት ታጠፋቸዋለህ። 4 “እግዚአብሔር አምላካችሁ እነርሱን ከፊታችሁ ካባረረላችሁ በኋላ ‘እግዚአብሔር ወደዚህች ምድር ያመጣን ስለ መልካም ሥራችን ነው’ ብላችሁ አታስቡ፤ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝብ ነቃቅሎ የሚያባርርልህ እነርሱ ክፉዎች ስለ ሆኑ ብቻ ነው። 5 እግዚአብሔር የእነርሱን ምድር እንድትወርስ የፈቀደልህ አንተ ደግ በመሆንህና ትክክለኛውን ነገር በማድረግህ አይደለም፤ እርሱ እነርሱን ነቃቅሎ የሚያባርርበት ምክንያት እነርሱ ክፉዎች ስለ ሆኑና እንዲሁም ለቀድሞ አባቶችህ፥ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ለመጠበቅ ሲል ነው። 6 እንግዲህ አንተ ልብህ የደነደነ እልኸኛ ስለ ሆንክ እግዚአብሔር ይህችን ለም ምድር የሚሰጥህ አንተ እርስዋን ለመውረስ የተገባህ አለመሆንህን ዕወቅ። 7 “እግዚአብሔር አምላክህን በበረሓ እንዴት እንዳስቈጣኸው ከቶ አትርሳ፤ የግብጽን ምድር ለቀህ ከወጣህበት ቀን ጀምሮ እዚህ እስከ መጣህበት እስከ አሁን ድረስ በእርሱ ላይ ዐምፀሃል። 8 በሲና በረሓ እንኳ እናንተን ለማጥፋት እስኪነሣሣ ድረስ እግዚአብሔርን በብርቱ አስቈጥታችሁታል። 9 እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የገባው ቃል ኪዳን የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላቶች ለመቀበል እኔ ወደ ተራራው ወጥቼ ነበር፤ በዚያም ምንም ነገር ሳልበላና ሳልጠጣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ። 10 ከዚያም በኋላ እናንተ በተራራው ግርጌ በተሰበሰባችሁ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የሰማችሁትን ቃል በእጁ የጻፈባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ሰጠኝ። 11 ከአርባ ቀንና ከአርባ ሌሊት በኋላ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን የጻፈባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ሰጠኝ። 12 “ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ ‘ፈጥነህ ከተራራው ራስ ላይ ውረድ፤ ከግብጽ ምድር መርተህ ያወጣኸው ሕዝብህ፥ ክፉ ነገር በማድረግ ረክሶአል፤ እኔ ከሰጠኋቸው ትእዛዝ ሁሉ ወዲያውኑ ርቀው፥ የሚያመልኩትን ጣዖት ለራሳቸው ሠርተዋል።’ 13 “ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ ‘እነሆ፥ ይህ ሕዝብ ልቡ የደነደነ፥ እልኸኛ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ 14 እንግዲህ ተወኝ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ሊያስታውሳቸው በማይችል ሁኔታ ልደምስሳቸው፤ ከዚያም በኋላ አንተን ከእነርሱ ይበልጥ ኀይልና ብዛት ላለው ሕዝብ አባት አደርግሃለሁ።’ 15 “ስለዚህም ቃል ኪዳኑ የተጻፈባቸውን ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች በሁለት እጆቼ እንደ ያዝኩ ከተራራው ተመልሼ ወረድኩ፤ በዚያን ጊዜ የእሳት ነበልባል ከተራራው ይታይ ነበር፤ 16 እናንተም እግዚአብሔር አምላካችሁ ከሰጣችሁ ትእዛዝ ወዲያው ፈቀቅ ብላችሁ፥ ወርቅ አቅልጣችሁ በጥጃ ምስል ጣዖት በመሥራት በእግዚአብሔር ላይ ማመፃችሁን ተመለከትኩ። 17 ስለዚህም የድንጋይ ጽላቶቹን በፊታችሁ ወርውሬ ሰበርኳቸው፤ 18 ከዚህም በኋላ እንደገና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ምንም ነገር ሳልበላና ሳልጠጣ በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፍቼ ቈየሁ። ይህንንም ያደረግኹት እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ኃጢአት ሠርታችሁ እርሱን በማስቈጣታችሁ ምክንያት ነበር። 19 በመዓቱም ሊደመስሳችሁ ስለ ተነሣሣ የእግዚአብሔር ብርቱ ቊጣ አስፈርቶኝ ነበር፤ ነገር ግን እንደገና እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማ። 20 እግዚአብሔር በአሮንም ላይ እጅግ ስለ ተቈጣ ሊገድለው ተቃርቦ ነበር፤ ስለዚህ በዚያው ጊዜ ለአሮንም ጭምር ጸለይኩ፤ 21 ያንንም በጥጃ አምሳል አቅልጣችሁ የሠራችሁትን በኃጢአት የተሞላ አጸያፊ ምስል አንሥቼ እሳት ውስጥ ጣልኩት፤ እርሱንም ሰባብሬ እንደ ትቢያ አደቀቅሁት፤ ትቢያውንም ከተራራው በሚወርደው ውሃ ውስጥ ጨመርኩት። 22 “እንደገናም በታብዔራ፥ በማሳህና በቂብሮት ሐታዋ እግዚአብሔርን አስቈጣችሁት። 23 እግዚአብሔር፥ ‘ሂዱ፤ የሰጠኋችሁንም የተስፋ ምድር ውረሱ’ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁም ጊዜ በእርሱ ላይ ዐመፃችሁ እንጂ አልተማመናችሁበትም፤ ለቃሉም አልታዘዛችሁም። 24 እኔ ካወቅኋችሁ ጊዜ ጀምሮ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ ናችሁ። 25 “ከዚያም ሁሉ የተነሣ በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፍቼ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤ ይህንንም ያደረግኹት እርሱ ‘እደመስሳችኋለሁ’ ብሎ ስለ ነበር ነው፤ 26 እንዲህም ብዬ ጸለይኩ፥ ‘ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ በታላቅ ኀይልህና ብርታትህ ዋጅተህ ከግብጽ ምድር ያወጣኸውን የራስህን ሕዝብ አታጥፋ፤ 27 አገልጋዮችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን አስብ፤ የዚህን ሕዝብ እልኸኛነት፥ ክፋትና ኃጢአት ሁሉ አትቊጠርበት፤’ 28 ይህ ባይሆን ግን፦ ‘እግዚአብሔር በሰጣቸው የተስፋ ቃል መሠረት ሕዝቡን ወደዚያች ምድር ሊያስገባቸው አልቻለም’ ብለው ግብጻውያን መዘባበት ይጀምራሉ፤ እንዲያውም፦ ‘ሕዝቡን ስለ ጠላቸው ሊገድላቸው ፈልጎ ወደ በረሓ አወጣቸው’ ይሉሃል። 29 ከዚህም ሁሉ በላይ ይህ ሕዝብ ለራስህ ወገን እንዲሆን የመረጥከውና በታላቁ ኀይልህና ብርታትህ ከግብጽ ምድር ያወጣኸው ነው።” |