Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ጌታ ለሕዝቡ ከአለት ላይ ውሃ ማፍለቁ
( ዘፀ. 17፥1-7 )

1 በመጀመሪያው ወር መላው የእስራኤል ማኅበር ወደ ጺን ምድረ በዳ መጥተው በቃዴስ ሰፈሩ፤ ማርያምም ስለሞተች በዚያው ተቀበረች።

2 በሰፈሩበት ቦታ ውሃ አልነበረም፤ ስለዚህ ሕዝቡ ሙሴንና አሮንን በመቃወም ተሰብስበው፥

3 እንዲህ በማለት ከሙሴ ጋር ተጣሉ፦ “በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ለፊት ከቀሩት እስራኤላውያን ወገኖቻችን ጋር ሞተን ቢሆን መልካም በሆነ ነበር።

4 የእግዚአብሔርን ማኅበር ወደዚህ ምድረ በዳ ያመጣችሁት እኛና እንስሶቻችን እዚህ እንድናልቅ ለማድረግ ነውን?

5 ከግብጽ አውጥታችሁ ምንም ነገር ወደማይበቅልበት ወደዚህ አስከፊ ምድር ለምን አመጣችሁን? በዚህ ስፍራ እህል፥ በለስ፥ ወይንና ሮማን አይገኝም፤ ሌላው ቀርቶ የሚጠጣ ውሃ እንኳ የለም!”

6 ሙሴና አሮን ከሕዝቡ ፈቅ ብለው ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሄዱ፤ በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ሳሉም የእግዚአብሔር ክብር ተገለጠላቸው።

7 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

8 “በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ያለውን በትር ወስደህ አንተና አሮን ሆናችሁ መላውን ማኅበር በአንድነት ሰብስቡ፤ እዚያም በእነርሱ ሁሉ ፊት ሆነህ ያንን አለት ውሃውን እንዲያወጣ እዘዘው፤ በዚህ ዐይነት ከአለቱ ውስጥ ውሃ ታወጣላቸዋለህ፤ እንዲሁም እነርሱና እንስሶቻቸውም ጠጥተው ይረካሉ።”

9 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ከድንኳኑ ውስጥ በትሩን አመጣ።

10 እርሱና አሮን መላውን ማኅበር በአለቱ ፊት ለፊት እንዲሰበሰቡ ካደረጉ በኋላ ሙሴ ሕዝቡን “እናንተ ዐመፀኞች! ከዚህ አለት ለእናንተ ውሃ እናውጣላችሁን?” አላቸው።

11 ከዚህ በኋላ ሙሴ በትሩን አንሥቶ አለቱን ሁለት ጊዜ መታው፤ ታላቅ የውሃ ምንጭም ከውስጡ ፈሰሰ፤ ሕዝቡና እንስሶቹም ሁሉ ጠጡ።

12 ነገር ግን እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ሲል ገሠጻቸው፤ “በእስራኤላውያን ፊት የተቀደሰ ክብሬን ትገልጡ ዘንድ ስላላመናችሁብኝ፥ ልሰጣቸው ቃል ወደገባሁላቸው ምድር የዚህ ሕዝብ መሪዎች ሆናችሁ አትገቡም።”

13 የእስራኤል ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር የተጣሉበትና እርሱም የቅድስናውን ክብር የገለጠበት ስፍራ መሪባ ስለ ተባለ ውሃውም የመሪባ ውሃ ነው።


እስራኤላውያን በኤዶም በኩል ማለፍ መከልከላቸው

14 ሙሴ ለኤዶም ንጉሥ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት መልእክተኞችን ከቃዴስ ላከ፤ “ወንድምህ እስራኤል እንዲህ ይላል፦ በእኛ ላይ የደረሰውን ችግር ሁሉ ሰምተሃል፤

15 የቀድሞ አባቶቻችን እንዴት ወደ ግብጽ እንደ ወረዱና እኛም በግብጽ ለብዙ ዓመቶች እንዴት እንደ ኖርን ታውቃለህ፤ ግብጻውያን የቀድሞ አባቶቻችንም ሆነ እኛን በብርቱ አሠቃይተዋል፤

16 እኛም ይረዳን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮኽን፤ እርሱም ጩኸታችንን ሰምቶ ከግብጽ የሚያወጣንን መልአክ ላከልን፤ እነሆ አሁን እኛ በግዛትህ ወሰን ላይ ባለችው በቃዴስ እንገኛለን።

17 ስለዚህ በምድርህ አልፈን እንድንሄድ እባክህ ፍቀድልን፤ እኛም ሆንን ከብቶቻችን ከመንገድ ውጪ አንወጣም፤ ወደ እርሻዎችህም ሆነ ወደ ወይን ተክሎችህ አንገባም፤ ከውሃ ጒድጓዶችህም አንጠጣም፤ ግዛትህን እስክናልፍ ድረስ ከዋናው መንገድ አንወጣም።”

18 ኤዶማውያን ግን እንዲህ አሉ፤ “በአገራችን አልፋችሁ እንድትሄዱ አንፈቅድላችሁም! ለመግባት ብትሞክሩ ግን በሰልፍ ወጥተን እንወጋችኋለን።”

19 የእስራኤል ሕዝብም “እኛ ከዋናው መንገድ አንወጣም፤ እኛ ወይም እንስሶቻችን ከውሃችሁ ብንጠጣ እንኳ ዋጋ እንከፍላችኋለን፤ እኛ የምንፈልገው በምድራችሁ አልፈን መሄድ ብቻ ነው” ሲሉ መለሱላቸው።

20 ኤዶማውያን ግን “አይሆንም! አናሳልፋችሁም!” አሉ፤ ብርቱ የጦር ሠራዊትም አሰልፈው የእስራኤልን ሕዝብ ሊወጉ ወጡ።

21 ኤዶማውያን እስራኤላውያን በግዛታቸው አልፈው እንዳይሄዱ በመከልከላቸው ምክንያት እስራኤላውያን መንገድ ለውጠው በሌላ በኩል ሄዱ።


የአሮን ሞት

22 መላው የእስራኤል ማኅበር ከቃዴስ ተነሥተው በመጓዝ ወደ ሖር ተራራ ደረሱ፤

23 ይህም በኤዶም ወሰን ላይ የሚገኝ ስፍራ ነው፤ እዚያም እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

24 “አሮን ለእስራኤላውያን ልሰጣቸው ቃል ወደገባሁላቸው ምድር አይገባም፤ እናንተ ሁለታችሁ በመሪባ ውሃ ዘንድ በትእዛዜ ላይ ስላመፃችሁ አሮን ይሞታል።

25 አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ ወደ ሖር ተራራ ውጣ።

26 እዚያም የአሮንን የክህነት ልብስ አውልቀህ አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም በዚያ ይሞታል።”

27 ሙሴም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ፤ መላው ማኅበር እየተመለከታቸው ወደ ሖር ተራራ ወጡ፤

28 ሙሴም የአሮንን የክህነት ልብስ አውልቆ አልዓዛርን አለበሰው፤ እዚያም በተራራው ጫፍ ላይ አሮን ሞተ፤ ሙሴና አልዓዛርም ተመልሰው ከተራራው ወረዱ፤

29 መላው ማኅበር አሮን እንደ ሞተ ሰሙ፤ እስከ ሠላሳ ቀንም ድረስ በሐዘን አለቀሱለት።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos