ኤርምያስ 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ኢየሩሳሌም ድል መሆን የተነገረ ትንቢት 1 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ የመልክያን ልጅ ፓሽሑርንና የመዕሤያን ልጅ ካህኑን ሶፎንያስን ወደ እኔ ልኮ እንዲህ ሲል አስጠየቀኝ፦ 2 “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከነሠራዊቱ ከተማይቱን ለመውጋት በመክበብ ላይ ይገኛል፤ ስለዚህ ምናልባት በረድኤት ከእኛ ጋር ሆኖ ድንቅ ሥራውን በመግለጥ ናቡከደነፆርን እንዲመለስ ያደርግልን እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ጠይቅልን።” 3 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ቃሉን ስለ ነገረኝ ወደ እኔ ተልከው የመጡትን ሰዎች ለሴዴቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት አልኳቸው፥ 4 “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል፤ ‘ሴዴቅያስ ሆ! ከቅጽርህ በስተውጪ በኩል ከበባ ያደረጉብህን የባቢሎንን ንጉሥና ባቢሎናውያንን የምትዋጋበት የጦር መሣሪያ አንተን ተመልሶ እንዲያጠቃ አደርጋለሁ፤ የጦር መሣሪያውንም በከተማይቱ መካከል እንዲከመር አደርጋለሁ። 5 እኔ ራሴ በሚነድ ቊጣ፥ በታላቅ ተግሣጽ በኀይሌና በሥልጣኔ አንተን እዋጋለሁ። 6 በዚህች ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ እመታለሁ፤ ሰዎችና እንስሶች በአንድነት በአሠቃቂ ወረርሽኝ ያልቃሉ፤ 7 አንተና መኳንንትህ ከወረርሽኝ፥ ከጦርነትና ከራብ የሚተርፉትንም ሕዝብ በሙሉ በንጉሥ ናቡከደነፆርና ሊገድሉህ በሚፈልጉህ ጠላቶችህ እንድትማረኩ አደርጋለሁ፤ እርሱም ምሕረት ወይም ርኅራኄ በማሳየት አንድ ሰው እንኳ አይተውልህም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ” 8 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ብዬ እንድናገር አዘዘኝ፦ “እነሆ አድምጡ! እኔ እግዚአብሔር ወደ ሕይወት የሚወስደውንና ወደ ሞት የሚያደርሰውን መንገድ በፊታችሁ አኑሬአለሁ፤ ከሁለቱ አንዱን ምረጡ፤ 9 በዚህች ከተማ የሚቀሩ ሁሉ በጦርነት ወይም በራብ፥ ወይም በወረርሽኝ ይሞታሉ፤ አሁን ከተማይቱን ከበው ወዳሉት ወደ ባቢሎናውያን ሄዶ እጁን የሚሰጥ ግን አይሞትም፤ ሌላው ቢቀር ሕይወቱን ያተርፋል፤ 10 ይህች ከተማ እንድትጠፋ ወስኛለሁ፤ ፈጽሞም ምሕረት አላደርግላትም፤ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” በይሁዳ ንጉሣዊ ቤተሰብ ላይ የተሰጠ ፍርድ 11-12 የዳዊት ዘሮች ለሆኑት ለይሁዳ ንጉሣዊ ቤተሰብ እንድነግራቸው እግዚአብሔር የሰጠኝ ቃል ይህ ነው፦ “እኔ እግዚአብሔር የምነግራችሁን አድምጡ፤ በየማለዳው ፍትሕ እንዳይጓደል አድርጉ፤ አንዱ ሌላውን በመቀማት ግፍ እንዳይሠራበት ጠብቁ፤ ይህን ባታደርጉ ግን ከምትሠሩት ክፋት የተነሣ ቊጣዬ እንደ እሳት ይነዳል፤ ሊያጠፋውም የሚችል አይኖርም፤ 13 አንቺም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ በሜዳ ላይ እንደሚገኝ ቋጥኝ ከሸለቆዎች በላይ ከፍ ብለሽ ትታዪአለሽ፤ ነገር ግን እኔ እዋጋሻለሁ፤ አንቺ ግን ማንም የሚደፍርሽና ምሽጎችሽን ጥሶ የሚገባ ያለ አይመስልሽም፤ 14 ነገር ግን ስላደረግሽው ነገር ሁሉ እኔ እቀጣሻለሁ፤ ቤተ መንግሥትሽ በእሳት እንዲቃጠል አደርጋለሁ፤ ያም እሳት በዙሪያው የሚገኘውን ነገር ሁሉ ያጋያል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” |