ዘዳግም 26:5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚያ በኋላ በእግዚአብሔር አምላክህ ፊት ይህን መግለጫ ስጥ፦ ‘አባቴ ከቦታ ወደ ቦታ በመዞር የሚኖር ሶርያዊ ነበር፤ ጥቂት ቤተሰብ ይዞ ወደ ግብጽ በመውረድ መጻተኛ ሆኖ ኖረ፤ ጥቂት የነበረው ታላቅ፥ ኀያል፥ ብዙ ሕዝብ ሆነ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም አንተም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፤ “አባቴ ዘላን ሶርያዊ ነበር፤ ከጥቂት ሰዎችም ጋራ ወደ ግብጽ ወረደ፤ በዚያም ተቀመጠ፤ ታላቅ፣ ኀያልና ቍጥሩ የበዛ ሕዝብ ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አንተም በጌታ እግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፥ ‘አባቴ ከቦታ ወደ ቦታ በመዞር የሚኖር ሶርያዊ ነበር፤ ከጥቂት ሰዎችም ጋር ወደ ግብጽ ወርዶ እዚያ ተቀመጠ። ከዚያም ታላቅ፥ ኀያልና ቁጥሩ የበዛ ሕዝብ ሆነ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለህ ተናገር፦ አባቴ ከሶርያ ወጥቶ ወደ ግብፅ ወረደ፤ በዚያም በቍጥር ጥቂት ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ታላቅና የበረታ፥ ብዙም ሕዝብ ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለህ ተናገር፦ አባቴ የተቅበዘበዘ ሶርያዊ ነበረ፤ በቁጥር ጥቂት ሳለ ወደ ግብፅ ወረደ በዚያም ተቀመጠ፤ ታላቅ የሆነ የበረታም ቁጥሩም የበዛ ሕዝብ ሆነ። |
ይስሐቅ የባቱኤልን ልጅ ርብቃን ሲያገባ አርባ ዓመት ሆኖት ነበር፤ የርብቃ አባት ባቱኤልና ወንድምዋ ላባ በመስጴጦምያ የሚኖሩ ሶርያውያን ነበሩ፤
አባቱ ስለ መረቀው ዔሳው ያዕቆብን አጥብቆ ጠላው፤ በልቡም “አባቴ በቅርብ ቀን ይሞታል፤ ከዚያ በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ” ብሎ አሰበ።
በዚህ ሁኔታ ይስሐቅ ያዕቆብን አሰናበተው፤ ያዕቆብም በመስጴጦምያ ወደሚኖረው ወደ ላባ ሄደ፤ ላባ የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም ነበረ፤ አባቱም ሶርያዊው ባቱኤል ነበር።
ለዮሴፍ በግብጽ ከተወለዱት ከሁለቱ ወንዶች ልጆች ጋር፥ ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የገቡት የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ቊጥር በአጠቃላይ ሰባ ነበር።
በከነዓን ምድር ራብ እጅግ ከመበርታቱ የተነሣ ለእንስሶቻችን ግጦሽ ስላጣን ለጊዜው በዚህች አገር ለመኖር መጥተናል፤ ስለዚህ አገልጋዮችህ በጌሴም ምድር እንድንኖር ፍቀድልን።”
ነገር ግን እስራኤላውያን በተጨቈኑ መጠን ቊጥራቸው ይበልጥ እየበዛና በምድሪቱም ላይ እየተስፋፉ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሣ ግብጻውያን እስራኤላውያንን ፈሩአቸው።
የቀድሞ አባቶችህ ወደ ግብጽ በወረዱ ጊዜ ብዛታቸው ሰባ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔር አምላክህ የአንተን ቊጥር ብዛት እንደ ሰማይ ከዋክብት አድርጎታል።
“እግዚአብሔር እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች ይበልጥ ብዙዎች በመሆናችሁ አይደለም፤ ይልቁንም እናንተ በምድር ላይ ከሁሉ በቊጥር ያነሳችሁ ሕዝብ ነበራችሁ።