ዘፍጥረት 47 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውንና ፍየሎቻቸውን ከብቶቻቸውንና ሌላም ያላቸውን ነገር ሁሉ ይዘው ከከነዓን ወደዚህ መጥተዋል፤ አሁንም በጌሴም ምድር ይገኛሉ” አለው። 2 ከወንድሞቹ መካከል መርጦ ያመጣቸውንም አምስቱን ወንድሞቹን ወደ ፈርዖን አቀረባቸው። 3 ፈርዖንም የዮሴፍን ወንድሞች፦ “የምትተዳደሩበት ሥራ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱለት፥ “እኛ አገልጋዮችህ በግ አርቢዎች ነን፤ አባቶቻቸንም ይተዳደሩበት የነበረ ሥራ ይኸው ነበር። 4 በከነዓን ምድር ራብ እጅግ ከመበርታቱ የተነሣ ለእንስሶቻችን ግጦሽ ስላጣን ለጊዜው በዚህች አገር ለመኖር መጥተናል፤ ስለዚህ አገልጋዮችህ በጌሴም ምድር እንድንኖር ፍቀድልን።” 5 ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፥ “አባትህና ወንድሞችህ ከመጡልህ፤ 6 እነሆ፥ መላው የግብጽ ምድር የአንተ ነው፤ ስለዚህ አባትህና ወንድሞችህ ምርጥ በሆነችው በጌሴም ምድር እንዲኖሩ አድርግ። ከእነርሱ መካከል ልዩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ካሉ፥ በእኔ እንስሶች ላይ የበላይ ኀላፊዎች አድርገህ ሹማቸው።” 7 ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን ወደ ፈርዖን አቀረበው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው፤ 8 ፈርዖንም “ዕድሜህ ስንት ነው?” በማለት ያዕቆብን ጠየቀው። 9 ያዕቆብም “በመንከራተት ያሳለፍኳቸው ዘመናት መቶ ሠላሳ ናቸው። እነርሱም የቀድሞ አባቶቼ በመንከራተት ካሳለፉአቸው ዘመናት እጅግ ያነሡና ችግር የበዛባቸው ናቸው” አለ። 10 ያዕቆብ ፈርዖንን ባረከውና ተሰናብቶት ወጣ። 11 ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱና ወንድሞቹ በግብጽ ምድር እንዲቀመጡ አደረገ፤ ፈርዖን ባዘዘው መሠረት በግብጽ ምድር ምርጥ የሆነውን፥ በራምሴ ከተማ አጠገብ ያለውን ቦታ በይዞታ ሰጣቸው። 12 ዮሴፍ ለአባቱና ለወንድሞቹ በልጆቻቸው ቊጥር ልክ እህል ይሰጣቸው ነበር። የራቡ ጽናትና የዮሴፍ አመራር 13 ይሁን እንጂ ራቡ እየጸና ስለ ሄደ፥ ከየትም አገር እህል ለማግኘት አልተቻለም ነበር፤ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦችም በረሀቡ እጅግ ተጐድተው ነበር። 14 ስለዚህ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች ወደ ዮሴፍ እየመጡ እህል ሲሸምቱ፥ ዮሴፍ ገንዘቡን ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ግምጃ ቤት ያስገባው ነበር። 15 በዚህ ሁኔታ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች ገንዘባቸውን በእህል ሸመታ ስለ ጨረሱ፥ ግብጻውያን ወደ ዮሴፍ ተሰብስበው መጥተው “የምንመገበው እህል ስጠን! ገንዘባችንን ስለ ጨረስን በራብ ማለቃችን ነው!” አሉት። 16 ዮሴፍም “ገንዘባችሁ ካለቀ ከብቶቻችሁን አምጡና በእነርሱ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። 17 እነርሱም ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸውና በአህዮቻቸው፥ በበጎቻቸውና በፍየሎቻቸው በከብቶቻቸውም ለውጥ እህል ሰጣቸው፤ ያንንም ዓመት በሙሉ በከብቶቻቸው ልዋጭ እህል ሰጣቸው። 18 በሚቀጥለውም ዓመት ወደ እርሱ መጡና እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ! ከአንተ የምንሰውረው ነገር የለም፤ ገንዘባችን ሁሉ አልቆአል፤ ከብቶቻችንንም ለአንተ አስረክበናል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው ከሰውነታችንና ከመሬታችን በቀር ሌላ ምንም ነገር የለንም። 19 እኛና ምድራችን በፊትህ እንጥፋን? እኛንና መሬታችንን ገዝተህ እህል ስጠን፤ እኛ የንጉሡ ባሪያዎች እንሆናለን፤ መሬታችንም የእርሱ ይሁን፤ በልተን በሕይወት እንድንኖር እህል ስጠን፤ በመሬታችን ላይ የምንዘራውም ዘር ስጠን።” 20 ዮሴፍ በግብጽ ያለውን መሬት ሁሉ ለንጉሡ ገዛ፤ ከራቡ ጽናት የተነሣ ግብጻውያን ሁሉ መሬታቸውን መሸጥ ግድ ሆነባቸው፤ በዚህ ዐይነት መሬት ሁሉ የንጉሡ ንብረት ሆነ። 21 ዮሴፍ በግብጽ አገር ዳር እስከ ዳር ያሉት ሰዎች ሁሉ የንጉሡ ባሪያዎች እንዲሆኑ አደረገ። 22 ዮሴፍ ያልገዛው የካህናቱን መሬት ብቻ ነው፤ ካህናት ከፈርዖን በየጊዜው ድርጎ ይቀበሉ ስለ ነበር መሬታቸውን ለመሸጥ አልተገደዱም። 23 ዮሴፍ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፥ እንግዲህ እናንተንና መሬታችሁን ለፈርዖን ስለ ገዛሁ ዘር ውሰዱና በመሬታችሁ ላይ ዝሩ። 24 ነገር ግን በመከር ጊዜ ከምታመርቱት ከአምስት አንዱን እጅ ለፈርዖን መስጠት አለባችሁ፤ የቀረው አራት አምስተኛው እጅ ግን ለመሬታችሁ ዘር፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ ለቤተሰባችሁም ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ።” 25 ሕዝቡም “ጌታችን ሆይ፥ ሕይወታችንን ስላዳንክልንና መልካም ነገር ስላደረግህልን ሁላችንም የፈርዖን ባሪያዎች እንሆናለን” አሉት። 26 በዚህ ዐይነት ዮሴፍ ከመከር ሁሉ አንድ አምስተኛው እጅ ለፈርዖን እንዲሰጥ የግብጽን መሬት ይዞታ በሚመለከት ሕግ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ድረስ ይሠራበታል፤ የፈርዖን ንብረት ያልሆነው የካህናት መሬት ብቻ ነው። የያዕቆብ የመጨረሻ ማሳሰቢያ 27 እስራኤላውያን በግብጽ አገር ጌሴም በተባለ ምድር ይኖሩ ነበር፤ እዚያም ብዙ ሀብት አገኙ፤ ብዙ ልጆችም ወለዱ። 28 ያዕቆብ ዐሥራ ሰባት ዓመት በግብጽ አገር ኖረ፤ ዕድሜውም መቶ አርባ ሰባት ዓመት ሆኖት ነበር። 29 ያዕቆብ የሚሞትበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ልጁን ዮሴፍን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በፊትህ ሞገስን አግኝቼ ከሆነ፥ በምሞትበት ጊዜ በግብጽ ምድር እንዳትቀብረኝ፥ እጅህን በጒልበቴ ላይ አኑረህ በመሐላ ቃል ግባልኝ። 30 አባቶቼ በተቀበሩበት መቃብር መቀበር ስለምፈልግ በምሞትበት ጊዜ ከግብጽ አገር ወስደህ፥ እነርሱ በተቀበሩበት ስፍራ ቅበረኝ።” ዮሴፍም “እሺ እንዳልከኝ አደርጋለሁ” አለው። 31 ያዕቆብም “ይህን እንደምታደርግ በመሐላ ቃል ግባልኝ” አለው። ዮሴፍ ይህንኑ በመሐላ አረጋገጠለት፤ ያዕቆብም በመኝታው ላይ እንዳለ በመስገድ እግዚአብሔርን አመሰገነ። |