Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 43 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የዮሴፍ ወንድሞች ብንያምን ይዘው እንደገና ወደ ግብጽ መሄዳቸው

1 በከነዓን ምድር ራቡ እጅግ እየበረታ ሄደ፤

2 የያዕቆብ ቤተሰብ ከግብጽ የመጣውን እህል ተመግበው በጨረሱ ጊዜ አባታቸው “እንደገና ወደ ግብጽ ሂዱና ጥቂት እህል ሸምቱልን” አላቸው።

3 ይሁዳ ግን ለአባቱ እንዲህ ብሎ መለሰለት፥ “ሰውየው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ እፊቴ እንዳትቀርቡ’ በማለት በብርቱ አስጠንቅቆናል፤

4 ስለዚህ ወንድማችንን ይዘን እንድንሄድ ከፈቀድክልን ሄደን እህል እንሸምትልሃለን።

5 ይህን የማትፈቅድልን ከሆነ ግን ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ እፊቴ እንዳትቀርቡ’ ስላለን ወደዚያ አንሄድም።”

6 ያዕቆብም “ ‘ሌላ ወንድም አለን’ ብላችሁ ለሰውየው በመናገር ለምን ይህን ያህል መከራ አመጣችሁብኝ?” አለ።

7 እነርሱም “ሰውየው ስለ ራሳችንና ስለ ቤተሰባችን አጥብቆ መረመረን፤ ‘አባታችሁ በሕይወት አለን? ሌላስ ወንድም አላችሁን?’ ብሎ ጠየቀን፤ እኛም ለጥያቄው ተገቢውን መልስ ሰጠን፤ ስለዚህ ሰውየው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ እንድትመጡ’ እንደሚለን እንዴት ልናውቅ እንችል ነበር?”

8 ይሁዳም አባቱን እንዲህ አለ፤ “ልጁን በእኔ ኀላፊነት አብሮን እንዲሄድ አድርግ፥ ሳንዘገይ አሁኑኑ ጒዞ እንጀምር፤ ይህ ከሆነ፥ እኛም አንተም ልጆቻችንም ሁሉ በራብ ከመሞት እንድናለን።

9 ልጁን በእኔ ዋስትና ስጠኝ፤ ስለ እርሱ እኔ ተጠያቂ እሆናለሁ፤ በደኅና ወደ አንተ መልሼ ባላመጣው በሕይወቴ ዘመን ተወቃሽ ልሁን።

10 ይህን ያህል ባንዘገይ ኖሮ እስከ አሁን ሁለት ጊዜ እዚያ ደርሰን መመለስ በቻልን ነበር።”

11 አባታቸው ያዕቆብም እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ መሄዳችሁ የማይቀር ከሆነ ለአገረ ገዢው ገጸ በረከት የሚሆን ምድራችን ከምታፈራው ምርጥ ነገር ሁሉ በስልቻዎቻችሁ ጨምራችሁ ሂዱ፤ ይኸውም በለሳን፥ ማር፥ ቅመማ ቅመም፥ ከርቤ፥ ተምርና ለውዝ ይዛችሁ ሂዱ።

12 ከዚህ በፊት በየስልቻዎቻችሁ ጫፍ ተመልሶ የነበረው ገንዘብ በስሕተት ሊሆን ስለሚችል እጥፍ ገንዘብ ይዛችሁ ሂዱ።

13 ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደ ሰውየው በቶሎ ሂዱ።

14 ብንያምንና ሌላውንም ወንድማችሁን መልሶ እንዲሰጣችሁ ሁሉን የሚችል አምላክ የዚያን ሰው ልብ ያራራላችሁ። እኔ በበኩሌ ልጆቼን ካጣሁ፥ ባዶ እጄን መቅረቴ ነው።”

15 ስለዚህ ወንድማማቾቹ ገጸ በረከቱንና እጥፍ ገንዘብ ይዘው ከብንያም ጋር ወደ ግብጽ ለመሄድ ጒዞ ጀመሩ፤ እዚያም በደረሱ ጊዜ ወደ ዮሴፍ ፊት ቀረቡ።

16 ዮሴፍ ብንያምን ከእነርሱ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ ጠራውና “እነዚህን ሰዎች ወደ ቤት ውሰዳቸው፤ ዛሬ ቀን ከእኔ ጋር ምሳ ስለሚበሉ አንድ ከብት ዕረድና አዘጋጅ” አለው።

17 አዛዡም ዮሴፍ በነገረው መሠረት ሰዎቹን ወስዶ ወደ ቤት አስገባቸው።

18 “ወደ እዚህ ያመጡን በመጀመሪያ ጊዜ በስልቻዎቻችን ውስጥ ተመልሶ ስለ ተገኘው ገንዘብ ሳይሆን አይቀርም” በማለት፤ ሰዎቹ ወደ ዮሴፍ ቤት በሚሄዱበት ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ “በዚህ ምክንያት ያሠቃዩናል፤ አህዮቻችንን ወስደው እኛንም የእነርሱ ባሪያዎች ያደርጉናል” ብለውም አሰቡ።

19 ስለዚህ ወደ ቤቱ በር አጠገብ ሲደርሱ የቤቱን አዛዥ እንዲህ አሉት፤

20 “ጌታዬ ከዚህ በፊት እህል ለመሸመት ወደዚህ መጥተን ነበር፤

21 ስንመለስ በመንገድ ለዐዳር በሰፈርንበት ቦታ ስልቻዎቻችንን ስንፈታ የያንዳንዳችንን ገንዘብ ምንም ሳይጐድልለት በየስልቻዎቻችን አፍ ላይ ተቋጥሮ አገኘነው። እነሆ፥ ያንን ገንዘብ መልሰን አምጥተናል።

22 አሁን እህል የምንሸምትበትንም ገንዘብ በተጨማሪ ይዘናል፤ በዚያን ጊዜ ገንዘባችንን መልሶ በየስልቻዎቻችን ማን እንደ ከተተው አናውቅም።”

23 የቤቱም አዛዥ “በዚህ ጉዳይ ጭንቀትና ፍርሀት አይድረስባችሁ፤ የእናንተና የአባታችሁ አምላክ ይህን ገንዘብ በየስልቻዎቻችሁ አስቀምጦላችሁ ይሆናል፤ የእናንተን ገንዘብ ግን እኔ ተቀብዬአለሁ” አላቸው። ከዚህ በኋላ ስምዖንን ወደ እነርሱ አመጣው።

24 የቤቱ አዛዥ ወንድማማቾቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባቸውና እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ ሰጣቸው፤ ለአህዮቻቸውም ገፈራ ሰጣቸው።

25 ከዮሴፍ ጋር ምሳ እንደሚበሉ ተነግሮአቸው ስለ ነበር፥ ዮሴፍ በምሳ ሰዓት እስከሚመጣ ድረስ ለእርሱ የሚያቀርቡለትን ስጦታ አዘጋጁ።

26 ዮሴፍ ወደ ቤት በገባ ጊዜ፥ እርሱ ወዳለበት ክፍል ገብተው ያመጡትን ስጦታ አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት።

27 እርሱም ስለ ደኅንነታቸው ከጠየቃቸው በኋላ “ያ የነገራችሁኝ ሽማግሌ አባታችሁ እንዴት ነው? አሁንም በሕይወት አለን?” አላቸው።

28 እነርሱም “አገልጋይህ አባታችን በሕይወት አለ፤ ጤንነቱም የተሟላ ነው” አሉት። ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት።

29 ዮሴፍ የእናቱ ልጅ የሆነውን ወንድሙን ብንያምን ባየው ጊዜ “ ‘ታናሽ ወንድም አለን’ ብላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ይህ እርሱ ነውን?” አለና “ልጄ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለው።

30 ዮሴፍ ወንድሙን በማየቱ ስሜቱ ስለ ተነካ ከዚያ ተነሥቶ ሄደ፤ ወደ እልፍኙም ገብቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።

31 ፊቱንም ከታጠበ በኋላ ወጣ፤ ራሱንም በመቈጣጠር ምሳ እንዲቀርብ አዘዘ።

32 ግብጻውያን ከዕብራውያን ጋር አብሮ መመገብን እንደ ጸያፍ ይቈጥሩት ስለ ነበር ለዮሴፍ ብቻውን አንድ ገበታ፥ ለወንድማማቾቹ ሌላ ገበታ፥ እዚያ ይመገቡ ለነበሩ ግብጻውያንም ሌላ ገበታ ተዘጋጀ፤

33 ወንድማማቾቹ ከታላቁ አንሥቶ እስከ ታናሹ በዕድሜ ተራ በዮሴፍ ፊት ለፊት ተቀመጡ፤ እንዴት እንደ ተቀመጡ ባዩ ጊዜ በመደነቅ እርስ በርሳቸው ተያዩ።

34 ለዮሴፍ ከቀረበለት ምግብ እየተወሰደ ይሰጣቸው ነበር፤ ለብንያም ግን ከሌሎቹ አምስት እጥፍ ተሰጠው፤ በዚህ ዐይነት ከዮሴፍ ጋር እስኪጠግቡ በልተው ጠጥተው ተደሰቱ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos