ዘፍጥረት 31 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምያዕቆብ ከላባ ተሰውሮ መሄዱ 1 የላባ ወንዶች ልጆች “ያዕቆብ የአባታችንን ሀብት ወሰደ፤ ይህን ሁሉ ሀብት ያገኘው ከአባታችን ነው” እያሉ መናገራቸውን ያዕቆብ ሰማ። 2 በላባም ዘንድ እንደ ቀድሞው ተወዳጅ አለመሆኑን ተረዳ። 3 በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ያዕቆብን “ወደ አባቶችህና ወደ ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” አለው። 4 ስለዚህ ያዕቆብ መንጋዎቹ ወደ ተሰማሩበት መስክ እንዲመጡ ራሔልንና ልያን አስጠራቸው፤ 5 እንዲህም አላቸው፤ “አባታችሁ እንደ ቀድሞው ጊዜ እንደማይወደኝ ተረድቼአለሁ፤ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር አለ፤ 6 ጒልበቴን ሳልቈጥብ በትጋት አባታችሁን እንዳገለገልኩ እናንተም ታውቃላችሁ፤ 7 እርሱ ግን ዐሥር ጊዜ ደመወዜን በመለዋወጥ አታለለኝ፤ ሆኖም እኔን ለመጒዳት እግዚአብሔር አልፈቀደለትም፤ 8 ላባ ‘ዝንጒርጒሮቹ ሁሉ ለአንተ ደመወዝ ይሁኑ’ ባለኝ ጊዜ፥ መንጋዎቹ ሁሉ ዝንጒርጒር ወለዱ፤ ደግሞም ‘ሽመልመሌ መሳዮቹ ሁሉ ለአንተ ደመወዝ ይሁኑ’ ባለኝ ጊዜ፥ መንጋዎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መሳዮች ወለዱ። 9 እግዚአብሔር የአባታችሁን የላባን መንጋዎች ወስዶ ለእኔ የሰጠኝ በዚህ ዐይነት ነው። 10 “እንስሶቹ ለመፅነስ ፍትወት በሚያድርባቸው ወራት የሚያጠቁአቸው አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፥ ዝንጒርጒርና ነቊጣ መሆናቸውን በሕልም አየሁ። 11 በዚያው ሕልም የእግዚአብሔር መልአክ ‘ያዕቆብ!’ ብሎ ጠራኝ፤ እኔም ‘እነሆ፥ አለሁ!’ አልኩ። 12 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘መንጋዎቹን የሚያጠቁአቸው አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፥ ዝንጒርጒርና ነቊጣ ያለባቸው መሆናቸውን ተመልከት፤ ላባ የፈጸመብህን በደል ስላየሁ ይህን ያደረግኹት እኔ ነኝ፤ 13 የመታሰቢያ ድንጋይ አቁመህ ዘይት በመቀባት በተሳልክበት ቦታ በቤትኤል የተገለጥኩልህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ አሁንም ከዚህ አገር በፍጥነት ወጥተህ ወደ ተወለድክበት አገር ተመለስ።’ ” 14 ራሔልና ልያ ለያዕቆብ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “በአባታችን ቤት የውርስ ድርሻ ቀርቶልናልን? 15 እርሱ እኛን የሚያየን እንደ ባዕድ አይደለምን? አስቀድሞ ሸጦን ነበር፤ አሁን ደግሞ ለእኛ ዋጋ የተከፈለውን ሁሉ አጥፍቶታል፤ 16 አሁንም እግዚአብሔር ከአባታችን ወስዶ ለአንተ የሰጠህ ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ሁሉ አድርግ።” 17 ያዕቆብም ተነሥቶ ልጆቹንና ሚስቶቹን በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ 18 በመስጴጦምያ ሳለ ያገኛቸውን መንጋዎችና ዕቃዎችን ሁሉ ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ሄደ። 19 ላባ በጎች ሊሸልት ሄዶ ስለ ነበር፥ እርሱ በሌለበት ራሔል በቤት የነበሩትን የአባቷን ጣዖቶች ሰርቃ ሄደች። 20 ያዕቆብ መሄዱን ለላባ ሳይገልጥለት አታሎት ሄደ፤ 21 የራሱ የሆነውን ሀብት ይዞ በፍጥነት ተጓዘ፤ የኤፍራጥስንም ወንዝ ተሻግሮ ወደ ኮረብታማው አገር ወደ ገለዓድ ሄደ። ያዕቆብ በጒዞ ላይ ሳለ ላባ መከታተሉ 22 ያዕቆብ በስውር መሄዱን ላባ ከሦስት ቀን በኋላ ሰማ፤ 23 ከዘመዶቹ ጋር ሆኖ ያዕቆብን ተከታተለው፤ ሰባት ቀን ከተጓዘ በኋላ ገለዓድ በተባለው ተራራማ አገር ላይ ሊደርስበት ተቃረበ። 24 በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ለላባ በሕልም ተገለጠለትና “ያዕቆብን፥ ክፉም ሆነ ደግ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ” አለው። 25 ያዕቆብ ገለዓድ በተባለው ኮረብታማ ስፍራ ድንኳኑን በመትከል ሰፍሮ ሳለ ላባ ደረሰበት፤ ላባና ዘመዶቹም እዚያው ድንኳናቸውን ተክለው ሰፈሩ። 26 ከዚህ በኋላ ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “ስለምን እንዲህ አድርገህ አታለልከኝ? ሴቶች ልጆቼንስ በጦርነት እንደ ተማረኩ ያኽል ይዘሃቸው ለምን ሄድክ? 27 ሳትነግረኝ ተሰውረህ በመሄድ ለምን አታለልከኝ? ነግረኸኝ ቢሆን ኖሮ በከበሮና በመሰንቆ እየተዘፈነ በደስታ በሸኘሁህ ነበር። 28 ልጆቼንና የልጅ ልጆቼን በመሳም እንድሰናበታቸው አላደረግህም፤ ይህ ያደረግኸው ነገር ስሕተት ነው። 29 ጒዳት ላደርስብህ እችል ነበር፤ ነገር ግን ባለፈው ሌሊት የአባትህ አምላክ ‘ያዕቆብን፥ ክፉም ሆነ ደግ አንድ ቃል እንዳትናገረው’ ብሎ አስጠነቀቀኝ፤ 30 ወደ ትውልድ አገርህ ለመመለስ ባለህ ብርቱ ፍላጎት እንደ ተለየኸኝ ዐውቃለሁ፤ ታዲያ የቤቴን ጣዖቶች የሰረቅህብኝ ለምንድን ነው?” 31 ያዕቆብም “ሴቶች ልጆችህን ነጥቀህ ትወስድብኛለህ ብዬ ስለ ፈራሁ ነው፤ 32 ከእኛ መካከል የአንተ ጣዖቶች የተገኙበት ሰው ቢኖር ግን ይሙት፤ እነሆ፥ አሁን ዘመዶቻችንን ምስክር በማድረግ የአንተ የሆነውን ነገር ሁሉ ፈልገህ ውሰድ” አለው፤ ያዕቆብ ይህን ያለው ራሔል የአባቷን ጣዖቶች ሰርቃ እንደ ወሰደች ስላላወቀ ነው። 33 ከዚህ በኋላ ላባ ወደ ያዕቆብ ወደ ልያና ወደ ሁለቱ አገልጋዮች ድንኳን ተራ በተራ ገብቶ በረበረ፤ ነገር ግን ምንም አላገኘም፤ በመጨረሻ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ፤ 34 ራሔል ግን ጣዖቶቹን ወስዳ በግመሉ ኮርቻ ሥር በመሰወር በላያቸው ላይ ተቀምጣባቸው ነበር፤ ላባ በድንኳኑ ውስጥ ያለውን ጓዝ ሁሉ በርብሮ ምንም ነገር አላገኘም። 35 ራሔልም አባቷን “ጌታዬ በወር አበባዬ ምክንያት መነሣት ስላልቻልኩ ቅር አትሰኝብኝም” አለችው። ላባ በሁሉ ስፍራ ፈልጎ ጣዖቶቹን ማግኘት አልቻለም። 36 በዚህ ጊዜ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ላባን በቊጣ ቃል ተናገረው፤ “ታዲያ፥ የፈጸምኩት በደል ምንድን ነው? እስቲ ምን አጥፍቼ ነው እንዲህ የምታሳድደኝ? 37 ዕቃዬን ሁሉ ከበረበርክ በኋላ የአንተ የሆነ ነገር ምን አግኝተሃል? አንዳች ነገር አግኝተህ ቢሆን በአንተና በእኔ ዘመዶች ፊት እዚህ አቅርበው፤ እነርሱም ከአንተና ከእኔ አጥፊው ማን እንደሆን ይፍረዱ። 38 ከአንተ ጋር መኖር ከጀመርኩ ኻያ ዓመት ሆነኝ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ በጎችህና ፍየሎችህ የጨነገፉበት ጊዜ የለም፤ ከመንጋህም አንድ ጠቦት እንኳ በልቼ አላውቅም፤ 39 ከበጎችህ አንዱን አውሬ ሲበላው ወዲያው እከፍልህ ነበር እንጂ የእኔ ስሕተት ያለመሆኑን ለማስረዳት ወደ አንተ አምጥቼው አላውቅም፤ በቀንም ቢሆን በሌሊት የተሰረቀ እንስሳ ቢኖር ታስከፍለኝ ነበር። 40 ብዙ ጊዜ በቀን ሐሩርና በሌሊት ቅዝቃዜ እሠቃይ ነበር፤ በቂ እንቅልፍ ያገኘሁበት ጊዜ አልነበረም። 41 ከአንተ ጋር የነበርኩበትን ኻያ ዓመት ያሳለፍኩት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ከዚህም ዐሥራ አራቱን ዓመት ያገለገልኩህ ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ለማግኘት ብዬ ነው፤ የቀሩትን ስድስት ዓመቶች ያገለገልኩህ መንጋዎችህን ለማግኘት ብዬ ነው። ይህም ሆኖ ደመወዜን ዐሥር ጊዜ ለዋወጥክብኝ። 42 አባቴ ይስሐቅ የሚያመልከው የአብርሃም አምላክ ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ ባዶ እጄን በሰደድከኝ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር መከራዬንና ልፋቴን አይቶ ባለፈው ሌሊት ገሥጾሃል።” በያዕቆብና በላባ መካከል የተደረገ ስምምነት 43 ላባም ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “እነዚህ ሴቶች የእኔ ልጆች ናቸው፤ ልጆቻቸውም የእኔው ናቸው፤ እነዚህም መንጋዎች የእኔ ናቸው፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ የምታየው ሁሉ የራሴ ነው፤ ነገር ግን ልጆቼንም ሆነ ልጆቻቸውን ለማስቀረት ምንም ማድረግ አልቻልኩም፤ 44 ስለዚህ እኔና አንተ በመሐላ የስምምነት ውል እናድርግ፤ ለምናደርገው ውል ምስክር ሆኖ እንዲኖር ድንጋይ ሰብስበን በመከመር ሐውልት እናቁም።” 45 ስለዚህ ያዕቆብ ትልቅ ድንጋይ አንሥቶ የመታሰቢያ ሐውልት እንዲሆን አቆመው። 46 ቤተሰቡንም ሁሉ “ድንጋይ ሰብስቡ” አላቸው፤ ድንጋይ ሰብስበው ከቈለሉ በኋላም በአጠገቡ ተቀምጠው ምግብ ተመገቡ። 47 ላባም ይጋርሣሀዱታ ብሎ ጠራት፤ ያዕቆብም ገለዓድ ብሎ ሰየማት። 48 ላባም “እነሆ፥ ዛሬ ይህ የድንጋይ ካብ በእኔና በአንተ መካከል ምስክር ነው” አለ። ገለዓድ ተብላ የተጠራችበት ምክንያት ለዚህ ነው። 49 ላባም “እንግዲህ ከዚህ በምንለያይበት ጊዜ እግዚአብሔር እኔንና አንተን ይጠብቀን” በማለት ያንኑ ስፍራ ምጽጳ ብሎ ጠራው። 50 ላባም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ልጆቼን ብታጒላላቸው ወይም ሌሎችን ሴቶች በላያቸው ብታገባ ምንም እንኳ እኔ ላውቅ ባልችል እግዚአብሔር ምስክራችን መሆኑን አትርሳ። 51 በመካከላችን የቈለልኩት ድንጋይና ያቆምኩት ሐውልት እነሆ፥ 52 እኔ አንተን ለማጥቃት ይህን የድንጋይ ቊልል እንደማላልፍ፥ አንተም እኔን ለማጥቃት ይህን የድንጋይ ቊልልና ይህን የመታሰቢያ ሐውልት እንደማታልፍ፥ ይህ የድንጋይ ቊልልና ይህ የመታሰቢያ ሐውልት ምስክሮች ናቸው። 53 ይህንን ሳናደርግ ብንቀር ግን ከአብርሃም አምላክ፥ ከናኮር አምላክና ከአባታቸውም አምላክ ቅጣት ይድረስብን።” ከዚህ በኋላ ያዕቆብ አባቱ ይስሐቅ በሚያመልከው አምላክ ስም ይህን ቃል ለመጠበቅ ማለ። 54 በተራራውም ላይ ያዕቆብ መሥዋዕት አቀረበ፤ ሰዎቹን ሁሉ ጠርቶም ምግብ እንዲመገቡ አደረገ፤ ከበሉም በኋላ ሌሊቱን በዚያ አሳለፉ። 55 በማግስቱ ላባ ጥዋት በማለዳ ተነሥቶ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን በመሳምና በመመረቅ ተሰናበታቸው፤ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ። |