Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 27 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ይስሐቅ ያዕቆብን መረቀው

1 ይስሐቅ አርጅቶ ዐይኖቹም ፈዘው ነበር፤ ታላቁን ልጁን ዔሳውን “ልጄ ሆይ!” ብሎ ጠራው፤ ልጁም “እነሆ፥ አለሁ!” አለ።

2 ይስሐቅም እንዲህ አለው፤ “እንደምታየኝ አርጅቼአለሁ፤ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም፤

3 ስለዚህ የምታድንበትን ቀስትና ፍላጻ ያዝ፤ ወደ ዱር ሂድና አውሬ አድነህ ሥጋ አምጣልኝ፤

4 ልክ እንደምወደው አድርገህ የጣፈጠ ምግብ ሠርተህ አምጣልኝ፤ ከበላሁም በኋላ ከመሞቴ በፊት የመጨረሻ ምርቃቴን እሰጥሃለሁ።”

5 ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው የሚለውን ሁሉ ርብቃ ትሰማ ነበር፤ ስለዚህ ዔሳው ወደ አደን ከሄደ በኋላ፥

6 ርብቃ ልጅዋን ያዕቆብን “አባትህ ወንድምህን ዔሳውን እንዲህ ሲለው ሰማሁ፤

7 ‘አውሬ አድነህ ሥጋ አምጣልኝ፤ ልክ እንደምወደው አድርገህ የጣፈጠ ምግብ ሥራልኝ፤ ሳልሞትም በእግዚአብሔር ፊት እመርቅሃለሁ፤’

8 አሁንም ልጄ ሆይ፥ የምነግርህን አድምጥ፤ የማዝህንም አድርግ፤

9 አባትህ እንደሚወደው አጣፍጬ ጥሩ ምግብ እንድሠራለት፥ ወደ መንጋዎች ሂድና ሁለት የሰቡ የፍየል ጠቦቶችን አምጣልኝ፥

10 አንተም ያዘጋጀሁትን ምግብ እንዲበላ ለአባትህ ወስደህ ታቀርብለታለህ፤ በዚህ ዐይነት አባትህ ከመሞቱ በፊት ይመርቅሃል።”

11 ያዕቆብ ግን እናቱን ርብቃን “የወንድሜ የዔሳው ገላ ጠጒራም ነው፤ የእኔ ገላ ግን ምንም ጠጒር የሌለው ለስላሳ ነው፤

12 ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝና እንዳታለልኩት ቢያውቅ በምርቃት ፈንታ ርግማን እንደማተርፍ ታውቂ የለምን?” አላት።

13 እናቱም “ልጄ ሆይ፥ የአንተ ርግማን በእኔ ላይ ይሁን፤ አሁንም እንደ ነገርኩህ አድርግ፤ ሄደህ ጠቦቶቹን አምጣልኝ” አለችው።

14 ስለዚህ ሄዶ ጠቦቶቹን አመጣላት፤ እርስዋም ልክ አባቱ እንደሚወደው አድርጋ ጥሩ ወጥ ሠራች፤

15 የታላቁ ልጅዋን የዔሳውን የክት ልብስ ከተቀመጠበት ቦታ አውጥታ ለያዕቆብ አለበሰችው።

16 የፍየሎቹንም ቆዳ በክንዶቹ ላይና ጠጒር በሌለበት በአንገቱ ላይ አለበሰችው።

17 ያዘጋጀችውንም ጥሩ ወጥ ከጋገረችው እንጀራ ጋር ለልጅዋ ለያዕቆብ ሰጠችው።

18 ያዕቆብም ወደ አባቱ ሄደና “አባባ!” አለው፤ እርሱም “እነሆ፥ አለሁ! ለመሆኑ አንተ የትኛው ልጄ ነህ?” አለ።

19 ያዕቆብም “የበኲር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ እነሆ፥ እንዳዘዝከኝ አድርጌአለሁ፤ እንድትመርቀኝ እስቲ ቀና በልና ያመጣሁልህን የአደን ሥጋ ተመገብ” አለው።

20 ይስሐቅም “ልጄ ሆይ፥ እንዴት በቶሎ ልታገኝ ቻልክ?” አለው። ያዕቆብም “አምላክህ እግዚአብሔር ስለ ረዳኝ በቶሎ ለማግኘት ቻልኩ” አለው።

21 ይስሐቅም “እስቲ ወደ እኔ ቀረብ በልና ልዳብስህ፤ በእርግጥ አንተ ዔሳው ነህን?” አለው።

22 ያዕቆብም ወደ አባቱ ተጠጋ፤ አባቱም ዳሰሰውና “ድምፅህ የያዕቆብን ድምፅ ይመስላል፤ ክንድህ ግን የዔሳውን ክንድ ይመስላል” አለው።

23 ክንዶቹ እንደ ዔሳው ክንዶች ጠጒራም ስለ ነበሩ ይስሐቅ ያዕቆብን ለይቶ ማወቅ አልቻለም፤ ሊመርቀው ከተዘጋጀ በኋላ፥

24 “በእርግጥ አንተ ልጄ ዔሳው ነህን?” ሲል እንደገና ጠየቀው፤ እርሱም “አዎ፥ ነኝ” አለ።

25 ይስሐቅም “ልጄ በል ከአደንከው ሥጋ አቅርብልኝ፤ ከበላሁም በኋላ እመርቅሃለሁ” አለው። ያዕቆብም ምግቡን አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም እንዲጠጣ አመጣለት።

26 ከዚህ በኋላ አባቱ ይስሐቅ “ልጄ ሆይ፥ ቀረብ በልና ሳመኝ” አለው፤

27 ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው። ይስሐቅ የያዕቆብን ልብስ ባሸተተ ጊዜ እንዲህ ሲል መረቀው፥ “እነሆ የልጄ መልካም ሽታ፥ እግዚአብሔር እንደ ባረከው የእርሻ ሽታ ነው፤

28 እግዚአብሔር ከሰማይ የሚያረሰርስ ጠል ይስጥህ! ምድርህን ያለምልምልህ! እህልህንና ወይንህን ያብዛልህ!

29 መንግሥታት ይገዙልህ፤ ሕዝቦችም ያገልግሉህ፤ በወንድሞችህ ሁሉ ላይ አለቃ ሁን፤ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤ የሚመርቁህም የተመረቁ ይሁኑ።”


ዔሳው የይስሐቅን በረከት መለመኑ

30 ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃና ያዕቆብም ከአባቱ ፊት እንደ ወጣ ወዲያው ወንድሙ ዔሳው ከአደን ተመልሶ መጣ።

31 እርሱም በበኩሉ የጣፈጠ ወጥ ሠርቶ ለአባቱ አቀረበለትና “አባቴ ሆይ፥ እንድትመርቀኝ፥ እስቲ ቀና ብለህ ካመጣሁልህ የአደን ሥጋ ብላ” አለው።

32 ይስሐቅም “አንተ ማን ነህ?” አለው። እርሱም “እኔ የበኲር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለ።

33 ይስሐቅም እጅግ ደንግጦ እየተንቀጠቀጠ “ታዲያ፥ አውሬ አድኖ ያመጣልኝ ማን ነበር? ልክ አንተ ከመምጣትህ በፊት ተመገብኩ፤ የመጨረሻ ምርቃቴንም ሰጠሁት፤ ምርቃቱም የእርሱ ሆኖ ይኖራል” አለው።

34 ዔሳው ይህን በሰማ ጊዜ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ እያለቀሰ “አባቴ ሆይ! እኔንም መርቀኝ!” አለ።

35 ይስሐቅም “ወንድምህ መጥቶ እኔን በማታለል የአንተን ምርቃት ወስዶብሃል” አለው።

36 ዔሳውም “እርሱ እኔን ሲያሰናክለኝ ይህ ሁለተኛው ነው፤ ያዕቆብ መባሉ ተገቢ ነው፤ ከዚህ በፊት ብኲርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ፤ ታዲያ፥ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለምን?” አለው።

37 ይስሐቅም “ቀደም ብዬ እርሱን የአንተ ጌታ አድርጌዋለሁ፤ ወንድሞቹ ሁሉ የእርሱ አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጌአለሁ፤ እህልና የወይን ጠጅ እንዲበዛለት አድርጌአለሁ፤ ልጄ ሆይ! እንግዲህ ለአንተ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?” አለው።

38 ዔሳውም “አባቴ ሆይ! ምርቃትህ አንዲት ብቻ ናትን? እባክህ እኔንም መርቀኝ” እያለ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ።

39 ይስሐቅም እንዲህ አለው፤ “በረከት ከሞላበት ለምለም ምድር ርቀህ ትኖራለህ፤ የሰማይ ጠልም አታገኝም፤

40 በሰይፍህ ኀይል ትኖራለህ፤ የወንድምህም አገልጋይ ትሆናለህ፤ በተቃወምከው ጊዜ ግን ከእርሱ ጭቈና ትላቀቃለህ።”

41 አባቱ ስለ መረቀው ዔሳው ያዕቆብን አጥብቆ ጠላው፤ በልቡም “አባቴ በቅርብ ቀን ይሞታል፤ ከዚያ በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ” ብሎ አሰበ።

42 ነገር ግን ርብቃ የዔሳውን ዕቅድ ስለ ሰማች፥ ያዕቆብን ጠርታ እንዲህ አለችው፤ “አድምጠኝ፤ ወንድምህ ዔሳው አንተን በመግደል ሊበቀልህ አስቦአል፤

43 አሁንም ልጄ ሆይ፥ የምልህን አድርግ፤ ተነሥተህ በካራን ወደሚኖረው ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሽሽ፤

44 የወንድምህ ቊጣ እስኪበርድ ድረስ ለጥቂት ጊዜ እዚያው ቈይ፤

45 ቊጣውም ሲበርድ ያደረግህበትን ነገር ይረሳል፤ ከዚያ በኋላ ሰው ልኬ አስመጣሃለሁ፤ ለምን ሁለታችሁንም በአንድ ቀን ልጣ?”


ይስሐቅ ያዕቆብን ወደ ላባ መላኩ

46 ርብቃ ይስሐቅን “ዔሳው ባገባቸው በእነዚህ በሒታውያን ሴቶች ምክንያት መኖሬን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ደግሞ ከነዚህ ከሒታውያን ሴቶች አንዲቱን ካገባ ከመኖር ይልቅ ሞቴን እመርጣለሁ” አለችው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos